በሦስት ወራት 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል

አዲስ አበባ፡– በ2017 በጀት ዓመት ሦስት ወራት ውስጥ ብቻ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጤና ሚኒስቴር በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ የወባና ሌሎች ትንኝ ወለድ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ አቶ ጉዲሳ አሰፋ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት ውስጥ ለ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን የወባ ተጠርጣሪ ሕሙማን ምርመራ የተደረገ ሲሆን 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የወባ ሕሙማን ሆነው ተገኝተዋል።

የወባ በሽታ ወቅታዊ እና ከቦታ ወደ ቦታ የሚለያይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሀገሪቱ ዋናውን የክረምት ዝናብ መውጣት ተከትሎ በተለይም ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ወር ከፍተኛ ስርጭት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል።

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም በተሠራ የወባ ትንኝ ቁጥጥር ሥራ በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን አጎበሮችን ከፍተኛ የወባ ጫና ባለባቸው ወረዳዎች ስርጭት ተደርጓል ብለዋል።

በቀጣይም በአጠቃላይ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን አጎበሮች የሚሰራጩ ሲሆን እስከ ታኅሣሥ ወር ባሉት ጊዜያት አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን አጎበር ለማሰራጨት የታቀደ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ 167 ወረዳዎች በሚገኙ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ቤቶች የቤት ውስጥ የፀረወባ ኬሚካል ርጭት በማድረግ 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አቶ ጉዲሳ ጠቅሰዋል።

እንዲሁም በበጀት ዓመቱ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን የወባ መመርመሪያ ኪት የጤና ኬላዎች የተሰራጨ መሆኑን አንስተው፤ ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎችን ማከም የሚችል የተለያዩ የፀረ ወባ መድኃኒቶች ተሰራጭተዋል ብለዋል።

አቶ ጉዲሳ እንደገለጹት፤ የወባ በሽታ በተለይም የክረምት ዝናብ ሲወጣ በየቦታው የታቆረ ውሀ ቦታዎችና ጎርፍ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ለትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታዎች የሚፈጥር መሆኑ እንዲሁም የእርሻ ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሰዎች እንቅስቃሴ ስለሚበዙ የወባ ስርጭት ይጨምራል።

በሽታው ከቦታ ወደ ቦታ የሚለያይ የስርጭት መጠን ቢኖረውም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አማራ ክልል፣ ምዕራብ ኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ ስርጭት አለ። የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ ስለሆነም የወባ ምርመራና ሕክምና የማይሰጡ የጤና ኬላዎችን ወደሥራ በማስመለስ አገልግሎት የማስፋት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሠራ ሥራ እንደሀገር ከፍተኛ የወባ ስርጭት የሚከሰትባቸውና 76 በመቶ የወባ ጫና የሚይዙ 222 ወረዳዎችን በ9 ክላስተር በመመደብና ባለሙያዎችን በማሠማራት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ወቅቱ የወባ በሽታ በስፋት የሚሰራጭበት ወቅት መሆኑን በመገንዘብ የሚሰጡ አጎበሮችን በትክክለኛው መንገድ ከመጠቀም ጀምሮ አጠቃላይ የወባ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶቹን በመተግበር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You