ክልሉ ከ137 ሺህ በላይ አዳዲስ የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጅት አድርጓል

አዲስ አበባ፡- በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ137 ሺህ በላይ አዳዲስ የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ሥራ እና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ፡፡ በቢሮው የተቋማት አቅም ግንባታ አግባብነትና የጥራት ማረጋገጥ ዳይሬክተር አቶ ሙላው ልመንህ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በክልሉ በሚገኙ በ126 የመንግሥትና በ120 የግል የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተያዘው የትምህርት ዘመን በተመረጡና ገበያን መሰረት ባደረጉ ዘርፎች 137 ሺህ 262 አዳዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በመደበኛ ፕሮግራም የሚቀበላቸውን 61 ሺህ 665 ነባር ሰልጣኞች ጨምሮ በድምሩ ከ198 ሺህ 900 በላይ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ዝግጅቶች መደረጋቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ የነባርም ሆነ የአዲስ ሰልጣኞች ምዝገባ የመቁረጫ ነጥቡ ይፋ ከሆነ በኋላ ምዝገባው መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

ኮሌጆችም የማስተዋወቅ ስራዎችን በመስራት ወደ ምዝገባ እየገቡ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዝግጅት ምዕራፎች ላይ የተለያዩ ንቅናቄዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ ሙላው አንስተዋል፡፡ሰልጣኞች በወቅቱ ተመዝግበው ስልጠናቸውን እንዲጀምሩ በየኮሌጆች ቅስቀሳዎች እየተካሄዱ ሲሆን፤ በቀጣይ ቅስቀሳው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት፡፡

እንደ አቶ ሙላው ገለጻ፤ በኮሌጆች መደበኛ ሰልጣኞችን መቀበል ብቻ ሳይሆን የስራ ዕድልን ሊፈጥሩ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ለ986 ሺህ 995 ስራ ፈላጊዎች አጫጭር ስልጠናዎች በመስጠት ወደስራ እንዲገቡ የማድረግ ስራም ይሰራል፡፡

በዚህም በዝግጅት ምዕራፉ ላይ 38 ሺህ የሚደርሱ ሰልጣኞች በስራ ፈጠራ ዙሪያ ስልጠና መውሰዳቸውን አንስተው፤ በተጨማሪም ለ24 ሺህ ሰልጣኞች የክህሎት ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

የየኮሌጅ አመራሮችና አሰልጣኞች በስራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካኝነት በቂ የአቅም ግንባታ ስልጠና መውሰዳቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ በክልሉ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ግጭቶች ቢኖሩም ትምህርት መሰረታዊ ነገር በመሆኑ በየትኛውም ቦታ መቆም እንደሌለበት በማመን ስልጠናው በሁሉም ቦታ እንዲጀመር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ የግልም ሆኑ የመንግሥት ኮሌጆች በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የተቀመጠውን የመቁረጫ ነጥብ ያላሟሉ ሰልጣኞችን መቀበል እንደሌለባቸውና የግል ተቋማት በክልሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመጠቀም ህገወጥ ተግባራትን ሊያከናውኑ ስለሚችሉ ሰልጣኞች ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በተለይም በግል ኮሌጆች የሚሰጡ ስልጠናዎች ለትርፍ ማግኛ ብቻ ሳይሆን ተገቢውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት የጨበጠ ሰልጣኝ ማፍራትን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበት የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የግልም ሆኑ የመንግሥት ኮሌጆች ለሰልጣኞች ጥራት ያለው ስልጠና ለመስጠት ትኩረት አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You