የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ አሠራርን ማቅለል እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ:- የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማሳደግ መንግሥት ዘንድሮ የያዘውን እቅድ ለማሳካት የቢዝነስ አሰራርን ቀላል ማድረግ፣ መሰረተ ልማት ማሟላት፣ ሰላም ማስፈንና የባንክ አገልግሎትን ማዘመን እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጠቆሙ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና፤ የውጭ ምንዛሪ ሪፎርሙ፣ ፕራይቬታይዜሽን መጀመሩ፣ የባንክ ሊበራላይዝድ መሆን እና የውጭ ባንኮች መምጣት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ሊስብ የሚችል መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ አስገባለሁ ላለው አምስት ቢሊዮን ዶላር እቅድ የመሰረተ ልማት ያለመሟላት ችግር፣ የትራንስፖርት እጥረት፣ የኃይል አቅርቦት እንዲሁም ቢሮክራሲው ቀልጣፋ ያለመሆን ተግዳሮት እንዳይሆኑ መፍትሄ እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በተለይም የቢዝነስ አሰራርን ቀላል ማድረግ፣ ቢሮክራሲውን ማቀላጠፍ፣መሰረተ ልማት ማሟላት፣ ሰላም ማስፈን እና የባንክ አገልግሎትን ማዘመን ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አመላክተዋል። በመንግሥት በኩል በኢኮኖሚ ሪፎርም የተወሰዱ ርምጃዎች ለውጭ ባለሀብቶች በጣም ጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በበኩላቸው፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበት እንዲጨምር የሚያደርጉ የተለመዱ መለከያዎች እንዳይዘጉ ማድረግና ክፍት መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሰላምና ደህንነት ጉዳይ የውጭ ባለሀብቶቹ እንደመለኪያ ከሚመለከቷቸው መካከል አንዱ መሆኑን በመጠቆም፤ ደህንነቱ አስተማማኝ ባልሆነበት ሀገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ይመጣል ተብሎ እንደማይታሰብም ያስረዳሉ።

ቢሮክራሲውም የሚያሰራ መሆን አለበት፣ የቢዝነስ አሰራርን ቀላል ማድረግ ያስፈልጋል። መንግሥት ከአንድ ባለሀብት እንዲሟሉ የሚፈልጋቸው ከታክስ አከፋፈል፣ በፍቃድ አሰጣጥ እና በእድሳት ቀላል መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በባንክ አሰራር የሚፈልጉት ነገር ካለም ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ባለሀብቶቹ ትክክለኛ ሀብት ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፣ ትንሽ ነገር አሳይተው የሀገርን ሀብት ወደውጭ እንዳያግዙ መጠንቀቅ ያስፈልጋልም ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው በፌዴራልና በክልሎች ከኢንቨስትመንት መሬት አቅርቦት አኳያ ያለውን ብልሹ አሠራር ማረም፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።

መንግሥት የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስትራቴጂን በመቅረጽ ኢኮኖሚውን ለውድድር ክፍት ለማድረግ እየሠራ ያለውን ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራ በማስተዋወቅ፤ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት በተለያዩ ዘርፎች ለመሳብ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአንድ መስኮት አገልግሎቶችን አጠናክሮ በስፋት በመስጠት፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማሳደግ እንደሚሰራም ማንሳታቸው ይታወሳል።

ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በ2016 ዓ.ም ሦስት ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ የተቻለ ሲሆን፤ ይህም የዕቅዱ 80 በመቶ ያህል መሆኑ ተጠቁሟል።

ዘላለም ግዛው

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You