በወባ ዜጎቿን የማትነጠቅ ኢትዮጵያን ለመፍጠር

የወባ በሽታ ዛሬም ድረስ በዓለማችን ላይ ለሰው ልጆች ጤና ጠንቅና ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው። በየዓመቱ በአማካኝ ከ200 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወረርሽኙ እንደሚያዙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከእነዚህ ውስጥ በበሽታው ሕይወታቸው ከሚቀጠፉት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው።

እኤአ በ2022 የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዓለም ላይ 608 ሺህ ሰዎች በወባ በሽታ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። በዚሁ ዓመት 249 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል። በበሽታው ከተያዙት ከእነዚህ ሰዎች መካከል 94 በመቶ የሚሆነውን የያዘችው አህጉራችን አፍሪካ ነች።

ቀደም ባሉት ዘመናት አሜሪካ ጭምሮ የሰለጠኑት ሀገራት በወባ የተፈተኑ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወረርሽኙ የህብረተሰብ የጤና ችግር ከማይሆንበት ደረጃ አድርሰውታል። ከአፍሪካ ሀገራትም አልጄሪያና ሞሪሺየስን ጨምሮ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ወባን ከሀገራቸው ማስወገድ ችለዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የወባ በሽታ በአሁኑ ጊዜ የሚገኘው ትሮፒካል በሚባሉ አካባቢዎች በተለይም በአፍሪካ፣ በተወሰኑ የኤሺያ ሀገራት እና በደቡብ አሜሪካ ብቻ ነው። በበሽታው በየቀኑም አንድ ሺህ ሕፃናት ይሞታሉ። ናይጄሪያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኡጋንዳና ሞዛምቢክ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ጨቅላ ሕፃናት፣ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ስደተኞችና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በብዛት ለበሽታው ተጋላጭ እንደሚሆኑም ይነገራል። የግንዛቤ እጥረት፣ የአጎበር ሥርጭት አለመኖር፣ የኬሚካል ርጭት አለማከናወንና መሰል ችግሮች ለብዙዎች በበሽታው መያዝ መንስኤ ሆነው የሚጠቀሱ ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው ፤ ኢትዮጵያ በሽታው በብዛት ከሚከሰትባቸው 15 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ትገኛለች። 75 በመቶ ያህሉ የቆዳ ስፋቷ ለወባ በሽታ ሥርጭት አመቺ ነው። 69 በመቶ ያህሉ የሀገሪቱ ነዋሪም ለወባ በሽታ ተጋላጭ ነው።

በኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች በጣም ጥሩ የሚባሉ ወባን የመቆጣጠር ሥራዎች ተከናውነው ጫናው የመቀነስ አዝማሚያ ቢታይም ፤ አሁንም በበሽታው በርከት ያሉ ሰዎች ይያዛሉ። በተለይ በቅርብ ዓመታት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መበራከቱን መረጃዎች ያሳያሉ። ችግሩ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የጤና ችግር እየሆነ መምጣቱም እየተስተዋለ ነው።

በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የወባ በሽታ ሥርጭት እየተስፋፋ ብዙዎችን ከአልጋ እያዋለ ነው። ባለፈው ዓመት በዘጠኝ ወራት ብቻ ምርመራ ካደረጉ 10 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮኑ ወባ በደማቸው ውስጥ መገኘቱን ሪፖርት ተደርጓል። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ 222 ወረዳዎች የበሽታው ሥርጭት በስፋት እንደተስተዋለ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር አሳውቋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለወባ መራባት አመቺ ሁኔታ መፈጠሩን ጨምሮ ለሥርጭቱ መባባስ የሚነሱ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ በማህበረሰቡና በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ዘንድ የተፈጠረው መዘናጋት፣ የወባ በሽታ ባህሪያት ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀያየር፣ የወባ መድኃኒት እንደልብ አለመገኘት እንዲሁም በተለያዩ ምክንያት ቀድሞ በነፃ ይታደል የነበረው ኬሚካል የተነከረ አጎበር በግዢ እንኳን አለመገኘቱ ተጠቃሽ ምክንያት ነው።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የዝናብ መቆራረጥ፣ ከመስኖ ልማት ጋር በተያያዘ በየአካባቢው ያቆረ ውሃ መኖር ከአሁን በፊት በተሰሩ ሥራዎች ወባ ሲቀንስ ጠፍቷል በሚል መዘናጋት መኖሩ ለመጨመሩ ሌሎች የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው። ይህ እንደ አጠቃላይ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቱ በሚገባው ልክ አለመዘመኑ፣ ዘላቂ የመከላከልና የመቆጣጠር ርምጃ ባለመወሰዱ ምክንያት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉን በመጥቀስ የሚሞግቱ አሉ።

ወረርሽኙ በተለይ የበልግ ዝናብን ተከትሎ ከሚያዝያ እስከ ታኅሣሥ ባሉት ወራት በስፋት ይከሰታል። ነገር ግን የባለፈው ክረምት መግቢያ አንስቶ አሁን ባለንበት ወቅትም የወባ ሥርጭቱ እየታየ እንደሆነ እየተመለከትን ነው። የጤና ሚኒስቴርም ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍ የጥናት እና የምርምር ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ ነግሮናል። በተለይ የወባ በሽታ ሥርጭትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የሶስት ዓመት እቅድም ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ከገለጸ ሰንበትበት ብሏል። ያም ሆኖ ግን ችግሩ ማህበረሰቡ ውስጥ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በበቂ ሁኔታ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ተግባራት አፋጣኝ መፍትሔ እያሳዩ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም።

በርግጥ የወባን ወረርሽኝ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራን በተመለከተ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት የሚጠቀሱ ሥራዎችን ሰርተዋል። በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሁለቱ ተቋማት የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ቅንጅታዊ ሥራ ሕብረተሰቡ ስለ ወባ መከላከያና የማጥፊያ መንገዶች ያለውን የግንዛቤ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦትና የሕብረተሰብ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ሰጥተዋል። በዚህም የወባን መከላከያ እና መቆጣጠሪያ መንገዶችን በዝርዝር ለመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች አቅርበው ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥሩም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የቁጥጥርና መከላከል ሥራው ጠንካራ በመሆኑ በኢትዮጵያ የወባ ሥርጭት ዝቅተኛ ነበር። ይሁንና የማህበረሰብ የመከላከል ሥራው ላይ መዘናጋት በተለይ ለወባ መከላከል ሥራ የሚያግዙ ግብዓቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ከአየር ንብረት ለውጥ ቀጥሎ ለወባ ሥርጭት በድጋሚ ማገርሸት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የወባ ጫና ከፍ ብሎ ታይቷል። በነዚሁ መነሻነትም የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ለወባ ተጋላጭ የሆኑ 220 ወረዳዎች ለይተው በ10 ክልሎች ውስጥ ጠንካራ የምልከታ፣ ክትትልና ቅኝት ሥራዎች መሥራታቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተው ተመልክተናል። ይኸው ሥራ አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል። ቀደም ተብሎ የተወሰደው ርምጃ በበሽታው ይደርስ የነበረውን የከፋ ጥፋት ማስቀረት የሚችል ነው። አሁንም በተመሳሳይ የቅድመ መከላከል ሥራው ላይ በማተኮር የወባ ወረርሽኝ እስከወዲያኛው ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ማድረስ ይገባል።

በየክልሉ የሚታዩ የወባ ሥርጭትን ለመቆጣጠር እየተሰሩ ያሉ የቅንጅት ሥራዎች እና ጥረቶች ሥርጭቱን ከመቀነስ ረገድ መሻሻሎች ቢኖሩም በአንዳንድ ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች ሥርጭቱን ትርጉም ባለው ደረጃ ለመቀነስ ተጨማሪ እና የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይጠቅባቸዋል። ሕብረተሰቡን በማሳተፍ እና ባለቤት በማድረግ መሥራት ያስፈልጋል። በቀጣይም የወባ በሽታ ሥርጭት እና ጫና በሚጨምርባቸው ወራት ተገቢው የመከላከል፣ የቅድመ ዝግጅት፣ ቅኝትና ምላሽ ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል።

ወቅት እየጠበቀ የሚከሰተው የወባ ወረርሽኝ በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች የማንሰራራት ሁኔታዎች እየታዩ እና ዜጎች በችግሩ ተጋላጭ በመሆናቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሥራዎችን መሥራት እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለይም የሚዲያ አካላት ሕብረተሰቡን የመከላከያ እና የመቆጣጠሪያ መንገዶቹን በማስተማርና ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። መንግሥትና የግል ተራዕዶ ድርጅቶች ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር ማህበረሰቡ የራሱ ጤና ዘብ ሊሆን ይገባል። የዚህ ድምር ውጤት ወባ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሁለንተናዊ የጤና ችግሮች ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ላይ ለማስቀመጥ ያግዛል።

የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ሥራ ላይ የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ እና ህብረተሰቡ የራሱን ጤና መጠበቅ እንዲችል የማስተማር እና የንቅናቄ ተግባራት ላይ እንዲሳተፍ ለማድረግ የመገናኛ ብዙኀንና ሕዝብ ግንኙነት የጤና ኮሙኒኬሽን ሥራዎችን አሁንም በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። አብዛኛውን ማህበረሰብ መድረስ የሚቻለው ተፅእኖ መፍጠር በሚችሉ መገናኛ ብዙኀን አማካኝነት ነው። የማህበራዊ ሚዲያውንም መጠቀም ያስፈልጋል።

የበሽታውን ሥርጭት ከመግታት እና ከመከላከል አንጻር የግብዓት አቅርቦትን፣ የአልጋ አጎበር፣ የወባ መከላከያ ኬሚካል የቤት ለቤት ርጭትን ማሻሻል እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና የጤና ኬላ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማጠናከርና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል።

ችግሩ የተረሳ፣ የተዘነጋ ጉዳይ እንዳይሆን ጊዜው ሳይረፍድና ብዙዎችን ሳንነጠቅ በርብርብ መነሳት ይገባል። ለዚህም መንግሥትን ጀምሮ ሁሉም የማህበረሰብ አንቂዎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በፊት የተለያዩ መገናኛ ብዙኅንን በመጠቀም ይተላለፉ የነበሩ የጥንቃቄ፣ የግንዛቤ መልእክቶች በስፋት መቀጠል አለባቸው። ሰዎች እንዳይጎዱ ስለበሽታው ጎጂነት መንገር፣ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መንገዶችን ማሳየትም ይገባል። በቀላሉ በሚደረጉ የጥንቃቄ መንገዶች ሰዎችን ማትረፍ እንችላለንና። በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሲኖሩም በአፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል።

የወባ በሽታን ቀድመን መከላከል ይኖርብናል፤ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው መከላከሉ ላይ አበክረን ስንሰራ ነው። ይህ ውጤት የማያስገኝ ከሆነና መከላከል ካልቻልን፣ ወረርሽኙን መቆጣጠርና ለሰዎችም አለሁ ማለት አለብን። በየአካባቢው ያሉ ለወባ ትንኝ መራባት መንስኤ የሆኑትን በውሃ የታቆሩ ቦታዎችን በማስወገድ ነዋሪው የራሱን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የሚመለከታቸው አካላትም ለወባ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ላይ ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ፣ የኬሚካል ርጭት በማከናወን፣ የአጎበር ሥርጭትንም በማዳረስ የሰዎችን ሕይወት መታደግ ይጠበቅባቸዋል።

ችግሩ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ አስቸኳይ የቅድመ መከላከል ሥራዎች መሰራት ተገቢና አስፈላጊ ነው። ዓለማችን ከጥቂት ዓመታት በፊት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሚሊዮኖችን አጥታለች። ይሁን እንጂ ሁሉም ለወረርሽኙ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አሁን ስጋትነቱ አብቅቷል። በሰው ልጅ ታሪክ አስከፊ ከሚባሉ ግዜያት እንደ አንዱ የሚቆጠረው የኮቪድ ወረርሽኝ የተከሰተበት ጊዜ መሰል ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ሁሉም ትምህርት ወስዷል። በመሆኑም መንግሥትም ይሁን ማህበረሰባችን ቀደም ካሉት አስቸጋሪ ወቅቶች የወሰደውን ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ ዳግም የዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ጥንቃቄ መውሰድ ይጠበቅበታል። በተለይ ወባን ሙሉ በሙሉ ከሀገሪቱ ለማጥፋት የተጀመረው ሥራ ሊጠናከርና በወረርሽኙ ዜጎቿን የማትቀብር ኢትዮጵያን መፍጠር ይገባል። ለዚህ ደግሞ የባለድርሻ አካላት ያልተቆጠበ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ሰላም!

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You