አዲስ አበባ፡- የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ወደትግበራ መግባቱ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ተርታ ሀገራት ለማሰለፍ የተያዘውን ሀገራዊ እቅድ ለማሳካት መሠረት ይሆናል ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ሰነድ ትናንት ይፋ ሲደረግ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ፖሊሲው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ያግዛል።
አዲሱን ስትራቴጂ ተጠቅሞ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲውን በአግባቡ ለመተግበር ቁርጠኝነትን እና በትብብር መሥራትን እንደሚጠይቅ ጠቁመው፤ ሁሉም ባለድርሻዎች ለፖሊሲው ተግባራዊነት የየድርሻቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የልማት አጋሮችና ሌሎችም ባለድርሻዎች ለስትራቴጂው ተግባራዊነት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቴክኖሎጂ ለግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት እንዲሁም አምራች ዘርፉ እድገት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህም ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የሥራ እድል ፈጠራን በማበረታታት በኩልም በር ከፋች ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ ቀጣና ድርጅት የኢትዮጵያ አስተባባሪ ተወካይ አቶ ሳሙኤል
የፖሊሲው ትግበራ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ መሠረት ይሆናል
ፈቃደ በበኩላቸው፤ ስትራቴጂው በ2014 ዓ.ም የጸደቀውን የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚረዳ ነው ብለዋል።
ፖሊሲው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን አንስተው፤ ስትራቴጂው ደግሞ የሌሎችን ሀገራት ልምዶች በመቀመርና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ባስገባ መልኩ ፖሊሲውን ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችሉ ዝርዝር እቅዶችን ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለትግበራው የሚያስፈልጉ የሰው ሀብት፣ የፋይናንስ ምንጭና ከልማት አጋሮች ጋር በምን መልኩ መተባበር ይቻላል የሚሉትን እንዲሁም ሌሎችንም አስፈላጊ ጉዳዮች ያካተተ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሳይንስ፣ ቴክሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ የላቸውም ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ ፖሊሲ ያላቸውም ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ አላዘጋጁም በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ አንድ ርምጃ ወደፊት ተጉዛለች ብለዋል፡፡
የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ በ2014 ዓ.ም መጽደቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ማስፈጸሚያ ስትራቴጂው ለቀጣይ 10 ዓመታት እንደሚያገለግል ተመላክቷል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም