በቅድመ ወሊድና ከወሊድ በኋላ የእናቶችን ጤና የሚያሻሽሉ ምርምሮች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፡- እናቶች በቅድመ ወሊድና ከወሊድ በኋላ ለሚገጥማቸውና ለሞት ለሚዳረጉበት የደም መፍሰስ ችግር መፍትሄ የሚሰጡ የተለያየ ምርምሮችን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይፋ አደረገ።

ጥናታዊ ጽሑፎቹን በውይይት ለማዳበር ታስቦ ሰሞኑን በተዘጋጀ መርሐ ግብር መክፈቻ ላይ የሥርዓተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አደራጀው መኮንን (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በኢንስቲትዩቱ የስብሰባ አዳራሽ ይፋ የሆኑት ጥናታዊ ጽሑፎች በተለያዩ አራት ተመራማሪዎች የተጠኑና በጤናው ዘርፍ ለውሳኔ ሰጪ አካላት ቀርበው ለውሳኔ አሠጣጥ የሚረዱ ናቸው።

ጥናታዊ ጽሑፎቹ በኢንስቲትዩቱ የሥርዓተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት መጠናታቸውን የጠቆሙት ዶክተር አደራጀው፤ የሀገራችንን የጤና ሥርዓት ለማሳደግና ለማበልፀግ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ንድፈ ሃሳቦችን ለውሳኔ ሰጪው አካል አዘጋጅቶ ማቅረብ መሆኑንም ገልፀዋል።

በእርግዝናና ወሊድ ወቅት እናቶችን ለሕልፈት በመዳረግ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው የጤና ህመሞች በመቀነሱ ረገድ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን የጠቀሱት ዶክተር አደራጀው፤ ሆኖም አሁንም የዓለም ጤና ድርጅት በ2030 ለመድረስ ካስቀመጠው ግብ አንፃር የሚፈለገውን ያህል አለመድረሱን ጠቁመዋል።

ጥናታዊ ጽሑፎቹ አራት መሆናቸውን አንስተው፤ ለውሳኔ ሰጪው አካል ደርሰው ሲተገበሩ የእናቶችን ሞት በከፍተኛ መጠን የሚቀንሱና የዓለም ጤና ድርጅት በ2030 ለመድረስ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከወሊድ በፊትና በኋላ የሚከሰት ከተገቢው መጠን ያለፈ የደም መፍሰስ፣ ውርጃ፣ ረዥም ምጥና የማህፀን መተርተር እናቶችን ለሞት ከሚዳርጉ ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውንም አስረድተው፤ ጥናታዊ ጽሑፎቹ ለነዚህ የእናቶች ጤና ችግሮች መፍትሄ በሚሆኑበት ዙሪያ በመርሐ ግብሩ ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉንና ገንቢ ግብዓቶች ማሰባሰብ መቻሉን ገልፀዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ደም መፍሰስን አስመልክተው ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ የዕውቀት ሽግግርና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ ፊርማዬ ቦጋለ በበኩላቸው፤ በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት በተለይም ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ደም መፍሰስ በአሁኑ ወቅት እናቶችን ለሕልፈት ከሚዳርጉ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ100 እናቶች ውስጥ ከአራት እስከ ስድስት የሚደርሱት ከወሊድ በኋላ በሚያጋጥም ለደም መፍሰስ አደጋ ሊጋለጡና ሕይወታቸውንም ሊያጡ ይችላሉ ያሉት ተመራማሪዋ ፤ በተደጋጋሚ ማርገዝ ፣ከአምስት በላይ ልጅ መውለድ፣ የልጁ የክብደት መጠን፣ የእንግዴ ልጅ ቅሪት በማህፀን ውስጥ መቅረት እናቶችን ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት የደም መፍሰስ የሚያጋለጡ እንደሆኑም አመልክተዋል።

ጥናታዊ ጽሑፎቹ የእናቶች የጤና ችግር ለመቀነስ በዓለም የጤና ድርጅትና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራባቸው ያሉ ወጥ ተግባራት ላይ ተደማሪ መፍትሄ የሚያመጣ መሆኑንም ገልፀዋል።

የፖሊሲ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሁለት መፍትሄዎችን በጥናቶቹ ላይ መስፈራቸውን የጠቀሱት ተመራማሪዋ ፊርማዬ፤ የመጀመሪያው የጤና ሥርዓቱ በአግባቡ እየተሰራ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን በመለየት እናቶች ለቅድመ ወሊድ ክትትል በሚሄዱበት ሰዓት የሚታዩበትን አግባብ የዓለም ጤና ድርጅት በሚያዘው መሰረት የተለያዩ መረጃዎችን ተጠቅሞ የበለጠ ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል። በተጨማሪ በእርግዝና ወቅት የደም ግፊት መታወክን ለመቀነስ የሚረዱ መፍትሄዎች መቀመጣቸውን አስረድተዋል። ጥናቶቹ የእናቶች ሞት አሁን ካለበት ስምንት ሺ 321 ወደ አምስት ሺህ መቀነስ ያስችላል ሲሉ አመላክተዋል።

በመድረኩ የእናቶችን ህይወት ለመታደግ የሚረዱ ስልቶች እና መንገዶች የሚጠቁም፤የማህጸን በር ካንሰር ምርመራን በማሻሻል ሞትን መቀነስ የሚያስችሉ፤ በመኪና አደጋ የሚጎዱ ወገኖች ወደ ጤና ማዕከላት ከመድረሳቸው በፊት መደረግ ያለበትን የሚያመላክቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በውይይት ዳብረዋል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You