የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ከተሞች ለዘርፉ ያላቸውን አስተዋጽኦ ከፍ ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፡- የከተማ ቱሪዝም ከፍተኛ የገበያ ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ በኢትዮጵያ ያሉትን ከተሞች ዘርፉን ለማሳደግ መጠቀም እንደሚገባ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በዓለም ለ45ኛ ጊዜ በሀገሪቱ ለ37ኛ ጊዜ የሚከበረውን የቱሪዝም ቀን አስመልክቶ “ዘመናዊነት አዲስ ከተማነትና ዕድገት’’ በሚል መሪ ሃሳብ በትናንትናው እለት ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ የቱሪዝም ልማት ስራዎች ውስጥ የከተማ ቱሪዝም የሚጠቀስ ሲሆን፤ ይህም የከተማ እድገት ለቱሪዝም እድገት ትልቅ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 50 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በከተማ የሚኖር ሲሆን፤ የከተማ ቱሪዝም ከ20 በመቶ በላይ የገበያ ድርሻ የሚይዝ ዘርፍ ነው ያሉት አቶ ስለሺ፤ ኢትዮጵያ ከሁለት ሺህ በላይ ከተሞች ያሉባት ሀገር በመሆኗ የከተማ ቱሪዝም ለማሳደግ ወሳኝ ዘርፍ ነው ብለዋል።

በከተማ ውስጥ የሚጎበኙ መስህቦች፣ ጎብኚዎች የሚንቀሳቀሱበት የትራንስፖርት አማራጭ እና ከጉብኝት በኋላ ማረፊያ፣ መዝናኛና መመገቢያ ቦታ ቱሪዝም የሚጠይቃቸው መሰረታዊ ነገሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የቱሪዝም ልማት ስራዎች የከተማ ቱሪዝምን ለማጠናከርና ለማስፋፋት ብሎም እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ አስፈላጊ የሆኑ የቱሪዝም መሰረታዊ ምሰሶዎች የሚያሟሉ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ስለሺ እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ከተማ በውጭ ቱሪስቶች ዘንድ እንደ መተላለፊያ ታገለግል የነበረች ከተማ ሆና ቆይታለች። አሁን ላይ በተሰሩ የቱሪስት መሰረተ ልማትና የመዳረሻ ማስፋፊያ ስራዎች የቱሪስቶች መዳረሻ መሆን ችላለች።

በመዲናዋ የሀገር ወስጥ ጎብኚዎች የሚጎበኟቸው ቦታዎች እንዳልነበሩ አንስተው፤ አሁን ላይ ባሏት የቱሪዝም መዳረሻዎች ከፍተኛ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከመፍጠር ባለፈ ከተማዋ ተመራጭ ዓለም አቀፍ ሁነት አስተናጋጅና የተቋማት መቀመጫ መሆኗን አስታውቀዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጡ የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ አንዱ የከተሞችና የነዋሪዎችን አኗኗር ሁኔታ አካታች፣ ሰላማዊና ችግሮች ቢመጡ መቋቋም የሚችል ማድረግ ያስፈልጋል የሚል መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ከተሞች ዘላቂ እድገት እንዲኖራቸው አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለከተማ እድገት የመሰረተ ልማት መስፋፋት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ የባህል መዛባት እንዳይከሰት ማድረግ እንዲሁም የከተማ ቱሪዝም ራሱን የቻለ የተቀናጀ የጉብኝት ጥቅል ሊኖር ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቱሪዝም የሰዎች እንቅስቃሴ እና የተለያዩ ባህልና እሴቶች ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ የአንድን ሀገር ሰላም ለማምጣት የሚችል ትልቁ መሳሪያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You