በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ የሚካሄደው የምክክር መድረክ አስመልክተው ትናንት በወላይታ ሶዶ ከተማ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክልል ደረጃ የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከዛሬ ጀምሮ ለስድስት ቀን በተከታታይ ይካሄዳል።

በክልል ደረጃ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ በጥልቀት በመመካከር አጀንዳዎችን የማሰባሰብና በሀገራዊ ምክክር የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍም የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ፥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች እንደሚሳተፉበት ጠቅሰዋል።

በምክክሩም ከ12 ዞኖች የሚሳተፋ አንድ ሺህ 950 እስከ 2000 የኅብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ተገኝ ወርቅ ጌጡ (ዶ/ር) በበኩላቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከዚህ በፊት በ12 ዞኖች በኅብረተሰቡ የተመረጡ ተወካዮች ያሳትፋል። ሀገራዊ ምክክሩ አሳታፊና አካታች ነው። በክልሉ የሚገኙ ሁሉንም ወገኖችን የሚያሳትፍ ነው ብለዋል።

ይህ ታሪካዊ ሀገር የማሻገር ተልዕኮ ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ እንዲሳካ ኅብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልል ደረጃ የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በጋምቤላ፣ በሲዳማ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሐረሪ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያካሄደ ሲሆን በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞችም አካሄዷል። በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በቀጣይ የሚካሄድ ይሆናል።

ጌትነት ምሕረቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You