አዲስ አበባ፡– በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን በመኸር ወቅት የተዘሩና ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ስራ እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን በመኸር ወቅት የተዘሩና ቀድመው የደረሱ ሰብሎች በሰው ኃይል የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ነው። በዚህም ከ13 ሺህ ሄክታር ማሳን በመሰብሰብ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀድመው የደረሱ የመኸር ሰብሎች ጊዜያቸውና ወቅታቸው ተላልፎ የምርት ብክነት እንዳይከሰት በሰው ኃይል የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ አመራሮችና ባለሙያዎች ወደየወረዳዎችና ቀበሌዎች በመሰማራት ማህብረሰቡን የማነሳሳትና የመቀስቀስ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል። ቀደመው የደረሱ ሰብሎችን በጊዜያቸውና በወቅታቸው በመሰብሰብ የክልሉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አብራርተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ2016/17 ዓ.ም የመኸር ወቅት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ አዝርእቶችንና ቋሚ ሰብሎችን ጨምሮ የማልማት ስራ ተሰርቷል ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ከዘሩትም ሰብሎች ውስጥ ጤፍ፣ ቦሎቄ፣ማሾና የሆርቲካልቸር ሰብሎች ደርሰው እየተሰበሰቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የደረሱ ሰብሎች በዝናብ እንዳይበላሹ በወቅታቸው የመሰብሰብና የመውቃት ስራ እየተሰራ ነው፤ እስካሁን ማለትም ጥቅምት 15/ 2017 ዓ.ም ድረስ ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ የመሰብሰብ ስራ ተከናውኖ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎች ሲሰበስቡና ሲወቁ በጥንቃቄ በመሰብሰብና በመውቃት የምርት ብክነትን ሊከላከሉ ይገባል ብለዋል።
እንደ አቶ አድማሱ አባባል፤ በክልሉ የስንዴ ሰብልን ምርታማነት ለማሳደግና የምርት ብክነትን ለመከላከል በኮምባይነር የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ ነው። በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን በመኸር ወቅት ሰባት መቶ 15 ሺህ 945 ሄክታር የእርሻ መሬትን በተለያዩና በቋሚ ሸብሎች የመሸፈን ስራ ተከናውኗል። በተለያዩና በቋሚ ሰብሎች በዘር ከተሸፈነው ሰባት መቶ 15 ሺህ 945 ሄክታር መሬትም 60 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።
የክልሉ አርሶ አደሮች ቀድመው የደረሱ ሰብሎች በጊዜያቸውና በወቅታቸው እንዲሰበሰቡና ወቅተው ወደ ጎተራ እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም