አዲስ አበባ፡- የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ውድድር የዜጎችን ሥራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስና ስታርት አፕን ለማጎልበት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተመላከተ፡፡
ሦስተኛው ምዕራፍ የዳሸን ባንክ “ዳሸን ከፍታ” የወጣቶች የስራ ፈጠራ ቅድመ ውድድርና ሥልጠና ትናንትና ተካሂዷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የስማርት ሲቲ አቅም ግንባታና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አመሃ ሲሳይ በዕለቱ እንደገለጹት፤ የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ውድድር የዜጎች የስራ አጥነት ምጣኔ ለመቀነስና የስታርት አፕ ዘርፉን ለማጎልበት ወሳኝ ሚና አለው፡፡
ቢሮው የከተማውን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ተግባራት ለማከናወን እንዲቻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የዳሸን ባንክ አክሲዎን ማህበር በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
በመጀመሪያውና በሁለተኛው ምዕራፍ ተገቢው ክትትልና እገዛ ተደርጓል ያሉት አቶ አመሃ፤ በአዲስ አበባ በሚካሄደው ሶስተኛው ምዕራፍ ላይም ተገቢው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ አመሃ ገለጻ፤ባንኩ በአጭርና በረጅም ጊዜ እያከናወነ የሚገኘውን “የዳሸን ከፍታ” የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ውድድር ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዝ ነው፡፡ ሦስተኛው ምዕራፍ በተፈለገው ልክ ውጤታማ እንዲሆን እና ስታርት አፖች እንዲበራከቱ ለማድረግ በተቀናጀ መልኩ መስራት ያስፈልጋል፡፡
የዳሸን ባንክ ቺፍ ስትራቴጂክ ኦፊሰር ተወካይ አቶ ወልደማርያም ደረሰ በበኩላቸው፤ የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ውድድር ኢኮኖሚውን ከመደገፍ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
ሦስተኛው ምዕራፍ የዳሸን ባንክ የወጣቶች የስራ ፈጠራ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ከሚገኘው በተጨማሪ አንደኛውና ሁለተኛው በተለያዩ ከተሞች መካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ባንኩ በስራ ፈጠራ ዘርፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት እየተገበረ ባለው ዳሸን ከፍታ የስራ ፈጠራ ውድድር ከመካሄዱ በፊት የሚሰጠው ስልጠና በተለያዩ ከተሞች መሰጠቱንም ነው ያብራሩት፡፡
እንደ አቶ ወልደማርያም ገለጻ፤ ከውድድሩ በፊት ለሰልጣኞች ተግባራዊ ሥልጠና ለመስጠት በተለያዩ ከተሞች እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ዳሸን ባንክ፤ አማካሪ ድርጅት ቀጥሮ ውጤታማ ስራ አከናውኗል፡፡
አቶ ወልደማርያም፤ በአዲስ አበባ ከተማ በስራ-ፈጠራ ፅንሰ-ሃሳብ፣በፈጠራ ንድፈ ሃሳብ አዘገጃጀት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ሥልጠናው የስራ-ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ሃሳባቸውን በምን መልኩ ማቅረብና ወደ ሥራ መቀየር እንዳለባቸው የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ወልደማርያም አክለውም፤የውድድሩ አሸናፊዎች ከዕውቅና እና ሽልማት በተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ ያገኛሉ ያሉ ሲሆን፤ ሦስተኛው ዙር ስልጠናና ውድድርም አዲስ አበባን ጨምሮ በአስር ከተሞች ላይ እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት የዳሸን ከፍታ የስራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች በባንኩ ፋይናንስ ተደርገው ስኬታማ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም