አዲስ አበባ:- ሕዝባዊ አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት ዲጂታል አስተውሎት እና ዲጂታል ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ገለጸ።
ፍርድ ቤቱ የ2016 አፈጻጸም ግምገማ፣ እውቅና እና ሽልማት፣ የ2017 ዓ.ም እቅድ ትውውቅ እንዲሁም ዲጂታል አስተውሎትና ዲጂታል ፍትሕ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡
የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ፉአድ ኪያር በመርሐ ግብሩ መክፈቻ፤ የአገልግሎት ጥራትን እና ቅልጥፍናን ለማሳደግ እና ተዓማኒነትን ያተረፈ የዳኝነት ሥርዓትን እውን ለማድረግ ቴክኖሎጂን ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የፍርድ ቤት አሠራርን ተደራሽ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ ለማድረግ፣ የዳኝነት ሥርዓቱንም ለማዘመን አሠራሩን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በ2016 ዓ.ም ከቀረቡለት 155 ሺህ በላይ መዝገቦች መካከል ለ135 ሺህ 233 መዝገቦች መፍትሔ መሰጠቱን፣ እስረኛ ያላቸውን መዛግብት ቅድሚያ ሰጥቶ መሠራቱንም ጠቁመዋል። ከ20 ሺህ በላይ መዝገቦች ደግሞ ወደ ተያዘው በጀት ዓመት መተላለፋቸውንም ነው የገለጹት።
የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አሸነፈች አበበ በበኩላቸው፤ በማስማማት ማዕከላት አንድ ሺህ 127 መዛግብት በስምምነት እንዲያልቁ መደረጉንና በቀጣይ በስምምነት የሚያልቁ ጉዳዩችን ለማሳደግ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
125 ሠራተኞች መልቀቃቸውንም በመጠቆምም፤ የአመራሮችና ሠራተኞችን ተነሳሽነት ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ 41 ሺህ መዝገቦች መከፈታቸውን ጠቁመዋል፡፡ መዝገቦች በተቀጠሩበት ሰዓት ስለመስተናገዳቸው ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋልም ብለዋል፡፡
የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ‹‹ዲጂታል አስተውሎት እና ዲጂታል ፍትሕን›› በሚመለከት ባቀረቡት ጽሑፍ፤ የዳኝነት ሥርዓትን ዲጂታላይዝድ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሠራር ሥርዓት ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱ በመጠቆምም፤ ጠንካራ የዳኝነት ሥርዓትን ለመገንባት ዳኞችም ሆኑ በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
በፍርድ ቤቶች በወረቀት እየተተገበሩ የሚገኙትን አሠራሮች በቴክኖሎጂ በመተካት አሠራርን ማዘመን እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ፍርድ ቤት መረጃ መስጫ እና ቅሬታ ማስተናገጃ መተግበሪያ ሥራ ላይ መዋሉን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፤ በቀጣይ ሥራውን ለማስፋት ትኩረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡
ከድምፅ ወደ ጽሑፍ የመቀየሪያ ሥርዓትን በፍርድ ቤት በማስጀመር በሙከራ ትግበራ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
መዝገቦች ተከፍተው የደረሱበትን ደረጃ መከታተል የሚያስችል የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ትግበራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት የሚገኝ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል፡፡
ዲጂታል አስተውሎት እና ዲጂታል ፍትሕን ተግባራዊ ማድረግ ለውጤታማነት፣ ለፍጥነት እንዲሁም ለወጪ ቁጠባ ጉልህ አስተዋፅዖ እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡ በፍርድ ቤቶች የሚገኙ መረጃዎች በየጉዳዮቻቸው በመለየት በቂ መረጃ ለማግኘት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት፡፡
ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሂደት፤ በዝግ ችሎት የሚታዩ ጉዳዮች ምስጢራቸውን የጠበቁ ከማድረግ አኳያ፣ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ባሕል አለማደግ፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ ሃገራት ዲጂታል ቴክኖሎጂን በኃላፊነት በመጠቀማቸው ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ኢስቶኒያዎች የጊዜ አጠቃቀም ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ማምጣት መቻላቸውን፣ ቻይናውያን የዳኞችን ጫና መቀነስ መቻላቸውንና የመወሰን ብቃትን ማሳደጋቸውን፣ ሕንዶች ወደዘጠኝ ቋንቋዎች የሚቀይር ሥርዓት መተግበራቸውን በአብነት አንስተዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም