የሊዝ አዋጁ ለሙስና አጋላጭ እንዳይሆን በአግባቡ ሊመረመር እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት አሳሰቡ

የአምስት ሚኒስትሮች ሹመት ጸደቀ

አዲስ አበባ:- የከተማ መሬትን በምደባ እና በድርድር በሊዝ ለመያዝ የሚያስችለው አዋጅ ውስን የሆነውን የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት ለሙስና ተጋላጭ እንዳያደርግ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ በአግባቡ እንዲመረምረው የምክር ቤት አባላት አሳሰቡ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባው የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ‹‹የከተማ መሬትን በሊዝ ስለመያዝ›› የወጣውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክተው ባቀረቡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ ለተሳለጠ፣ ለውጤታማ፣ ለፍትሐዊና ለጤናማ የመሬት እና መሬት ነክ ንብረት ገበያ ልማትን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የከተማ መሬት አስተዳደር ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ነው፡፡

ቀጣይነትን የተላበሰ የነጻ ገበያ ሥርዓትን ለማስፋፋት፣ ግልጽና ተጠያቂነት ለሰፈነበት የከተማ መሬት አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ነው ተስፋዬ (ዶ/ር) የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የከተማ መሬት ፍላጎትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ማድረጉን በማስታወስም፤ ፍላጎቱን ባግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል የመሬት ሀብት አቅርቦት እና አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ማሻሻያው ወሳኝ እና አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

ለፌዴራል የባለበጀት የመንግሥት ተቋም ለአገልግሎት የሚውል ቦታ በፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ሲቀርብ በክልል፣ በአዲስ አበባ በከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ የከተማ መሬት በምደባ እንዲሰጥ የሚፈቅድ መሆኑ በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል፡፡

ለሃይማኖት ተቋማት የአምልኮ ማካሄጃ ቦታ፣ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለሚካሄዱ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ቦታ፣ ለከተማ ግብርና የሚውል፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚውል በምደባ ሊፈቀድ ይችላል ተብሎ ከተዘረዘሩት መካከል ይጠቀሳል፡፡

የምክር ቤት አባላት የከተማ መሬትን በምደባ እና በድርድር በሊዝ እንዲያዝ የማድረግ አሰራር ለሙስና የሚያጋልጥ ነው፤ መሬት ውስን ሀብት እንደመሆኑ ለሙስና እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ባግባቡ መርምሮ በምደባ እና በድርድር የሚሉትን ሃሳቦች ከረቂቅ አዋጁ እንዲያስወግድም ጠይቀዋል፡፡

ምክር ቤቱ የከተማ መሬት ይዞታ እና መሬት ነክ ንብረት ለመመዝገብ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን፣ የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት ያጸደቀ ሲሆን፤ ሹመታቸው የፀደቀው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያ ሥላሴ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ናቸው፡፡

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You