በበጋ መስኖ ከ145 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፡– ከመኸር እርሻ ከ50 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በበጋ መስኖ ከ145 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ክልሉ ባለፉት ሶስት ወራት ግብርናን ለማዘመን ፣ ምርትና ምርታማትን ለመጨመር በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እንዲሁም በመኸር እርሻ ወቅት የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎች በስፋት ተሠርተዋል።
በመኸር እርሻ ወቅት ክልሉ 564 ሺህ ሄክታር በማልማት ከ50 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅዶ እስካሁን 550 ሺህ ሄክታር መሬት ለምቷል ብለዋል።
በዝናብ ስርጭት መብዛት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች የስንዴ ዘር ያለተዘራ መሆኑን ያነሱት የቢሮ ኃላፊው፤ ያንን ለማካካስም ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ ባለው የጸደይ ወቅት ተጨማሪ 16 ሺህ ሄክታር መሬት ስንዴ መልማቱን ጠቁመዋል።
በመኸር እርሻው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ፣ የአርሶ አደሩ የማሳ አያያዝ፣ የተባይና አረም መከላከል ሥራው በጥሩ ሁኔታ መሆኑንና የማሳ ሰብሎች ቁመናም ምርታማነት የሚጨምር መሆኑን ያሳያሉ ሲሉ ገልጸዋል።
በተለይም በጋሞ አካባቢ የተጎዱ መሬቶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በስፋት የተሰራ ሲሆን፤ አሲዳማ መሬቶች ያሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ የአፈር ህክምና ተደርጎ በክላስተር እንዲለማ ተደርጓል ብለዋል።
እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ፤ የደረሱ ሰብሎች በወቅቱ መሰብሰብ አስፈላጊ በመሆኑ ከጥቅምት ወር ጀምሮ የተለያዩ ንቅናቄዎች እየተደረጉ ነው። እስካሁን 60 ሺህ በላይ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በንቅናቄው መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
ንቅናቄው በመኸርና በበልግ የለሙ ምርቶችን ከብክነት በጸዳ መልኩ መሰብሰብ ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሰብሎችን እንዳያበላሽ፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምርት አሰባሰብ ላያ ያተኮረ ሲሆን፤ በዚህም ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አመላክተዋል።
የቢሮ ኃላፊው፤ በተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራ በበጋ መስኖ 146 ሺህ ሄክታር መሬት በማረስ 35 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ። በበጋ መስኖ ከሚታረሰው መሬት 141 ሺህ ሄክታሩ በአትክልት፣ ፍራፍሬ እና በስራስር የሚሸፈን ሲሆን፤ የተቀረው መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የሚሸፈን መሆኑን አስረድተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ረገድ የተሠሩ ሥራዎችን በተለመለከተ በመኸር ወቅት ክልሉ በአንድ ጀንበር አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ዘጠኝ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን ያስታወሱት አቶ ኡስማን፤ ከችግኝ መትከል ባለፈም ወንድማማችነትና አንድነት ያጎለበተ ነበር ሲሉ ገልጸዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም