የታዳጊዎችን ስብዕና ለመታደግ

ዜና ትንታኔ

እ.አ.አ በወርሃ መስከረም 2016 ነበር ባይትዳንስ በተሰኘው የቻይናው ቴክኖሎጂ ካምፓኒ ለአገልግሎት የበቃው። ቲክቶክ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ቢሊዮን ወርሃዊ ንቁ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ወርሃዊ ተጠቃሚዎች እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ።

ቲክቶክን የፈጠረችው ቻይና ብትሆንም ለሌሎች ሀገራት የምታሰራጨውና የራሷ ዜጎች የሚጠቀሙት የቲክቶክ መተግበሪያ ይለያያል። ቻይናውያን የሚጠቀሙት መተግበሪያ በእጅጉ ቁጥጥር የሚደረግበትና ለመማሪያነት እንዲያገለግል ብቻ ተደርጎ የተሰናዳ ነው። አፍጋኒስታን፣ ህንድ፣ ኢራን፣ ኪርጊስታን፣ ኔፓል እና ሶማሊያ በቲክቶክ ላይ ሙሉ እገዳ የጣሉ ሀገራት ናቸው።

የቲክቶክ ማኅበራዊ ትስስር አጠቃቀም ዝንባሌ በጨመረበት በአሁኑ ወቅት ወላጆች ልጆቻቸውን ቪዲዮ እየቀረጹ መልቀቅ፣ ፎቶ እያነሱ ማጋራት እና ቤተሰባዊ መረጃዎችን መጻፍ በስፋት እየተስተዋለ ያለ ተግባር ነው።

ለመሆኑ ቲክቶክ በማህበረሰቡ አኗኗርና በልጆች አስተዳደግ ላይ እያስከተለ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ እንዴት ይታያል? እንዴትስ መከላከል ይቻላል?

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሰለሞን ሙሉ እንደሚናገሩት፤ ቲክቶክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣ ማህበራዊ ሚዲያ ሲሆን፤ የራሱ ጥቅምና ጉዳቶች አሉት። ዜጎች ያላቸው የሚዲያ እውቀት ወይም ግንዛቤ የተለያያ በመሆኑ የእያንዳንዱን የማህበራዊ ሚዲያ አሰራር ካለመረዳት ተጠቃሚዎች አሉታዊ ተጽእኖ ውስጥ ሲወድቁ ይስተዋላል። ነገር ግን አጠቃቀሙን የቻሉበት ዜጎች እጅጉን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

አብዛኛው የቲክቶክ ተጠቃሚ እስክሮል እያደረገ የተለያዩ ይዘቶችን ይከታተላል። ይህም ባህልን የመልቀቅ፣ ማንነትን የመርሳትና የማንነት ቀውስ (identity cri­ses) ውስጥ ያስገባል። በዚህም የራስን ባህል በመበረዝ የሌሎችን ባህልና እሳቤ እንድንከተል ያደርገናል የሚሉት መምህሩ፤ ከዚህ አለፍ ሲልም ዜጎች ኢትዮጵያዊ ማንነትን በመርሳት የሌሎችን ናፋቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ ቀለል ተደርጎ መታየት የለበትም ባይ ናቸው።

እንደ መምህር ሰለሞን ገለጻ፤ ቲክቶክን በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ይመለከቱታል። ከወጣቶች በተጨማሪም በእድሜ ገፋ ያሉ አዛውንቶችም ጭምር ያልተገቡ ይዘቶችን በቲክቶክ ሲያሰራጩ ይስተዋላል፤ ታዳጊዎችን መምከርና መለወጥ ያለባቸው እነኝህ ዜጎች በዚህ ባልተገባ ተግባር ላይ ሲሳተፉ ማየት የተለመደ ቢሆንም እጅጉን የሚያሳዝን ነው።

ወጣቶች በተለይም ቲክቶክ ላይ በማዘውተር የትምህርት ወይም የስራ ጊዜያቸውን ትርጉም በሌለው ጉዳይ ላይ ማሳለፋቸው በሁለንተናዊ የህይወት እንቅስቃሴያቸው ላይ ጫና በማሳደር ለድብርትና ለማይጨበጥ ምኞት ይዳርጋቸዋል። በዚህም ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚመለከቱት ብልጭልጭ ይዘት እየሳባቸው ስብዕናቸው እየወረደ የሀገራቸው ጉዳይ የማያሳስባቸው እየሆኑ መጥተዋል ነው የሚሉት መምህር ሰለሞን።

ህጻናትም እንዲሁ በደካማ ወላጆች አማካኝነት ቲክቶክን አዘውትረው እየተመለከቱ መሆኑንና በቲክቶክ ላይ የሚለቀቀው ይዘትም አብዛኛው ለህጻናት የሚመከር እንዳልሆነ የሚገልጹት መምህር ሰለሞን፤ ተማሩ የሚባሉ ወላጆችም ሳይቀሩ ስማርት ስልክ ለልጆቻቸው በመስጠት ልቅ የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚነትን እያበረታቱ መሆናቸውን ያነሳሉ።

ዜጎች ቲክቶክንም ሆነ ሌሎችን የማህበራዊ ሚዲያዎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ስለእያንዳንዱ የማህበራዊ ሚዲያ አይነት፣ አሰራርና ስለቢዝነስ ሞዴላቸው እንዲረዱ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህም የሚዲያና የመረጃ አጠቃቀም ስልጠናዎችን ለዜጎች በመስጠት የሚያደርሰውን ተጽእኖ መቀነስ ይቻላል ሲሉም ያክላሉ።

ማህበራዊ ሚዲያ በወጣቶችና በህጻናት ላይ እያደረሰ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ወላጆች ህጻናት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ እንዲቀንሱ በማድረግ በትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው መምህር ሰለሞን ይመክራሉ።

የስነልቦና ባለሙያና የህይወት ክህሎት አሰልጣኝ ሲሳይ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ቲክቶክ ማለት ጥልቅ ያልሆነ ቁንጽል ወይም አጫጭር ሃሳቦች የሚዘዋወሩበት የማህበራዊ ሚዲያ አይነት ነው። ይህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍ በባህሪው ትናንሽና አጫጭር መረጃዎች የሚዘዋወሩበት በመሆኑ ተጠቃሚዎቹ በሚመለከቱት ጉዳይ ላይ የጠለቀ እውቀት እንዲኖራቸው የማያደርግ መሆኑን ይናገራሉ።

ቲክቶክ የራሱ ጥቅሞች ቢኖሩትም ጉዳቱ ያመዝናል። በዚህም ተጠቃሚዎች ለሰከንዶች ብቻ ሃሳባቸውን ሰብስበው የሚያዩት በመሆኑ ጥልቅ ማንነት በማሳጣት ወደቁንጽል እሳቤ ያመጣቸዋል የሚሉት የስነልቦና ባለሙያ፤ በተለይም በታዳጊዎች የዛሬም ሆነ የነገ ህይወት ላይ አሉታዊ ጫና በማሳደር በጉዳዮች ላይ የጠለቀ አተያይና አስተሳሰብ እንዳይኖራቸው እንደሚያደርግ ይገልጻሉ።

አቶ ሲሳይ እንደሚናገሩት ቲክቶክ ተጠቃሚዎችን ወደአንድ መዳረሻ የማይወስድ፣ ተከታታይነትና አድራሻ የሌለው መረጃ የሚሰራጭበት ነው። መተግበሪያው ታዳጊዎች ችግሮችን የመቋቋም ጥበብ እንዳይኖራቸው በማድረግ ለተለያዩ ጉዳቶች እየዳረጋቸው በመሆኑ ወላጆች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።

ቲክቶክ በታዳጊዎች ላይ የጥድፍያ ህይወት፣ ትዕግስት የሌለውና ችኮላ የበዛበት ማንነትን ይፈጥራል። በዚህም ከራሳቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች መግባባት የሚሳናቸው እንዲሆኑ ያደርጋል። በትምህርታቸውም ቢሆን ረጅም የትምህርት ክፍለ ጊዜን ታግሰው መማርም ሆነ ማጥናት እንዳይችሉ የማድረግ አቅም አለው ነው የሚሉት የስነልቦና ባለሙያው።

በርካታ ችግሮች ባሉባቸው እና በነገሮች ላይ መመራመርና ጠንክሮ መስራት አስፈላጊ በሆነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ላይ ልቅ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እንደማይመከር የሚያነሱት አቶ ሲሳይ፤ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጥናት በማድረግ በቲክቶክ ላይ እርምጃ ከወሰዱ ሀገራት ልምዶችን በመቅሰም ነገሮች ወደከፋ ሁኔታ ሳይቀየሩ ወደመፍትሄ መሄድ እንደሚገባው አመላክተዋል።

እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ትውልዱን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ተከታዮቻቸውን የማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማስተማር ይኖርባቸዋል። ወላጆችም ከልጆቻቸው ጋር በቅርበት በመነጋገር ለልጆቻቸው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ገደብ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም መክረዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You