ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) የፖለቲካ ተንታኝ
አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ በየትኛውም ደረጃ ሉዓላዊነቷን የማስከበር በቂ ዝግጅት አላት ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመንካት በየትኛውም ደረጃ ቢመጡና ቢተባበሩ ሀገሪቱ የመጠቃትና የመውደቅ ደረጃ ላይ አይደለችም፡፡
ጠላት በሃይማኖት፣ በብሔረሰብ እና በማንኛውም ሽፋን ቢመጣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በቂ ዝግጅት ያላት ሀገር መሆኗን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ሲመጣ በዘመቻ የመነሳት ልምድ ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያን ለማጥቃት መሞከር ከንቱ ልፋት ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ገለጻ፣ የጠላቶችን ዓላማ መረዳት ካልቻልን እንደሀገር ጸንተን ለመቆም ያዳግታል፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶች መንግሥትን እወጋለሁ ሀገርን አፈርሳለሁ ለሚሉ አካላት የሎጀስቲክስ ድጋፍ ሰለሚያደርጉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጠላቶቻችንን ዓላማ መረዳት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ከውጭም ከሀገር ውስጥም ከሚነሱ ጠላቶች ራሳቸውን መጠበቅና ሀገራቸውን ማስከበር እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
አልሸባብ ላለፉት ዓመታት በሰሜንም፣ በምሥራቅም፣ በደቡብ ምሥራቅም ሃይማኖትን፣ ዳር ድንበርን እና ብሔረሰብን ሽፋን አድርጎ ጥቃት ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
እንደ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ገለጻ፣ አልሸባብን ከኋላ የሚገፉት ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ጠላት የሆኑ አሉ፡፡ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚያዳክም፣ ሀገርን የሚያፈርስና ሉዓላዊነትን የሚነካ ድርጊት ሲኖር መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምትፈልገው ከማንም ሳትደርስ ሕዝቧን፣ ሀብቷን፣ ሠላምና ደኅንነቷን መጠበቅ ቢሆንም፤ አንዳንድ ሀገራት ጥቅሟን በመፈለግ ይበጠብጣሉ፡፡ እነዚህ ሀገራት ከድርጊታቸው ተቆጥበው በመከባበር አብረው ቢሠሩ ያዋጣቸዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር አብሮ ለመልማት፣ ለማደግና ለመበልፀግ የጋራ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ትስስሮችን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሆነው የሚበጠብጡ አካላት ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም