ውይይት – ከግጭት የሚታደግ የድል መሣሪያ

ወደ ፍቅር ጉዞ..

ተያይዞ..

ቂምን ከሆድ ሽሮ..

ኦላን ይዞ..

ድምጻዊ ክብር ዶክተር ቴዎድሮስ ካሳሁን ኢትዮጵያ በተሰኘ አልበሙ ላይ ኦላ የሚል ቃልን ተጠቅሟል። (ኦላ ማለት ፈጣሪ ማለት ነው። ፈጣሪን ይዘንና አስቀድመን በፍቅር ምሬት፣ ቂምን በመሻር ወደፍቅር ቤት እንግባ የሚል መልዕክት አለው። ቴዲም ሆነ ሌሎች ድምጻውያን በሙዚቃቸው ፍቅርን ሰብከዋል፣ አንድነትን ነግረውናል፣ ኢትዮጵያዊነትን መስክረዋል። በዚህ ልክ ለኢትዮጵያዊነት ከቀረብን ስለምን መግባባትና ሰላማዊ ፖለቲካ መፍጠር አቃተን የሚለው በቀዳሚነት የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡

ጥላቻ ወለድ ከሆነ ዘረኝነት እና የፖለቲካ እድፍ ጋር ሚዛን ላይ ብንቀመጥ ኢትዮጵያዊነትና ወንድማማችነት ገዝፎ በሚታይበት የእርስ በርስ ጉርብትና ውስጥ እንገኛለን። ከኋላ የመጡ የትርክት እዳዎች ፊተኛ መልኮቻችንን አወይበው በሰው ፊት በሞገስ እንዳንቆም አድርገውናል። አሁናዊ ልባዊ መሻታችን ከፉክክር ወጥተን በውይይት ነጻ አውጪ ድልን ለመቀዳጀት ነው።

በውይይት የሚመጣ ነጻ አውጪ ድል ሀገርን የሚያስቀድም፣ ብዙሃነትን የዋጀ፣ ለዘረኞች የማይመች አካሄድ ነው። ካለፈው ይልቅ ለሚመጣው የሚተጋ፣ በሰላማዊ ፖለቲካ ሰላማዊ ትግልን የሚያቀነቅን ብዙሃነ መርህ የሆነ ነው። በምክክር የሚመጣ ህብረብሄራዊ ገድል ትናንትን ሽሮ ዛሬን ዋጋ ባለው ጠቃሚ ምክረ ሃሳብ የሚጨብጥ፣ ፍቅርና ይቅርታን፣ እርቅና ምክክርን እንደ ነጻ አውጪ የድል መሣሪያ ወስዶ ትውልድ ላይ የሚሠራ አስተሳሰብ ነው።

ሀገር በቀደመችበት የትስስብ ፖለቲካ ሚዛን ደፍተን ጉድፎቻችንን ካላጠራን፣ እንከኖቻችንን ካልነቀስን እዳችን አስከፊ ነው። እውነት በራቃቸው ከዛም ከዚም በተነዙ የጥላቻ ስብከቶች ወገባችን ጎብጧል። መሠረት በሌላቸው፣ ታሪክ ባልከተባቸው የአሉባልታ ወሬ ፍቅር ያሰመረው ዳናችን ጠፍቷል። ወዴት እንደምንሄድ ባልገባንና በማይገባን ርምጃ መሀል ነን። ሀገርን የሚያህል፣ ትውልድን መሳይ ትልቅ የጸሀይ መውጫ አድማስ በሃላፊነት ይዘን ወዴት እንደምንሄድ አለማወቅ ከጥያቄም በላይ አፋጣኝ መልስ የሚፈልግ ነው፡፡

የነጻነት ምኩራቦቻችን፣ የፍቅር መጎናጸፊያችን ፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት መነሻዎቻችን በዘረኝነት መሠረታቸው እየጠፋ ይገኛል። እንደሀገር ያበለጸጉን፣ ልዩና ብርቅ አድርገው በጉርብትና ያስጠሩን እሴትና ባህሎቻችን የፍቅር ሳይሆን የልዩነት አተሃራ ፈሶባቸው ገርጥተዋል። በትርክትና በፖለቲካ ሽኩቻ የተጠነሰሰ ጫንቃችን ላይ የተሸከምናቸው የጥላቻ መንፈሶች አጓርተው እስካልወጡ ድረስ፣ ኢትዮጵያዊነትን አስቀድመን በውይይት መርህ በአንድ ሰርጥ ላይ እስካልተከተልን ድረስ ከችግሮቻችን በላይ ሆነን መፍትሄ ማምጣት አይቻለንም፡፡

ክፉዎች ከነገሩን፣ ከራስ ወዳዶች ከሰማነው፣ እዚያም እዚህም ጆሯችን ከተማገደ የጥላቻ ወሬ በላይ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እናውቃለን። ፖለቲከኞቻችን ሹክ ካሉን ትርክት በላይ፣ ዘረኞች በአደባባይ ካስጨበጡን የክፋት ሃሳብ በበለጠ ስለአብሮነትና ወንድማማችነት የገባን ነን። በየቦታው ከተሰራጩ የበቀልና የእልህ መንፈስ፣ ጦርነትና ክፋት ነጋሪ ከሆኑ አፎች በላይ ስለፍቅርና ስለይቅርታ የሰማነው ይበልጣል። እንደዚህ ከሆነ ስለምን ለክፋት ተቧደንን? ስለምን ጦርነትን ብቸኛ ነጻ አውጪ የድል ጎዳና አደረግን? የሚሉ አይጠፉም፡፡

ችግር የሆነው ያለንን እና የነበረንን አለማወቃችን ነው። የነበረን በጊዜያዊ የክፋት ሃሳቦች ጨቅይቶ የነበረንን ፍቅር እንዳናይ ከልሎብናል። ላሉብንና ወደፊትም ለሚኖሩብን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንደመፍትሄ የሚቀመጠው ኢትዮጵያዊነት ለንጽጽር ሚዛን ላይ የማይቀመጥ ብቸኛ የአብሮነት አርማችን እንደሆነና ጦርነትን ሽሮ በሃሳብና በውይይት የዳበረ ፖለቲካ መፍጠር ነው። ከዚህ ጋር አብረው የሚነሱ እንደበጎ እሴትና ሀገርና ሕዝብ የቀደሙበት እሳቤዎች ያሉ ለእርቅና ለአብሮነት መንገድ የሚከፍቱ አያሌ የትስስር ገመዶች መኖራቸው ሀቅ ነው፡፡

ከምናውቀውና ከሰማነው በጎ ወሬ በላይ የጥላቻ ወሬዎች ገዝፈው ጥንተ ጠዋታችንን ደመናማ አልብሰውት አሁን ላይ በደመና ስር በጭፍጋጌ እንገኛለን። የጥላቻ ፖለቲካ፣ የዘር ቡዳኔ ትርፍ የለውም። ሀገራችንን እንደየመንና አፍጋንስታን ታሪክ አልባ ከማድረግ ባለፈ ይሄ ነው የሚባል ዋጋ የሌለው ነው። የዘር አቀንቃኞች ሄደው ሄደው ዳር መቅረታቸው አይቀርም። በብዙሃነት በተደወረች ሀገር ላይ ጋቢ የሚሠራ ድውር ሃሳብ እንጂ በነጠላነት የሚጠራ ወደአንድ ወገን ያዘነበለ ትርክት አያስፈልገንም፡፡

ሀገራችን የእምነት ሀገር ናት.. የእምነት መለኪያውና መመዘኛው ደግሞ የኔ በሚሉት ፈጣሪ ፍቃድ ውስጥ መኖር ነው። ሁላችንንም በሚያግባባ መልኩ የፈጣሪ ፍቃድ ፍቅርና ሰላም፣ ከሰው ልጆች ጋር ሁሉ ተቻችሎ መኖር ነው። የፈጣሪ ፍቃድ በይቅርታና በመከባበር የጸና ነው። ከዚህ ውጪ የሆነ የትኛውም አይነት አካሄድ የነበረንን ከማሳጣት ባለፈ ትርፍ የሌለው እንደሆነ በበርካታ ታሪኮቻችን ላይ አስተውለናል፡፡

የሚጠቅመን ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን እንዳለው ኦላን ይዞ ወደ ፍቅር መሄድ ነው። የሚጠቅመን ቂምን ከሆድ ሽሮ ወደ ፍቅር መጓዝ ብቻ ነው። የሚጠቅመን ኢትዮጵያን አስቀድመን በወንድማማችነት መተባበር ነው። የእኛን ሰላም፣ የእኛን ፍቅር፣ የእኛን አንድነት የሚሹ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ከፊታችን አሉ። ፍቅርን ለብሰን፣ ሰላምን ተጎናጽፈን በጦርነትና በመለያየት በከሰርነው ልክ የምናተርፍበት የእርቅ ጊዜ እንዲመጣ ሁላችንም መተባበር ያስፈልገናል። በእርቅና በምክክር የጎደሉትን የምንሞላበት፣ ያጣነውን የምናገኝበት የኢትዮጵያዊነት ጊዜ ያስፈልገናል፡፡

ሰላምና ፍቅር በሌለበት ልብ ውስጥ የሚመጣ ጸጋና በረከት የለም። ሀገራችን በረከት የራቃት በእኛ በልጆቿ ሰላም አልባነት ነው። ሕዝባችን በችግር፣ በኑሮ ውድነት የሚሰቃየው ፍቅር ባልነካው ልባችን ነው። ሀገራችን በረከቷ እንዲመለስ ፍቅርን አፍቅረን፣ ሰላምን አስቀድመን መራመድ አለብን። ራሳችንን ከፍቅርና ከሰላም ስናርቅ የእግዚአብሄር መንፈስ ይርቀንና በምንም የማይሞሉ ብዙ ጎደሎዎችን፣ ብዙ ቀዳደዎችን እንፈጥራለን። እነዚያ ቀዳዳዎች ወደጦርነት፣ ወደጥላቻ፣ ወደ መገፋፋት ወስደውን እኛንም ሀገራችንንም ያከስሩናል። አሁንም ባለፉት ጊዜያትም እየሆነ ያለው ይኸው ነው።

ዝማኔ ቀለሙ በሃሳብ ልዕልና መዳበር ነው። ስልጥንና ከሚተረጎምባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ልዩነትን በምክክር መፍታት ነው። የሚቀረን ይሄ ነው..ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ መፍታትና ልዩነትን በምክክር ማርገብ። እንደሚታወቀው ሀገራችን በድግግሞሽ ፖለቲካ፣ በድግግሞሽ አስተሳሰብ፣ በድግግሞሽ ልማድ ውስጥ ለበርካታ ዘመን ኖራለች ይሄ አጉል ልማድ ከኪሳራ ባለፈ ያተረፈልን ነገር የለም። አሁን ፖለቲካችንንም፣ አስተሳሰባችንንም፣ ልማዳችንንም ከትናንት አላቀን ሰላምና ፍቅርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ልንለማመደው ይገባል፡፡

ታሪኮቻችን የአንድነት ታሪኮች ናቸው። ታሪኮቻችን የሰላም ታሪኮች ናቸው። ከዚያ እዚህ የደረስነው አብረን እየበላን አብረን እየጠጣን በክፉና በደጉ ተያይዘን ነው። እኚህ እሴቶቻችን ዳብረው በመሀከላችን እንደአስታራቂ መግባት ከቻሉ ብዙ ነገሮቻችንን ሊቀይሩልን አቅም አላቸው። ስለኢትዮጵያ በጋራ እስካልቆምን ድረስ የምንደርስበት የስኬት ተራራ የለም። በፍቅርና በይቅርታ ኢትዮጵያን እያሰበ የሚኖር ትውልድ መፍጠር አለብን።

ለሀገራችን ብዙ ምኞት አለን። ብንጠየቅ ስለሀገራችን የምንመልሰው በጎ መልስ አለ። ሕዝባችንን ከድህነት ማውጣት የሁላችንም የጋራ ፍላጎት ነው። ግን እንዴት የሚለውን መልስ አልደረስንበትም። ህልምና ምኞት እንጂ ህልምና ምኞታችንን ወደመሆን የሚያመጣ ጥበብ የለንም። የሆነ ቦታ ላይ ጥበብ ጎሎናል..በችግሮቻችን እየተሸነፍን፣ ለችግሮቻችን እጅ እየሰጠን የመጣንበት ሁኔታ ነው ያለው። የሰው ልጅ ሰላም እስካልገባው ድረስ ምንም ቢገባው ትርጉም የለውም። የምንፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ህልውና የሚያገኙት በሰላም ውስጥ ነው፡፡

ሰላም ሀገር ከሚገነባባቸው፣ ትውልድ ከሚቀረጽባቸው አውዶች ውስጥ አስኳሉ ነው። ለሀገራችን መሀል መሆን አለብን..መሀል ስንሆን ዳርም አለን። ዳር ስንቆም ግን ሌላ ነን። ዳር ቆመን ስለሰላም ማውራት አንችልም። ለሀገራችን ችግር የሆኑ ሰዎች ዳር የቆሙ ሰዎች ናቸው። በሀገራችን ጉዳይ ላይ መሀል ሆነን ስለሰላም መናገር መቻል አለብን፡፡

ሀገራዊ ህልሞቻችን የሚሳኩት ችግሮቻችንን በሰላም መፍታት ስንችል እንደሆነ ቢገባን ለንትርክ ጊዜ ባላጠፋን ነበር። አሁን ላይ አምነን መቀበል የሚገባን እውነት ይሄ ብቻ ነው። ሀገራችንን ከፍ ለማድረግ ልዩነቶቻችንን በንግግር ከመፍታት የተሻለ ሌላ አማራጭ የለንም። ልንለማመደው የሚገባን ሕይወት ሰላምን በሰላም ማምጣት እና ሀገርን በምክክር መፍጠርን ነው። በጦርነት ሰላምን ማምጣት ሞክረነው ያልተሳካልን ነገር ነው። ስለሀገርና ሕዝብ የምናስብ ከሆነ፣ ስለ ተሻለች ኢትዮጵያ የምንጨነቅ ከሆነ ሰላምን በሰላም መምጣትን መለማመድ አለብን፡፡

ችግሮቻችንን በችግር እየፈታን፣ በተፈጠረና በተደራረበ ችግር ውስጥ እየኖርን ህልሞቻችንን መኖር አንችልም። በችግር ላይ ችግር ደርበን ሕዝባችንን ከድህነት ማውጣት ያልቻልነው ልዩነታችንን በምክክር ማጥበብ ተስኖን ነው። ፍየል ወዲህ ቅምዝምዝ ወዲያ ከሆነ ፖለቲካ መላቀቅ አለብን። ፍላጎታችን ሰላም ከሆነ ስለሰላም ብቻ ማውራት አለብን። ጀግኖቻችንን ሰላም ውስጥ እንውለዳቸው። በጦርነት መጀገን ይብቃንና ፊታችንን ወደትቅቅፍ እንመልስ፡፡

በጦርነት አረር ደስታ፣ ፍንደቃ ሩቃችን ከሆኑ ሰንብተዋል። እፎይታ፣ እልልታ ከተለያዩን ከርመዋል። እኚህ ነገሮች እንዲመለሱ ስለሰላም በሰላም እናውጋ። በየትኛውም መስፈርት ቢታይ ኢትዮጵያ ሀገራችን የሚያስፈልጋት ሰላም ብቻ ነው። ሕዝባችን በብዙ ድህነት፣ በብዙ ማጣት ውስጥ ያለ ሕዝብ ነው። ጦርነትና ሽብር ጨምረንበት በስቃዩ ላይ ስቃይ ልንሆነው አይገባም። ዝቅታውን ለምን እንመርጣለን? ጦርነት እኮ ዝቅታ ነው፣ ጥላቻ እኮ ዝቅታ ነው። ከፍታውን እንምረጥ..ፍቅር ያለበትን፣ ሰላም የሞላበትን ከፍታ እንከተል። አንድነት የሞላበትን፣ ይቅርታ የተትረፈረፈበትን ከፍታ የእኛ እናድርግ፡፡

ሰላም ብዙ ትርፍ አለው.. በሰላም ማሸነፍን ስላልተለማድን ግን ትርፉን አናውቀውም። በእኔና በእናተ ሰላም፣ በፖለቲከኞቻችን ሰላም የምታተርፈው ኢትዮጵያ ናት። በኢትዮጵያ ትርፍ ውስጥ ደግሞ ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆናል። በኢትዮጵያ ትርፍ ውስጥ ደግሞ ትውልድ ይፈጠራል። የመልማት፣ የማደግ፣ የመበልጸግ ህልሞቻችን ሁሉ እውን የሚሆኑት ኢትዮጵያ ሀገራችን በሰላም ማሸነፍ ስትችል ነው። ማሸነፊያችንን ጦርነት ሳይሆን ሰላም እናድርግ፤ መለያየትን ሳይሆን አንድነትን እናድርግ። በሰላም የሚያሸንፉ ልቦች፣ በሰላም የሚያሸንፉ መሪዎች፣ በሰላም የሚያሸንፉ ፖለቲከኞች እነሱ እውነተኛ የሕዝብ አገልጋዮች ናቸው። እነሱ እውነተኛ የሥልጣኔና የዘመናዊነት መጀመሪያዎች ናቸው፡፡

እስከዛሬ ዋጋ ያስከፈሉን ነገሮች እጅግ ቀላል የሆኑ ነገሮች ናቸው። ሰው እጅግ ቀላል ለሆኑ ነገሮች እጅ ሲሰጥ ዋጋ ያላቸውን ጸጋዎቹን መሰወር ይጀምራል። ልብ ብለን ካየን በሰላምና በእርቅ ማለቅ በሚገባቸው ጉዳዮች ነው እየሞትንና መከራ እየደረሰብን ያለው። ማስተዋል ከቻልን ከጦርነት በኋላ በምንታረቅባቸው ነገሮች ነው ከጦርነት በፊት መነጋገር ያልቻልነው። ልብ ካልን ሊረቱን አቅም በሌላቸው ነገሮች ነው እየተረታንና ሰላማችንን እያጣን ያለነው። ሰላማችንን ለትንሽ ነገር አሳልፈን መስጠታችን ይቁም። በትንሽ ነገር ትልቅ ነገራችንን ማጣታችን በዚህ ትውልድ ላይ መቆም አለበት። ሃይላችንን፣ እውቀታችንን፣ ወንድማማችነታችንን ለትንሽ ነገር አሳልፈን ስንሰጥ ትልቅ ነገር ይርቀናል፡፡

ወደ ላይ እንያ.. ከላይ ሁሉም አለ። ሰላም እርቦን፣ አንድነት ናፍቆን በየሃይማኖታችን ሰማይ ስናይ እንያ። ሞትና መርዶ ባደበየው ልባችን ላይ የሰላምን ጮራ እንፈንጥቅ። በእርቅና በይቅርታ በልባችን ላይ ጸሀይ እናውጣ.. ንጋትን እንፈንጥቅ። ሰላም ጠምቶት የደነደነው ጭንጫ ልባችን በፍቅር ይረስርስ። ነፍሳችን እፎይ ትበል..በሰላም እንረፍ። ለመከራዎቻችን ሳይሆን መከራዎቻችን በእኛ ተሸንፈው እጅ እንዲሰጡን የሰላም ሰዎች እንሁን።

በገባሁበት ልውጣ…

ወደ ፍቅር ጉዞ..

ተያይዞ..

ቂምን ከሆድ ሽሮ..

ኦላን ይዞ..

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You