ዜና ሀተታ
የሃይማኖት አባት ናቸው። ሰዎች ሲጣሉ መክረውና ገስጸው አስታርቀዋል። ስለ ሀገር ሰላምም መስበክ የስብከት ስራቸው አካል ነው። ቀሲስ በድሉ ፈቀደ። እኝህን አባት ያገኘናቸው ወላይታ ሶዶ ከተማ ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተካሄደ ያለውን የሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች ልየታ ለመሳተፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከጋሞ ዞን ገረሱ ወረዳ እንደመጡ ይናገራሉ። እንኳን ለሀገር ሰላም ይቅርና በግለሰብ ደረጃ ለመግባትም፣ ሃሳብ ለመስጠትና ህይወትን ለመለወጥም መመካከር ብዙ ጥቅም አለው ይላሉ።
አሁን የመጣንበት ዓላማ ትልቅ ነው። ከግለሰብ አልፎ የሀገርን ሰላምና አንድነት የሚያጸና ነው። በህዝቦች መካከል የጋራ መግባባት የሚጎለብትና የሚያጠብቅ ነው። ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ በመሆኑ በእጃችን የያዝነው ወሳኝ ዕድል መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይህን ዕድል በአግባቡ መጠቀም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻ መሆኑን ያመለክታሉ።
“ወጥቶ ለመግባት፣ተምሮ ለመለወጥ፣ ነግዶ ለማትረፍ፣የሰላም መረጋገጥ ያስፈልገናል። ሃይማኖትም ቢሆን ያለሰላም ዋጋ የለውም’’ የሚሉት ቄስ በድሉ፤የታጠቁ ወገኖቻችን ከአውዳሚ ተግባር ተመልሰው ለውይይትና ለምክክር ዕድል መስጠት ይጠበቅባቸዋል ።ምክንያቱም ጦርነትም ሆነ ግጭት መቋጫው ምክክር ነው ብለዋል። ከዚህ መነሻነት የከፋ ጉዳትና ውድመት ከመድረሱ በፊት ልዩነቶችንና ችግሮችን በምክክር መፍታት ከአሁን ጀምሮ መለማመድና ባህል ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ መክረዋል።
ለእኔ ኢትዮጵያ ሀገሬም እናቴም ናት። በዕድገት እየገሰገሰች እንድትሄድ እፈልጋለሁ። ህዝቡ ከድህነት እንዲወጣ ፍላጎቴ ነው። ለዚህ ደግሞ ሰላም ያስፈልጋል። ምክክሩ የኢትዮጵያ ችግሮችን ቋጠሮ ይፈታል ብዬ ስለማምን እኔም የድርሻዬን እየተወጣው ነው ሲሉ ገልጸውልናል ።
ሴት አርሶ አደሮችን ወክለው ተመርጠው ከደራማሎ ወረዳ እንደመጡ የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት አደኘ፣ የግብርና ስራዬን ጥዬ የመጣሁት ምክክሩ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ያመጣል ብዬ ስለማምንና ከፍተኛ ፍላጎት ስላለኝ ነው ያሉት። ሰላም ከሌለ አርሶ አደሩ ምርት ለማምረት ይቸገራል፣ምርቱን በሚፈልገው ዋጋ መሸጥ አይችልም። ሀገራዊ ምክክሩ በሀገራችን ልዩነቶች በምክክር ተፈትተው ሰላም ስለሚያረጋግጥ እየተሳተፍኩ እገኛለሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለእኛ ሰርቶ መለወጥ ቀላል ነው ያሉት አርሶ አደሯ፣ በተለይ እናቶች ሰላም ብዙ ነገራቸው ነው። ይህ ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካም በጸሎትም በተሳትፎም በግንባር ቀደምትነት መሳተፍ አለብን ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረኩን መጀመር አስመልክቶ እንዳሉት፤ኢትዮጵያ እኛን በውብ ባህልና እሴቶች ያላበሰች ሀገር ናት። የሀሳብ ልዩነቶች ሀገራችንን እየፈተኗት ነው። እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር እየተካሄደ ነው።
እስካሁን ሰባት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በክልል ደረጃ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች መረጣ በስኬት መካሄዱን አውስተው፣ በቀሪ ክልሎችም ለማካሄድ አሰፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ይጠቁማሉ ።
በደቡብ ኢትዮጵያ በክልል ደረጃ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ለስድስት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ይናገራሉ። በክልል ደረጃ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ በጥልቀት በመመካከር አጀንዳዎችን የማሰባሰብና በሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣ እንደሚካሄድም ይጠቁማሉ፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ቀናት እየተካሄደ የሚገኘው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቨል ማህበረሰ፣ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ይገልፃሉ። በምክክሩም ከ12 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 96 ወረዳዎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ይህ ታሪካዊ ሀገር የማሻገር ተልዕኮ እንዲሳካ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ላቅ ያለ ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ያቀርባሉ ።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም