አዲስ አበባ፡- ሁለቱም አካላት ወደ ድርድርና ውይይት እንዲመጡ የማቀራረብ ጥረቶች ቀጥለዋል ሲል የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል አስታወቀ።
የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ሰብሳቢ አቶ ያየህይራድ በለጠ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ በአራቱም ቀጣናዎች ላይ ሁለቱን አካላት ወደ ድርድርና ውይይት እንዲመጡ የማቀራረብ ጥረቶች ቀጥለዋል።
የሰላም ካውንስሉ ሁለቱ አካላት ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ የማቀራረብ ሥራ እየሠራ ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ ሁለቱም ወገኖች ወደ ድርድርና ውይይት እንዲመጡ የማቀራረብ ሥራ የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።
የድርድር ጥሪውን መንግሥት የተቀበለ በመሆኑ ፋኖዎች እንዲቀበሉ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በፋኖዎች በኩል አስፈላጊነቱን ማመን፣ የመመካከር፣ በውስጣቸው ያለውን ልዩነት ወደ አንድነት ማምጣት፣ የሕዝቡንም ችግር በመመልከት የመፍትሄ ሃሳቡ ውይይትና ንግግር መሆኑን በመረዳት ወደ ውይይት መምጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የካውንስሉ ገለልተኛነት ችግሮችን በጦርነት ሳይሆን በድርድር፣ በውይይትና በንግግር ሊፈቱ ይገባል የሚል ሃሳብ የያዘ መሆኑን የገለጹት አቶ ያየህይራድ፤ ሁሉቱም አካላት በየትኛውም ቦታ፣ ሀገር፣ የፈለጉትን አደራዳሪ እና ጥያቄዎችን አቅርበው እንዲወያዩና እንዲደራደሩ የሚያቀራርብ ነው ብለዋል።
ካውንስሉ በገለልተኝነት ሁለቱንም አካላት እንዲወያዩ፣ እንዲደራደሩ ግጭት እንዲቆምና ወደ ሰላም መመለስ እንዲቻል እየጠየቀ መሆኑን በመግለጽ፤ መደራደር በራሱ የስልጣኔ ምልክት መሆኑንና ግጭቱ የፈጠረውን ማህበራዊ ቀውስ በማየት ችግሮችን በድርድር፣ በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት የሰላም ካውንስሉን ጥሪ ተቀብሎ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑንና በፌዴራል መንግሥት በኩልም በተለያዩ አጋጣሚዎች መገለጹን ጠቅሰው፤ ሌላኛውም ወገን የድርድርና ውይይት ጥሪውን በመቀበል መግለጫ ማውጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የሰላም ካውንስሉ ሁለቱንም ወገኖች ተደራደሩ የሚል አቀራራቢ ሃሳብ ይዞ የመጣ ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ ካውንስሉ ሕዝብ የሰጠውን አደራ ወደ ዳር ለማድረስ እየሠራ በመሆኑ ህብረተሰቡም መደገፍ አለበት ብለዋል።
የማቀራረቡን ሥራ ለሰላም ካውንስሉ ብቻ ተሰጥቶ ጠያቂና ተጠያቂ መሆን እንደሌለበት ጠቅሰው፤ ችግሮችን በውይይት መፍታት የሚለው ሃሳብ ሕዝባዊ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ተጽዕኖና ጫና እንዲፈጥር ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ፤ ድርድርን እንደ አጀንዳ ማንሳትና መወያየት አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም የችግር መፍቻ ንግግር መሆኑን ማመን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የሲቪክ፣ የሙያ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የሴቶች፣ የወጣቶች አደረጃጀቶች፣ የፖለቲካ ምክር ቤቶች ሰላም ካውንስሉ ያቀረባቸውን የድርድር፣ የውይይትና የሰላም አማራጮችን ሊደግፉ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ሰላም እንዲመጣ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግና ሁሉም ሰው ወደ ውይይትና ድርድር እንዲመጣ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም