ጥያቄዎቻችን ለምላሾቻቸው ጊዜ እንደሚፈልጉ አንዘንጋ

ለውጥ የሚለው ቃል ሲሰማ ሁሉም በየድርሻው፤ በየፊናው የሚመጣበት ሀሳብና ትዝታ ይኖራል። በብዙ ኢትዮጵያውያን የለውጥ ወይም የአብዮት ጊዜ ተብሎ የሚታወቀው የቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሣዊ ሥርዓት አክትሞ ዘመነ ደርግ በጀመረበት ጊዜ ነው። በእውነትም ይህ ወቅት ሀገሪቷ በደግም ይሁን በክፉ በርካታ ለውጦችን ያስተናገደችበት ነበር ለማለት ያስደፍራል።

በመቀጠል ደግሞ ኢሕአዴግ ተከተለ፡፡ ኢሕአዴግ በመምጣቱ፤ የተደሰቱበት እንዳሉ ሁሉ የተከፉበትም አልታጡም ነበር። ይህም ሆኖ ሀገሪቷም ሕዝቡም በለውጥ በተስፋም ውስጥ በመሆን ሦስት አሰርት ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ መዝለቅ ችሏል። ይህኛውም ለውጥ ግን ጊዜው ደረሰና የሕዝቡም ጥያቄ ጨመረና አዲስ ነገር በማስፈለጉ ሌላ የለውጥ ሂደት በሀገሪቱ ለመከሰት በቃ።

የዛሬው የጽሑፌ ማጠንጠኛ የሚሆነው ግን ለውጥን ተከትሎ የሚመጡ ውጤቶችን በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ማግኘት እንችላለን የሚል ይሆናል። ይህንን ለማለት ያነሳሳኝ ሀሳብ እንደ ሀገር ለውጥ ተከሰተ ከተባለ እለት ጀምሮ በአንድ ጀንበር ሀሳባቸው እና ምኞታቸው ሁሉ የሚሳካ ለሚመስላቸው የዋሆች እያስተዋልኩ ስለሆነ ነው።

በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት አመለካከቶች እንደ ሀገር የተከሰቱ ለውጦችን ተከትሎ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ተቋማት የሚካሄዱ ትንንሽ ሹም ሽሮችንም ተከትሎ መላ ሕይወታቸው እንዲቀየርላቸው ለጥያቄያቸው ሁሉ መልስ እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው። እንዲህ አይነት ምኞት ካላቸው መካከል ጥቂት የማይባሉት ለተከሰተው ለውጥ ምንም ዓይነት አስተዋፅዖ ያልነበራቸው ሊሆኑ ይችላሉ ።

የነዚህን ግለሰቦች ፍላጎት ለውጡን ያመጡት አካላት ራሳቸው የሚረዱት አይደሉም። በመሠረቱ ከለውጥ እንዲመጣ የሚጠበቀው እያንዳንዱ ውጤት የሚፈልገው የራሱ የሆነ ጊዜ ይኖረዋል። በዚህ ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ እንደተከሰቱት አይነት ሀገራዊ ለውጥ ሲሆን፤ ነገሩ ጊዜ ከመውሰዱም ባለፈ የሚያስከትላቸው በርካታ ተጨማሪ ጥያቄዎች ይኖራሉ።

ለዛሬ ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ለውጥና ዛሬ ያለው ሁኔታ ነው። በወቅቱ ሀገሪቷ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቃ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህም ማለት የሠላም እጦት፤ የኢኮኖሚ ድቀት፤ የፖለቲካ ውጥረት ገኖ ወጥቶ ነበር።

ከችግሮቹ ስፋትና ግዝፈት አንፃር ብዙዎች ‹‹ኢትዮጵያ አበቃላት የዘመነ መሳፍንት ታሪክ ሊደገም ነው፤ ልትበታተን ነው›› እያሉ በአደባባይ ሲተነብዩ ነበር። በእርግጥም ለሀገራዊ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት በብዙ መስዋዕትነት ነገሩን መቆጣጠር ባይቻል ኖሮ የተሰጋው መድረሱ አይቀርም ነበር።

የሆነው ሆኖ ነገሮች እየተስተካከሉ ሲመጡና ውጥረቶች መርገብ ሲጀምሩ ሁሉም የየራሱን ጥያቄ ይዞ ከተደበቀበት መውጣት ጀመረ። አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ከለውጡም በፊት ሲነሱ የነበሩ ቢሆኑም፤ ከፊሎቹ ግን የለውጡን አጋጣሚ እንጠቀም በሚል መንፈስ በብልጣብልጥነት የሚቀርቡ ነበሩ።

በእርግጥ የየትኛውም ማኅበረሰብ ጥያቄ ቢሆን በሠላማዊና በሕጋዊ መንገድ ሥርዓት ይዞ እስከቀረበ ድረስ ለጊዜውም ቢሆን የጥያቄው አይነት ችግር የሚኖረው አይመስለኝም። አሁን አሁን ግን እያስተዋልን ያለነው ፋታ የማይሰጥ አካሄድ ግን ለማንም የሚበጅ አይመስለኝም። ይህንን ያልኩት ደግሞ በሁለት መሠረታዊ እሳቤዎች ነው።

የመጀመሪያው የሀገሪቱ አቅም ነው። ይህንን ስል በሁለት አይነት መንገድ ነው። የመጀመሪያው በቀጥታ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ድሃ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ ሀገር እንደመሆኗ በአንድ ጀንበር ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሚገመትን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ አይቻልም።

መንግሥት ራሱ ፈቃደኛ ሆኖ አቅሙ ኖሮት ፕሮጀክቶችን ቢጀምር እንኳን ራሳቸው ፕሮጀክቶቹ የሚፈልጉት ዓመታትን የሚወስድ ጊዜ እንደሚኖር መገንዘብ ያስፈልጋል። ሌላው ከአቅም ጋር የሚነሳው ጉዳይ የሠላም ማስጠበቅ እንቅስቃሴው ነው። ይህም ቢሆን መታየት ያለበት በቀጥታ ሊሆን ከሚገባው ጋር ብቻ በማያያዝ ሳይሆን የነበርንበትንም መነሻ በማድረግ ነው።

ይህም ማለት አዲሱ ለውጥ በሀገሪቱ ከመከሰቱ በፊት ለውጡ በተከሰተባቸው ወራቶችና ከዛም በኋላ በተለያዩ አካላት የተሸረቡ በርካታ ሴራዎች ነበሩ። ሴራዎቹ ደግሞ እንደቀልድ የተሠሩ ሳይሆን፤ ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿ ያሉባቸውን ችግሮች በማጥናት በጥንቃቄ እንደ ሸረሪት ድር ተወሳስበው የተሸረቡ ናቸው። እነዚህን ውስብስብ የተንኮልና የጥፋት ገመዶች ለመበጣጠስ መንግሥት ምንም ያህል አቅሙና ቁርጠኝነቱ ቢኖረውም ጉዳዮቹ በራሳቸው የሚፈልጉት ጊዜ መኖሩ ሊታወቅ ይገባል ።

ሁለተኛው እንደ ሕዝብ የምናነሳቸው ጥያቄዎች እርስ በእርስ የሚጠላለፉ እና የሚደራረቡ መሆናቸው ነው። በአንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚቀርቡ ጥያቄዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የሚፈጥሩበትና ጥያቄ እንዲያስነሳ የሚያደርጉት የማኅበረሰብ ክፍል ይኖራል። መንግሥት ደግሞ ማሰብም መሥራትም ያለበት እንደ ሀገር ሁሉንም ነገሮች ከግምት በማስገባት መሆን አለበት።

ይህም ማለት የአንድን ማኅበረሰብ ጥቅም ሲያስከብርም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎችን ሲመልስ የሌላ ማኅበረሰብን ጥቅም በመጋፋትና ሌሎችን በማስቀየም ሊሆን አይገባም። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጥናቶችን ማድረግ በባለሙያዎችና የሕዝብ ለሕዝብ ምክክር ማካሄድ የግድ የሚሉ ይሆናል። እንደ «የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን» ማለቴ ነው። ይህም ቢሆን ችግሮች እና ተመልሰው የሚነሱ ጥያቄዎች እንዳይኖሩ በጥንቃቄ ጊዜ ሰጥቶ መሥራት የሚጠበቅ ይሆናል ።

ዛሬ ዛሬ እያየነው እና እየሰማነው ያለነው ግን ከዚህ በፍጹም የተቃረነ ነው። ሁሉም ያቀረበው ጥያቄ በአንድ ጀንበር እንዲመለስለት ይፈልጋል። አንዳንዱማ ጥያቄው ለምን እንደዘገየ ጠይቆ ምላሽ ከመስማት ይልቅ ‹‹እኔ ተገልያለሁ፤ እኔ ተገፊ ነኝ›› በሚል መንፈስ ለውጡን እስከማማረር ሲደርስ እየተመለከትን ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ ጥሩ አይደለም ብቻ ሳይሆን በዚሁ ከቀጠልንበት የሚያመጣብን ችግር መኖሩ አይቀርም። ሲጀመር እንደ ሀገር የምናስብ ከሆነ ኢትዮጵያ ብቻችንን የምንኖርባት እንዳለመሆኗ ሁሉ ለብቻችን የሚሰጠን ምላሽ የትም እንደማያደርሰን ልንገነዘብ ይገባል።

በተጨማሪ የመንግሥትን ኃላፊነትና ግዴታ ከራሳችን ጉዳይና ፍላጎት ጋር ብቻ ማገናኘቱ በራሱ ጤነኝነት አይደለም። በነጋ በጠባ ይሄን ጠይቀን ነበር … መንግሥት ይሄን አደርጋለሁ ብሎ ቃል ገብቶ ካደን… ከማለታችን በፊት ራሳችንንም ሆነ በቅርባችን ያሉ የመንግሥት አካላትን ፊት ለፊት ሄደን ለምን እንዲህ ሆነ? አልያም ለምን እንዲህ አልተደረገም? ብለን መጠየቅ መቻል አለብን። የእኛ የየግላችን ጉዳይ የየራሳችን የየግላችን ብቻ ነው።

መንግሥት ጉዳይ የሚያደርገው ግን የሁላችንንም ጉዳይ የሁላችንንም ጥያቄ ነው። በዛ ላይ ሀገራዊ የሚባል ከውጪ ሀገራት ጋር የሚሠራቸውም ሁላችንንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንደ ህዳሴው ግድብና የወደብ ጉዳይ ያሉ ኃላፊነቶችም አሉበት። በመሆኑም ጥያቄ መጠየቅ ችግር ባይሆንም ለመልሱ ጊዜ መስጠትና በትዕግስት ነገሮችን መጠበቅ የግድ ይላል። ቸር እንሰንብት።

ፍስሐ ተስፋይ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You