103 ሺህ የንግድ ተቋማት ላይ ርምጃ ተወስዷል
አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከወጪ ንግድ ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በሩብ ዓመቱ 103 ሺህ በሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱም ተመላክቷል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገምግመዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ አንደኛ ሩብ ዓመት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት የአፈፃፀም ውጤቶች ጎልተው የወጡበትና በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክትትል ከሚያደርግባቸው ምርቶች የወጪ ንግድ አንድ ቢሊዮን 508 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡
የገቢ ግኝቱ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ700 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በንግድ ስርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ ከ900 ሺህ በላይ ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ450 ሺህ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በግምገማቸው የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት አማራጭ ገበያዎችን ከማስፋፋት አንፃር በሩብ ዓመቱ 88 አዳዲስ የሰንበት ገበያዎች ተመቻችተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በመላ ሀገሪቱ አንድ ሺህ 334 የሰንበት ገበያዎች ተመቻችተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በህገ-ወጥ ንግድ ላይ ከክልል ንግድ ቢሮዎች ጋር ባደረገው የክትትልና የቁጥጥር ስራ 103 ሺህ በሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ ርምጃ በመውሰድ ገበያው እንዲረጋጋ መደረጉን አመላክተዋል፡፡
ከጥራት መሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ለዘጠኝ ዓመታት ግንባታው ተጓቶ የነበረው የህንጻ ግንባታና የላብራቶሪ ተከላ ስራ በሩብ ዓመቱ በተደረገው ከፍተኛ ስራ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸው ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም