የዓባይ ወንዝ የአስራ አንዱ የተፋሰሱ ሀገሮች ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የጋራ ሀብት እንደሆነ፤ እያንዳንዱ ሀገርም በፍትሀዊነት እና በኃላፊነት በወንዙ ውሃ የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይታመናል።
እ.ኤ.አ. በ1929 እና 1959 የተደረጉ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች የተፋሰሱን ሀገራት በወንዙ ውሃ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት በማገድ ግብፅ እና ሱዳን የወንዙን ውሀ በበላይነት እንዲጠቀሙበት ያልተገባ መብት አጎናጽፏቸው ቆይቷል። ይህንኑ ስምምነት ታሳቢ ባደረገ መልኩም ሀገራቱ በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ የበላይነትን ለማስፈን ረጅም ርቀቶችን ተጉዘዋል ፡፡
ይህንን ያልተገባ አካሄድ ለመለወጥ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የወንዙን ውሃ በፍትሀዊነት እና በኃላፊነት መጠቀም የሚያስችል አዲስ የስምምነት እና የትብብር ማሕቀፍ ለመፍጠር ላለፉት አስር ዓመታት ሰፊ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በቅርቡም የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ጸድቆ ወደ ትግበራ ገብቷል።
የማሕቀፉ ወደ ስራ መግባት የወንዙን የውሃ በፍትሃዊነት ለማስተዳደር መሰረት የሚጥል፤ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ያለውን ውስብስብ እና አሁንም ድረስ አከራካሪ ሆኖ የቀጠለውን የውሃ ተጠቃሚነት ችግር ለመፍታት የሚያስችል ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰሱን ሀገራት ባገለለ መንገድ የተካሄዱ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች የአሁኑን ዘመን የሚመጥኑ አይደሉም። ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ለግብፅ እና ለሱዳን ያልተገባ መብት የሚያጎናጽፉ እና የተፈሰሱን ሀገራት ፍትሀዊ በሆነ መንገድ በወንዙ የመጠቀም መብት የሚገድቡ ናቸው፡፡
ስምምነቶቹ ሲፈረሙ የሀገራቱ ሕዝቦች አስከፊ በነበረው በየቅኝ ገዥዎች ቀንበር ስር መከራ እያዩ ከመሆናቸው አኳያ ስምምነቶች በርግጥ የታችኛውን የተፋሰሱን ሀገራት ለመጥቀም ታስቦ ስለመሆኑ አፍን ሞልቶ መናገር፤ በስማቸው ከመነገድ ያለፈ ፋይዳ ነበረው ማለትም አይቻልም።
የትብብር ማሕቀፉ ይህንን ለቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብ የተገዛ እና የአፍሪካውያንን አብሮ ተቻችሎ እና ተስማምቶ ለጋራ እጣ ፈንታ የመኖር እሴቶች ያደበዘዘን ስምምነት በመሻር ፤አዲስ የትብብር ምእራፍ መፍጠር የሚያስችል ነው።
የተፋሰሱ ሀገራት በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የጋራ መረዳት እና ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው የሚረዳ፣ ሀገራቱ ሉዓላዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ እና ወንዙን በጋራ እንዲያለሙ የሚያስችሉ የሕግ ማሕቀፎችን የሚያካተተ ነው።
የወንዙን ዘላቂ ልማትና አስተዳደር ለማረጋገጥ በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ሊኖር ስለሚገባው ትብብር አጽንኦት የሰጠ፤ በተለይም ከ85 በመቶ በላይ የወንዙ ውሃ ባለድርሻ የሆነችው ኢትዮጵያ ተገቢነት ባለው መልኩ የወንዙ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ሕጋዊ መብት የሚያጎናጽፏት ነው ።
የልማት እና የትብብር በረከትን ይዞ የመጣው የትብብር ማሕቀፉ፤ ገና ከጅምሩ ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳ በሚጋሩት ላምዎ በሚገኘው እና የናይል ገባር በሆነው ሊሙር ወንዝ ላይ ለመስኖ እና መጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚውሉ የሁለት ግድቦች ግንባታ መጀመር የሚያስችላቸውን አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል ፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ሁሉም አካላት በጋራ የሚጠቀሙበት የትብብር መድረክ እንዲኖር ስትንቀሳቀስ የቆየችባቸውን ዓመታት ወደ ውጤታማነት የቀየረ ነው፡፡ ማሕቀፉ መሬት ላይ ወርዶ ወደ ተግባር መለወጡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወንዙን ሳይጠቀሙ ለረጅም ዘመናት ለኖሩት የተፋሰሱ ሀገራት ትልቅ የምስራች ተደርጎ የሚወሰድ፤ በቀጣይም በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ተመሳሳይ ስትራቴጂክ የትብብር መድረክ መፍጠር የሚያስችል ነው።
ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ለመጣው የኃይል ፍላጎቷ ሆነ ለግብርና ልማት ስራዎቿ የማሕቀፉ ወደ ትግበራ መግባት ፣ በፍትሀዊነት እና በኃላፊነት የወንዙን ውሃ ለመጠቀም የሚያስችላት ነው። ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በትብብር ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት እንድታቅድ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው።
በቅኝ ግዛት ውሎች ላይ የሙጥኝ ያለችው ግብፅ እንዲሁም እሷን ተከትላ ወጥ አቋም መያዝ የተሳናት ሱዳን ስምምነቱ በተፋሰሱ ሀገራት በአብላጫ መጽደቁ ፤በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ላይ ያላቸውን ጊዜ ያለፈበት አቋም እንዲያስተካክሉ የተሻለ እድል የሚሰጣቸው ነው ፡፡
ኢትዮጵያ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በሚመለከት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማክበር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየችበት ይህ ትብብር፤ ከውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በመተማመን እና በትብብር እንዲፈቱ ያደርጋል፡፡
ሀገራችን ከጎረቤቶቿ እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በመሆን ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ተግዳሮቶችን በአንድነት በመፍታት የጋራ እድገትን እውን ለማድረግ ያላትን ፍላጎትን በማሳየት ረገድም ትልቅ ድርሻ አለው።
እስካሁን ድረስ ማሕቀፉ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት በመፍጠር እኔ ብቻ የውሃ ተጠቃሚነት ይኑረኝ በሚል የተፋሰሱ ሀገራት ስምምነት እንዳይኖራቸው ሴራዎችን ስትጠነስስ ለኖረችው ግብጽም ሃያ አንደኛው ዘመንን የሚመጥን ፍትሃዊ እና የእኩል ተጠቃሚነት መርህን መተግበር የውዴታ ግዴታ መሆኑን እንድትረዳ የሚያግዛት ነው ፡፡
የተፋሰሱ ሀገራት ትልቅ ድል የሆነውን ይሄን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ወደ መሬት ወርዶ ተፈጻሚ እንዲሆን ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ጥረት የሚያስፈልግ በመሆኑ፤ በተለይም በወንዙ ውሃ ፍትሀዊ አጠቃቀም ዙሪያ ቆርጠን አቋም ያላቸው የተፋሰሱ ሀገራት የቀደመውን ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል ይጠበቅባቸዋል።
ኤልያስ ጌትነት
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም