በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ አጥነት ችግር በታሰበው ልክ እየቀነሰ አይደለም

አዲስ አበባ፡- የሥራ አጥነት ችግር በታሰበው ልክ እየቀነሰ እንዳልሆነ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ይህን ያስታወቀው በሥራ ዕድል ፈጠራ ችግሮች ዙሪያ ባሰናዳው የንቅናቄ መድረክ ላይ ነው።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ እንደገለጹት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ አጥ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስ አልተቻለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በክልሉ የሥራ ባሕል መገንባት ባለመቻሉ እና ፍትሐዊ አገልግሎት ባለመኖሩ ነው፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ባሕል መገንባት አለመቻሉ እና ፍትሐዊ አገልግሎት አለመኖሩ እንደምክንያት ይጠቀስ እንጂ በክልሉ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ከመንግሥት እቅድ ጋር ያልተገናዘቡ መሆናቸውም የሥራ አጥ ቁጥሩን ለመቀነስ አዳጋች ማድረጉን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በክልሉ ጤናማ የሆነ የብድር ሥርዓትን በመጣስ የሚሰጡ ብድሮች እና ብድሮች በወቅቱ አለመመለሳቸውም የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ወደ ኋላ እየጎተተው እንደሆነ ነው ያብራሩት።

ከመሬት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችም ሊቀረፉ እንደሚገባ ሀሳብ ቀርቧል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በክልሉ የሚስተዋለውን የሥራ አጦች ቁጥር ለመቀነስ እየሠራሁ ነው ብሏል።

የኢኮኖሚ ሥርዓቱ የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጥል ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቼ እሠራለሁ ያለው ቢሮው፤ እየተካሄደ ያለው የንቅናቄ መድረክም ይህን ለማሳወቅ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል።

በክልሉ 63 ተኪ ምርት ላይ የተሰማሩ እና 8 ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ የሚልኩ ኢንተርፕራይዞች እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል ሲል የዘገበው ኢቢሲ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You