ሩሲያ በድጋሚ ከዩክሬን ሰፊ ግዛት መያዟ ተገለጸ

ሩሲያ ባለፈው ሳምንት 196 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ያለው የዩክሬን መሬት መያዟ ተገለጸ። የሩሲያ ኃይሎች ወደ ፊት መግፋት ሩሲያ በሰው ኃይል እና በጦር መሳሪያ ያላትን የኃይል የበላይነት የሚያሳይ መሆኑም ተመላክቷል።

ፈጣን ግስጋሴ እያደረገች ያለችው ሩሲያ ባለፈው ሳምንት እ.ኤ.አ ከጥቅምት 20 እስከ 27 196 ነጥብ አንድ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የዩክሬን መሬት መያዟን ሮይተርስ የዩክሬንን ኦፕን ሶርስ ካርታ የሚተነትነውን የሩሲያ ሚዲያ ቡድን ኤጄንትስትቮን ጠቅሶ ገልጿል።

ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የዩክሬን ጦርነት የሩሲያ ኃይሎች እጅግ አደገኛ ወደሚሉት ዙር ገብቷል። የሩሲያ ኃይሎች በፍጥነት እየገፉ ሲሆን፤ ምዕራባውያን ጦርነቱን እንዴት ይቁም በሚለው ጉዳይ መግባባት ላይ አልደረሱም።

ዩክሬን የሩሲያን ኩርስ ግዛት የወሰነ ክፍል መያዝ ብትችልም የሩሲያ ወታደሮች በበኩላቸው ካለፈው የመስከረም ወር አንስቶ በፍጥነት ወደፊት መግፋታቸው ተመላክቷል።

“የሩሲያ ኃይሎች ቢያንስ ይህ ዓመት ከገባ ወዲህ እንዲህ አይነት ፈጣን ሳምንታዊ ግስጋሴ አድርገው አያውቁም” ሲል በሩሲያውያን “የውጭ ኤጀንት” ተብሎ የሚጠራው ኤጄንትስትቮ በቴሌግራም ቻናሉ መግለጹን ዘገባው ጠቅሷል።

ኤጀንትስትቮ እንደገለጸው፤ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው የዩክሬንን ‘ዲፕ ስቴት ኦፕን ሶርስ ኢንተለጀንስ’ ተንታኞችን መረጃ መሰረት በማድረግ ነው።

ባለፈው ሳምንታት የሩሲያ ኃይሎች በቩሌዳር ከተማ አቅራቢያ 95 ኪሎ ሜትር ስኩዌር እና በፖክሮቭስክ ከተማ ደግሞ 63 ኪሎ ሜትር ስኩዌር መሬት ተቆጣጥረዋል። ሁለቱም በምስራቅ ዩክሬን በሚገኘው የዶምባስ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

በዶምባስ ግዛት ያለው የዩክሬን ኃይል ኪቭ ወታደሮችን ወደሩሲያ ኩርስክ ግዛት በመላኳ ምክንያት እና ሩሲያ ወታደሮቿን ከዶምባስ ወደ ኩርስክ ባለመላኳ ምክንያት ደክሟል።

ግማሽ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት የተቆጣጠሩት የሩሲያ ኃይሎች ወደ ፊት መግፋት፣ ሩሲያ በሰው ኃይል እና በጦር መሳሪያ ያላትን የኃይል የበላይነት የሚያሳይ ነው ተብሏል።

ዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮቿ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ እንዲያስታጥቋት እና በረጅም ርቀት ሚሳይል ሩሲያ ውስጥ ዘልቃ ጥቃት እንድትፈጽም እንዲፈቅዱላት እየተማጸነች ነው።

ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን በከፊል የያዘቻቸውን አራት የምስራቅ እና የደቡብ ዩክሬን ግዛቶችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ትፈልጋለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You