ለብሔራዊ ጥቅም-ብሔራዊ አቋም

ኢትዮጵያዊነት በርካታ መገለጫዎች እንዳሉት እሙን ነው። ሀገራችንን ባሰብን ጊዜ የሚሰማንን ጥልቅ ስሜት “ኢትዮጵያዊነት” ብለን ልንገልጸው እንችላለን። የዚህ ስሜት ጥልቀት እንደ አስተዳደጋችን፤ ስለሀገራችን በሚኖረን እይታ እና መረዳት ልክ ሊለያይ ይችላል።

ለሀገራችን የምንሰጠው ዋጋ እና ሀገራችንን የምንወድበት መጠን የአንዳችን ከአንዳችን ቢለያይም ሀገሩ ቢያምርባት፣ ከድህነት ብትላቀቅ፣ ሕዝቦቿ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው ቢሟሉና ባማረ ስፍራ ቢኖሩ የማይወድ፤ በዓለም አደባባይ ስሟ ከፍ ቢል፣ ከአደጉ ሀገራት ተርታ ብትሰለፍ የሚጠላ ኢትዮጵያዊ አይኖርም።

እድገት በቅጽበት፣ ለውጥም በአንድ ጀንበር አይመጣምና የምንመኛት ኢትዮጵያ እውን ሆና ለማየት ከእያንዳንዱ የልማት ሥራ ጎን በቀናነት መሰለፍን፣ በብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ተመሳሳይ አቋም መያዝን ይጠይቃል። እንደ ማኅበረሰብ ልዩ ልዩ መልክ፣ ባሕል፣ ቋንቋ፣ አስተሳሰብና የፖለቲካ አቋም ቢኖርም በሀገር ጥቅምና እድገት ላይ የሚያስማማ አቋም ሊኖረን ይገባል። ሀገር የጋራ ናትና!

ፖለቲከኛው አቶ ግርማ ሰይፉ የሀገር ፍቅር አለኝ ብሎ የሚያስብ የትኛውም ዜጋ፣ ሀገር ውስጥ የሚከናወን የልማት ሥራን የእኔ ነው ብሎ መያዝ አለበት ይላሉ። እንደ እርሳቸው ሐሳብ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩ፣ በተራ በተራ ሀገር እንመራለን ተብሎ ነው የሚታሰበው፣ እንደዛ ካሰብን ደግሞ ገዢው ፓርቲ በሚያስተዳድርበት ጊዜ የሚሠራቸውን ሥራዎች በሙሉ መንቀፍ ሥራችን መሆን አይኖርበትም ሲሉ ያስረዳሉ።

ገዢው ፓርቲ በሚሠራቸው የልማት ሥራዎች ችግሮች ቢቃለሉ እኛ ሥልጣን ብንይዝ የእኛ ችግር ነው የሚቃለለው ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግም ያብራራሉ።

በመምህርነት የሚያገለግሉት አቶ ዘላለም ግርማም በበኩላቸው በሀገራችን ሊቀረፉ የሚገቡ ችግሮች በርካታ ናቸው የሚል ሀሳብ በማንሳት አስተያየታቸውን ይጀምራሉ። እነዚህን ችግሮች እየፈታን ለመጓዝ ከሕዝብ ዘንድ መንግሥትና ማኅበረሰብ በሚሠሯቸው የልማት ሥራዎች ጎን መሰለፍ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

ዛሬ የተሻለች አድርገን የምንገነባት ኢትዮጵያ ልጆቻችን ከእኛ የተሻለ ሕይወት የሚመሩባት ትሆናለች ያሉት መምህሩ የትኞቹንም የልማት ሥራዎችና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮችን ስናስብ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ትውልድን እያሰብን መሆን አለበት ይላሉ።

አቶ ግርማ፣ ያደጉ ሀገራት የፖለቲካ መከራከሪያ አጀንዳዎቻቸውን ስንመለከት እዚህ ግባ የሚባል ዓይነት እንዳልሆነ ያነሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ በእነዚህ ሀገራት የነበሩ ቀደምት ትውልዶች በርካታና መሠረታዊ የልማት ሥራዎችን ሠርተው ለተተኪው በማስረከባቸው የክርክር አጀንዳዎቻቸው የእኛ አጀንዳ ከሆኑት ከእነ መብራት፣ መንገድ ውሃና ሌሎችም የልማት ጥያቄዎች ያለፈ ነው። እነርሱ የስደተኞችን፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድልን መፍጠርን አጀንዳቸው ሲያደርጉ እኛ ግን የመሠረተ ልማት ፍላጎትን እናሳካለን እያልን ነው የምንከራከረው። እንደ እኛ ሀገር፣ ያደጉ ሀገራት ቀደምት ትውልዶች እነዚህን ሥራዎች አሳድረውባቸው ቢሆን ኖሮ፣ የእነርሱም የክርክር አጀንዳ ውሃና መብራት ይሆን ነበር። ስለዚህ ልማትን ማንም ይሥራው ለሀገር የሚጠቅም ከሆነ በጋራ ልንቆምለት ይገባል ያሉት ፖለቲከኛው፣ አሁን እየገጠመን ያለው ችግር ግን ልማቱ ጥሩ ነው ከተባለ በኋላ “ግን” ተብሎ የሚከተለው ነገር ነው ብለዋል።

መምህር ዘላለምም የልማት ሥራዎች ሲሠሩ ብዙዎን ጊዜ ከአንዳንድ ወገኖች ዘንድ አሉታዊ አስተያየቶች እንደሚደመጡ ያነሳሉ። ልማት ተሠርቶ ሲጠናቀቅ የመጡ ለውጦችን አለማስተዋልና እያዩ ዓይኔን ግንባር ያድርገው አይነት ቀና ምልከታ ለመስጠት ወደኋላ የማለት ልማድ ከአንዳንድ አካላት ዘንድ ማስተዋላቸውን በመጥቀስ፣ የመቃወም ልማዳችን መልካሙንም የምንቃወም አይነት አድርጎናልና ይህ አይነት እይታ መቀየር እንዳለበት፤ በጎ በጎውን ማበረታታት ጥቅሙ ለራስ መሆኑን መረዳት ያሻል በማለት አስተያየት ይሰጣሉ።

መምህር ዘላለምም እንዳሉት፣ የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ብቻ ሳይሆን የሀገርን ሉዓላዊነት በሚፈታተኑ ጉዳዮች ሲገጥሙን ብሎም ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ሊያሳጡን የሚሞክሩ አካላት ሲነሱብንም ጭምር ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ለሀገራችን በጋራ ልንቆም ይገባል። “ፖለቲከኞች ያልፋሉ ሀገርና ትውልድ ግን ይቀጥላል። ሀገርን ለማስተዳደር ዕድል ያገኘ መንግሥት የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎችና ከዓለም ሀገራት ጋር የሚከራከርባቸው ብሔራዊ ጉዳዮች እንደ ሀገር የሚጠቅሙን እንጂ ለግለሰብ አሊያም ለፖለቲካ ፓርቲ ጥቅም የሚውሉ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም።

የሀገራችን ኢኮኖሚ ሊደግፉ፣ ምርቶቻችን ወደ ውጪ ለመላክ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርልንን የባሕር በር እና ወደብ ጉዳይን ጨምሮ ሌሎችንም የልማት ሥራዎች የሚቃወሙ አካላት ጤናማ ናቸው ብዬም አላስብም በማለት የተናገሩት አቶ ግርማ፣ በልማት ጉዳይ ላይ ልዩነት ካለም ልማቱ እንዴት ነው የሚመጣው የሚለው እንጂ ይጠቅማል አይጠቅምም የሚለው ሊሆን አይገባም የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You