ዜና ትንታኔ
በኢትዮጵያ ከመሬት ጋር የተያያዙ ግጭቶች ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በዓመት ወደሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ የግጭት መንስኤ ጉዳዮች “ኬዞች” እንደሚነሱ የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ በመደበኛ የፍትህ ሥርዓት የሚያልቀው ጉዳይ ጥቂቱ ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። አብዛኛው ጉዳይ በባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችና በባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሚቋጭ አሊያም በእንጥልጥል የሚተው ነው።
በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት በመሬት ጉዳይ የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመቅረፍ፤ በተለይም በተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሱ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የኢትዮጵያ መሬት ፍትህ መመሪያ ይፋ ተደርጓል። መመሪያው የመሬት አለመግባባቶች በሚፈቱበት ጊዜ ለተጠቃሚዎች እና ባለሙያዎች መፍትሄ የሚያገኙበትን መንገድ ያቀርባል፡፡
በማህበረሰብ ደረጃ የፍትህ አቅርቦትን በማጠናከር. የፍትህ መመሪያዎች ምርጥ ተሞክሮዎችን በማዋሃድ እና በማስተካከል የቀረበ መመሪያ መሆኑም ሲገለጽ ይሰማል። መመሪያው በውስጡ በያዛቸው ጉዳዮች ፍትህን ለማስፈን ምን ፋይዳ ይዞ መጣ? ምን አይነት መፍትሔስ ይኖረዋል በሚሉ ጉዳዮች ላይ የዘርፉ ኃላፊዎችና ምሁራን ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በየዓመቱ ከሚፈጠሩ ሁለት ሚሊዮን የመሬት ጉዳትን መነሻ ካደረጉ አለመግባባቶች መካከል አብዛኛው ጉዳይ የሚያልቀው ማህበረሰቡ ለረጅም ጊዜ ሲጠቀምበት የነበረውን ልማድና ባህልን መሠረት አድርጎ ነው ይላሉ።
ማህበረሰቡ ሲጠቀምበት የነበረውን ልማድና ባህል ቦታ ሰጥቶ ማገዝ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነትም ጭምር መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራራሪያ፤ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ልማዳዊ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገቢውን እውቅና እንደሚሰጥ ያስቀምጣል፡፡ የልማዳዊ ሥርዓቶች በህግ ጉዳይ የሚነሱ ችግሮችን ጭምር እየፈቱ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ተነስቶ አግባብ ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል፡፡
የመሬት ፍትህ መመሪያው የመነጨውም በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ድረጃ ተግባራዊ የሚሆን የፍትህ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ሲሆን፤ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ከያዛቸው ዋና ጉዳዮች አንዱ የመሠረተ ማህበረሰብ ፍትህን በኢትዮጵያ እውን ማድረግ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፍትህ ዘርፍ የተለያዩ ማሻሻያዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ማሻሻያዎቹ ያመጧቸው በጎ ውጤቶች እንዳሉ ሁሉ ፍትህ ሚኒስቴር ከሌሎች አካላት ጋር በሠራው ጥናት እስካሁን የሕዝቡን ፍላጎት ከማሟላት አንጻር የሚቀሩ ጉዳዮች እንዳሉ ያብራራሉ፡፡ መፈታት ያለባቸውን ችግሮች በጥናት ለመለየትና እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ የሶስት ዓመት የፍትህ ትራንስፎርሜሽን እቅድ መቀመጡን አመላክተው፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ዋነኛው የመሰረተ ማህበረሰብ ፍትህ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የመሰረተ ማህበረሰብ ፍትህ ደግሞ ህብረተሰቡን መሠረት ያደረገና ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነጥብ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ህብረተሰቡ የእለት ከእለት ግጭቶቹን የሚፈታበትና ለዘመናት የነበሩ ልማዳዊ ሕግ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ከመሬት ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮችን እንደሚያካትትም ያስረዳሉ። ይህንን አግባብ ባለው መልኩ ተገቢውን እውቅና በመስጠት ከመደበኛ ፍትህ ሥርዓት ጋር ውጤታማ በሆነ መልኩ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
አዲሱ የመሬት ፍትህ መመሪያ ሀገሪቱ በመሬት ላይ የሚነሱ አለመግባባቶችን እንዴት እንደምትይዝ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መሆኑ በመመሪያው ላይ ሰፍሯል፡፡ ይህ ጉዳይ በተለይም ባህላዊና መደበኛ የፍትህ አሠራሮችን የማሰናሰል፤ ሴቶችና የተጋላጭ አካላትን ከመሬት ጋር በተያያዙ ግጭቶች ውስጥ ያላቸውን አቋም ለመፍታት ትልቅ ሚና ያለው እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
መመሪያው ባህላዊ የማህበረሰብ እሴቶችንና መደበኛ የሕግ ሂደቶችን የሚያከብር ሥርዓት ለመዘርጋት ሚናው የጎላ መሆኑን ያመላክታሉ።
አዲሱ መመሪያ ለልማዳዊ ፍርድ ቤቶች መደበኛ የሆነ ማሕቀፍ ለመዘርጋት እንደሚጠቅም፤ ይህም በመሬት አለመግባባት ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑንም ነው የሚጠቁሙት።
መመሪያው እንደሚያብራራው፤ ሰዎች መሬታቸውን በሚጠቀሙበት መንገድ ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ እና መሬት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያዝ ስለሚፈልጉ፣ ለመፍታት የተለያዩ የፍትህ አካላትን ይጠይቃሉ፡፡ ሰዎች የሚያጋጥሟቸው አብዛኛዎቹ የመሬት ሙግቶች ከመሬት ውርስ፣ ፍቺ፣ እንዲሁም የመሬት ባለቤትነት ይገባኛል ጥያቄዎች፣ ወሰኖች፣ የመንገዶች ወይም የንብረት ባለቤትነት መብቶች እና ከመሬት ወረራ ጋር የተያያዙ ናቸው።
በመሬት ላይ የሚነሱ ግጭቶችን ማርገብ ለሰላምና ደህንነት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የመሬት ፍትህ መመሪያውም በዚህ መንገድ የተቃኘ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በሀገሪቱ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ ይመቻቻልም ነው ያሉት፡፡
የሂዩጅ ኢንስቲትዩሽን ፎር ኢኖቬሽን ኦፍ ሎ (Hiil) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳሙኤል ሙለር (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ይህንን መመሪያ በመቀበል ህብረተሰባዊ ትስስርን የሚያጎለብት፣ ግጭቶችን በብቃት የሚፈታ እና የሕዝቦቿን ፍላጎት በትክክል የሚያንፀባርቅ ፍትሐዊ ሞዴል የመፍጠር አቅም አላት።
መመሪያው ፍትሐዊነትን፣ አካታችነትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ልማዳዊ አሰራሮችን የሚያከብር የፍትህ ሥርዓት ለመፍጠር ወሳኝ ርምጃ ነው። በተጨማሪ የመሬት አለመግባባቶችን ለመከላከል ጠንካራ መደበኛ ማሕቀፍ ያለው፣ የክርክር መንስኤዎችን በመፍታት እና በቀላሉ መረጃን እና ሰነዶችን ተደራሽ ለማድረግ አጋዥ ነው ይላሉ።
የግለሰቦች መብቶችና ስምምነቶች መከበራቸውን እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነም ተፈጻሚ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ሲሆን፤ በመሬት ጉዳይ ክርክር ውስጥ ያሉ ወገኖች አንዳቸው ለሌላው አሉታዊ አመለካከቶች እንዳይኖራቸው ያደርጋልም ሲሉ ያስረዳሉ።
የመመሪያው አጥኚ ቡድን እንዳመላከተው፤ የኢትዮጵያ መሬት ፍትህ መመሪያ በመሬት ላይ የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት በተለይም በተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሱ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሂደቶች ተካተውበታል። መመሪያዎቹ የተነደፉት ከባህላዊ እና መደበኛ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ውስጥ ምርጥ ልምዶችን በማቀናጀት በኢትዮጵያ የመሬት ፍትህ ለሁሉም ፍትሐዊ፣ ዘላቂ እና ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
መመሪያው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች እና በመሬት ፍትህ ላይ ያሉ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ እንደሚያመላክተው፤ ከመሬት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ የመሬት ፍትህ መመሪያን ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ በተለይም ለችግር ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አካባቢ ያለው የግጭት ምክንያቶች አሳሳቢነት እያደገ ይሄዳል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም