ለምርት አሰባሰብ ትኩረት እንስጥ!

ግብርና የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕይወት መሰረት ነውና ስለግብርናው ዘርፍ ደግሞ ደጋግሞ ማውራት ተገቢም አስፈላጊም ነው:: የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሰረትም እንደመሆኑ የዚህ ወሳኝ ዘርፍ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል::

በተለይም በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከፍተኛው ዓመታዊ የግብርና ምርት የሚገኝበት፣ የመኸር እርሻ ምርት ስብሰባ ስራ በሚከናወንበት በአሁኑ ወቅት ስለግብርናው መጠየቅና መከታተል በእጅጉ ያስፈልጋል:: የግብርና ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ከ2016/17 የመኸር እርሻ 616 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል:: ይህን እቅድ ለማሳካት የምርት አሰባሰብ ስራን በከፍተኛ ጥንቃቄና ትጋት ማከናወን ያስፈልጋል::

በምርት አሰባሰብ ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮች ከፍተኛ የምርት ብክነት እንዲከሰት ያደርጋሉ:: የምርት ብክነት መከሰት ደግሞ በኅብረተሰቡና በሀገሪቱ ላይ ተራዛሚ ተፅዕኖዎችን የሚያስከትሉ ችግሮችን ይፈጥራል::

የምርት አሰባሰብ ስራ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት በሚገባ ካልተከናወነ፣ በተለይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚከሰት ከሆነ ይገኛል ተብሎ በሚጠበቀው ምርት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል፤ ይህም እንደ ምርት ብክነት ካሉት ችግሮች ጋር ሲደማመር የምርት እጥረት እንዲፈጠርና የዋጋ ንረት እንዲከሰት ምክንያት መሆናቸው አይቀርም::

ሀገሪቱ ከበቂ በላይ የምታመርታቸው የሰብል አይነቶች ጭምር ዋጋቸው ሰማይ እያነካ ያለበትን ሁኔታ በተደጋጋሚ እንታዘባለን:: ለአብነት ያህል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከበቂ በላይ ተመርተው ከማሳ የሚያነሳቸው አጥተው ለብክነት እንደሚዳረጉ የምርቶቹ ባለቤቶች ሲናገሩ ደግመን ደጋግመን ሰምተናል:: በከተሞች ያለው የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ግን ‹‹ጆሮ አይስማ›› የሚያሰኝ ነው::

የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ለማሳያነት ያህል ተጠቀሰ እንጂ በሌሎቹም ምርቶች ላይ ተመሳሳይ ችግር መከሰቱ አይቀርም:: የዚህ ችግር ስር ቢመዘዝ ምርት አሰባሰብ ድረስ እንደሚዘልቅ አያጠራጥርም:: አሁን ባለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ላይ ተጨማሪ የዋጋ ንረት ከተፈጠረ ለኅብረተሰቡ ኑሮ ፈተና ይሆናል፤ ይህ እንዳይሆን በሌላው የግብርናው ስራ የተሰጠው ትኩረት በምርት አሰባሰቡም በጉልህ መታየት ይኖርበታል::

መንግሥት በተለይ በግብርና ምርቶች ላይ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ለማስቀረት አንዱ መፍትሄ አቅርቦት ላይ መስራት መሆኑን በማመን በግብርናው ዘርፍ ላይ በስፋት እየሰራ ነው:: ይህን ተከትሎም የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መጥቷል:: ዘንድሮም ይሄው እንደሚሆን ይጠበቃል:: ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ምርቱ በተገቢው መንገድና በወቅቱ ተሰብስቦ ጎተራ ሲገባ ነው:: ያለንበት ወቅት ይህን ማድረግን የግድ ይላል::

የምርት ስብሰባ ስራው ምርትን ሰብሰቦ በጥንቃቄ ለፍጆታም ይሁን ለገበያ የማቅረብ ተግባርን ያካተተ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ይገባል:: ይህን በማድረግ እያደገ ለመጣው የምግብና የገበያ ፍላጎት በጊዜ እና በጥራት ተወዳዳሪ የሆነ ም ላሽ መስጠት እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ በቂ የሰብል ምርት ማቅረብ እና ዋና ዋና የምግብ ሰብሎች ለዘላቂ የግብርና ልማት ያላቸውን ሚና ማሳደግ ይቻላል::

የምርት ብክነትን ከሚቀንሱ ዘዴዎች መካከል አንዱ፣ ምርትን በዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ መሳሪያዎች መሰብሰብ ነው:: ይህ ግብርናውን በቴክኖሎጂ የማዘመን ተግባር የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ ሀገሪቱ የግብርና አቅሟን በመጠቀም ከድህነት እንድትላቀቅ ለማድረግ ከሚቀርቡ ምክረ ሃሳቦች መካከል አንዱ ነው:: በተለይ ትርፍ አምራች በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የማጨጃና የመውቂያ ማሽኖችን የሚያገኙባቸውን አሰራሮችን መዘርጋት እጅግ አስፈላጊ ነው:: ይህን አሰራር በመተግበር የምርት ጥራትን መጨመርና ብክነትን መቀነስ ይቻላል::

የምርት ብክነት እንዳይፈጠር ከሚደረገው ጥረት ባሻገር፣ የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹም መትጋት ያስፈልጋል:: የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን እንዲሰበስብ አሳስቧል:: አንዳንድ ክልሎችም ተማሪዎች በምርት ስብሰባ ስራ ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ አድርገዋል:: እንዲህ ዓይነቶቹ ተገቢ ውሳኔዎች የመኸር እርሻ ምርት በሚሰበሰብባቸው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊተገበሩ ይገባል:: ሰብሎች ከታጨዱ በኋላም በፍጥነትና በጥንቃቄ ወደ አውድማ እንዲገቡ መደረግ አለበት::

በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል:: በመንግሥትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ትብብር በተተገበሩት ተከታታይነት ያላቸው የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ያሳደጉና የሕዝቡን፣ በተለይም የአርሶ አደሩን፣ ሕይወት ያሻሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል:: ከግብርና የሚገኘው ምርት በየዓመቱ ጭማሬ አሳይቷል፤ቁጥሩ ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍልም ከድህነት መላቀቅ ችሏል:: የግብርናና ገጠር ልማትን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች ብዙ ባለሀብት አርሶ አደሮችን መፍጠርም ችለዋል::

ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ካላት አቅም አንፃር ሲመዘኑ ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና፣ የስራ እድል ፈጠራና የምጣኔ ሀብት እድገትም ሆነ ለዘርፉ ችግሮች አስተማማኝ መፍትሄ የሰጡ አይደሉም:: አሁንም ግብርናው በዘላቂነት ከኋላ ቀር አስተራረስና ከዝናብ ጥገኝነት አልተላቀቀም፤የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በብዛት ከመጠቀም የራቀ ሆኖ ይታያል:: ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች እየኖሩ ነው:: በአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ከተወጠነ ቢቆይም፣ እስካሁን እውን ማድረግ አልተቻለም::

የምርት አሰባሰብን ጨምሮ በሌሎች የግብርናው ዘርፍ ስኬት ግብዓቶች ላይ የሚስተዋለው የትኩረት እጥረት የዘርፉ ልማት እንቅፋት እንዳይሆን መስራት ቀጣዩ ተግባር መሆን ይኖርበታል:: የዘርፉ ልማት በምርት አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችንም በመሙላት መደገም ይኖርበታል::

ወቅቱ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመኸር እርሻ ምርት የሚሰበሰብበት ጊዜ በመሆኑ፣ ዋናው ሀገራዊ ትኩረት የምርት አሰባሰብ ሊሆን ይገባል:: የምርት አሰባሰቡ ዕለታዊ ክትትል ይፈልጋል፤የጎደለውን መሙላት፤የተበላሸውን ማስተካከል ያስፈልጋል:: ኢትዮጵያ ለብዙ ሰብሎች ተስማሚ ስነ-ምህዳር ያላት ቢሆንም የሰብሎቹ ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ አለማደጉ፣ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል:: ይህን ችግር ለማቃለል ከሚያስችሉ የመፍትሄ አማራጮች መካከል አንዱ ለምርት አሰባሰብ ስራ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ነው::

የመኸር እርሻ ምርት ስብሰባ ስራ በሚከናወንበት በዚህ ወቅት አርሶ አደሩ፣ የልማት ጣቢያ ሰራተኛው እንዲሁም አመራሩ ሁሉ ወደ ማሳ ዘልቆ ደፋ ቀና ማለት አለበት:: አርሶ አደሩ ምርቱን ይሰብስብ፤የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ሙያዊ/ቴክኒካዊ ድጋፍ ያድርጉ፤አመራሩ ደግሞ ከአርሶ አደሩና ከባለሙያዎች በሚቀርቡ ጥያቄዎች መሰረት የጎደለው እንዲሟላ ትዕዛዝ ይስጥ፤ክትትል ያድርግ!

ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ አጨዳና ድህረ ምርት አያያዝ ድረስ ለሰብሎች ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ በግብርና ሚኒስቴር የብርዕና አገዳ ሰብሎች አመራረት ኤክስቴንሽን ማኑዋል ላይ በዝርዝር ተብራርቷል:: የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ይህን የምርት አመራረት መመሪያ ከአርሶ አደሩ ልምድና ተሞክሮ ጋር በማቀናጀት እንዲተገበር በብርቱ መትጋት ይኖርባቸዋል::

የሰብል መሰብሰቢያና መውቂያ ማሽነሪዎችን አቀናጅቶ ማሰማራት ወሳኝ ስራ ተደርጎ ሊሰራበት ይገባል:: ማሽነሪዎቹን ከዞን ዞን፣ ከክልል ክልል በማንቀሳቀስ ጭምር የአዝመራ ስብሰባው ስኬታማ እንዲሆን መረባረብ ያስፈልጋል::

የዚህ ወሳኝ ዘርፍ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል:: ዘርፉ ለአፍታም ቢሆን ትኩረት ሊነፈገው አይገባም:: ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግብርናን ዘንግተው መኖር አይችሉም:: ቢያንስ፣ ለዓመታት የተመኘነው ‹‹ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ›› እውን እስከሚሆን ድረስ ግብርናውን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት አንችልም!

ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You