«መንግሥት ባከናወናቸው የልማት ሥራዎች አዳዲስ ነገሮችን እየተመለከትን ነው» አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች

አዲስ አበባ፡- መንግሥት ባከናወናቸው በርካታ አመርቂ የልማት ሥራዎች በየቀኑ አዳዲስ ነገሮችን እየተመለከትን ነው ሲሉ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ሳምንትን በማስመልከት ሰሞኑን የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻዎችና በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የተሠሩ የልማት ሥራዎች ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችን አስጎብኝቷል።

የጉብኝቱ ተሳታፊ የሆኑት በኢትዮጵያ የዮርዳኖስ ኤምባሲ ቻርጅ ዲአፌር ኤማድ ማሳልሜህ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው በርካታ አመርቂ የልማት ሥራዎች በየቀኑ አዳዲስ ነገሮችን እየተመለከትን ነው፤ በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ በፈጣን ለውጥ ላይ ትገኛለች።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራርና አቅጣጫ ሰጭነት በመከናወን ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት አዲስ አበባ ከተማን ለመኖሪያ ምቹ እያደረጋት መሆኑን የገለጹት ኤማድ (ዶ/ር)፤ ከወራት በፊት የኮሪደር ልማቱ በተጀመረበት ወቅት እንደዚህ አይነት ፈጣን ለውጥና እድገት ይመጣል ብለው አለማሰባቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ ኤማድ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የዓድዋ ሙዚየም ዘመናዊቷን የኢትዮጵያ ታሪክ አጉልቶ የሚያሳይ ነው። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሊኮሩበት የሚገባ ስኬት ነው። በሙዚየሙ የሚገኙ እያንዳንዱ ቁሳቁሶች የኢትዮጵያውያንን ጀግንነትና ስልጣኔ የሚገልጹ ናቸው።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ልዩ ስሜት የሚያጎናጽፍ ነው ያሉት ኤማድ (ዶ/ር)፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየመጡ ያሉ ለውጦች ዜጎችን ከመጥቀም ባለፈ በቱሪስቶችም ተመራጭ እንድትሆን እያደረጋት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የጋና ኤምባሲ አማካሪ ኤሊኬም አሃዲዚ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ በመከናወን ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ማራኪ እና የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየረ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማ ደረጃ የተከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተሳካ ሁኔታ መፈጸማቸው የአመራሩን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ያሉት አማካሪው፤ ታሪካዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የተከፈለውን መስዋዕትነት በማጉላት የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አማካሪው ገለጻ፤ ከተማዋ የአፍሪካ መዲናነቷን የሚመጥን፣ ለነዋሪዎቿ የሚመች የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎቶችን እያዘመነች ነው። የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የከተማዋን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸው የዜጎችን ኑሮ ከመቀየር ባለፈ የከተማዋን ገጽታ ለመገንባት ወሳኝ ሚና አለው።

በመዲናዋ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ሥራዎች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትምህርት ሊሰጡ የሚችሉ መሆናቸውን የገለጹት አማካሪው፤ አፍሪካውያን አህጉሪቱን ለማሳደግ ሁሌም በአንድነት መቆም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You