መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ ማቀዱን ገልጿል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው ዕቅዱን ለማሳካት ብልሹ አሠራርን ማረምና አሠራሮችን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ ትኩረት ከሚደረግባቸው ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የተጀመረው ሪፎርም እየተሻሻለ ከሄደ ዕቅዱ ሊሳካ፤ ካልሆነ ግን ላይሳካ እንደሚችል ይጠቁማሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና እንደሚሉት፤ የውጭ ምንዛሪ ሪፎርሙ፣ ፕራይቬታይዜሽን መጀመሩ፣ የባንክ ሊበራላይዝድ መሆን እና የውጭ ባንኮች መምጣት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ሊስብ ይችላል።
የፖቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ሸዋፈራሁ ሽታሁን፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር የሚያደርጉ የተለመዱ መለኪያዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
የሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ባለሃብቶች እንደመለኪያ ከሚመለከቷቸው ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ደኅንነቱ አስተማማኝ ባልሆነበት ሀገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ይመጣል ተብሎ እንደማይታሰብ ይጠቁማሉ።
የቢዝነስ አሠራርን ቀላል ማድረግ ስለሚያስፈልግ ቢሮክራሲው የሚያሠራ መሆን እንዳለበት የሚገልጹት ተንታኙ፤ መንግሥት ከአንድ ባለሀብት እንዲሟሉ የሚፈልጋቸው የታክስ አከፋፈል፣ ፍቃድ አሰጣጥ እና እድሳት ቀላል መሆን እንዳለባቸው ይናገራሉ።
አቶ ክቡርም ይህንን ሃሳብ በመጋራት፤ ባለሀብቶቹ በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች በቂ የሰው ኃይል መኖሩ፣ የቢሮክራሲው መቀላጠፍ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ እና የቴሌኮሙኒኬሽን አቅርቦት ገብተው ሀብታቸውን ለማፍሰስ እንዲወስኑ ከሚያደርጓቸው መስፈርቶች መካከል እንደሚመደቡ ይጠቁማሉ።
በባንክ አሠራር የሚፈልጉት ነገር ካለም ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ ሸዋፈራሁ፤ ባለሀብቶቹ ትክክለኛ ሀብት እንዳላቸው መረጋገጥ አለበት። ትንሽ ነገር አሳይተው የሀገርን ሃብት ወደውጭ እንዳያግዙ መጠንቀቅ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ።
መንግሥት የሚሰጠው ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ ክቡር ደግሞ፤ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለማምጣት ከሌላ ሀገር ጋር ተወዳድሮ ማሸነፍ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። ለአብነትም በአየር መንገድ ረገድ ከሌሎች ጋር ለመገናኘት የሚያስችል አቅርቦት መኖሩን እንደአማራጭ ሊመለከቱት ይችላሉ ባይ ናቸው።
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ኬንያ ወይንም ደግሞ ታንዛንያ መሄድ የሚችል ከሆነ ለምን ኢትዮጵያ ይመጣል? ከሌሎች ጋር አወዳድሮ ስለሚወስን ከሌሎች አገሮች የተሻለ ጥቅም ማቅረብ ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ።
የኤሌክትሪክ አቅርቦት እና የታክስ ክፍያን ከኬንያም ሆነ ከታንዛኒያ በተሻለ ዋጋ ማቅረብ ከተቻለ፣ የሠራተኛ ደመወዝ አከፋፈል ከሌሎቹ ተወዳዳሪ ወይንም የሚቀንስ ሆኖ ከተገኘ እና መሰል ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩላቸው ለመምጣት እንደሚመርጡም አቶ ክቡር ይጠቅሳሉ።
አያይዘውም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የባንክ፣ የቴሌኮም ፕራይቬታይዜሽን እንዲፋጠን ይፈልጋል። ይህ በኢትዮጵያ እውን እየሆነ ነው። የሚመጣው ለራሱ ጥቅም እንጂ ለሀገር ጥቅም ብሎ አይደለም ነው የሚሉት።
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ጠንካራ እና ኃይለኛ ሆኖ ከመጣ ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ሀገሪቷ ኢንዱስትሪዎችን ፈተና ውስጥ የሚጥልበት ዕድል በመኖሩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ያስረዳሉ።
ዝም ብሎ በር መክፈት አይገባም ሲሉ የሚያሳስቡት አቶ ክቡር፤ የቻይናን ወይንም የጃፓንን አሊያም የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ብንመለከት የሚፈልጉትን እየመረጡ ነው የሚያስገቡት ነው የሚሉት።
አቶ ሸዋፈራሁ ኢትዮጵያ የገበያ ሥርዓቱን ነፃ ማድረጓን ተከትሎ የውጭ ባለሀብቶች በችርቻሮም በጅምላም ንግድ ሥራ ላይ መሠማራት የሚችሉበት አዋጅ መፅደቁን ያስታውሳሉ። የሚመጡ ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ጋር እኩል ተወዳድረው ትርፋቸውን የሚወስዱበት አጋጣሚ መፈጠሩንም ያነሳሉ።
እንዳይጎዱ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ከለላ ይደረግ ቢባል ግን ከፖሊሲ ውጭ ያደርጋል። ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር ሊያጋጭ ይችላል በማለት የአቶ ክቡርን ሃሳብ ይቃወማሉ።
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለእነርሱ ጥሩ ጥቅም ስላለው እንደመልካም አጋጣሚ ተመልክተው ሊሳቡ ይችላሉ። የገበያ ሥርዓቱ ነፃ መሆኑ ምናልባት ችግር የሚሆነው በሀገር ውስጥ ብር ለምንጠቀም እንጂ፤ ዶላር ላላቸው ሰዎች ተጠቃሚ ስለሚያደርጋቸው በኢትዮጵያ ካላቸው መልካም አጋጣሚ ይህ አንዱ ነው ይላሉ አቶ ሸዋፈራሁ።
ባለሀብቶቹ ሲመጡ ተነጋግረው ነው። ለምሳሌ የታክስ ቅነሳ ጥያቄ ሊያቀርቡ ወይም ለተወሰነ ጊዜ ታክስ እንዳይከፍሉ እፎይታ ሊሰጣቸው ይችላል። ዋናው ፍላጎቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ እስከሆነ ድረስ በሕግም ደረጃ ቢሆን የሌሎች ሀገራት የበለጠ ሳቢ እና የሚያበረታታ ከሆነ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ሁኔታ እንዳይቀንስ ከሌሎቹ ጋር ተወዳዳሪ በሆነ መልኩ የሚስብና የሚያበረታታ መሆን አለበት ሲሉም ይመክራሉ።
አቶ ሸዋፈራሁ ፕራይቬታይዝድ የሆኑ ኩባንያዎች መኖራቸውም ይጠቅመኛል ብለው እንዲገምቱ ያደርጋቸዋል። ጥሩ ትርፍ አግኝተው ትርፋቸውን ወደሀገራቸው ለመውሰድ የሚያስችል ሁኔታ እንደሚፈጠር ስለሚያስቡ የውጭ ምንዛሪም በገበያ መር መሆኑም ሊስባቸው ይችላል ነው የሚሉት።
ፕራይቬታይዜሽን መምጣቱ ተመሳሳይ የሆነ የሕግ ሥርዓት እና አሠራርን የሚያበረታታ የታክስ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ሃሳብም ሊኖራቸው እንደሚችል ነው የሚናገሩት።
በመንግሥት በኩል በኢኮኖሚ ሪፎርም የተወሰዱ ርምጃዎች ለውጭ ባለሀብቶች በጣም ጠቃሚ ናቸው። ውጭ ያለ ባለሀብት ፋብሪካ ለማቋቋም 100 ሺህ ያስፈልገው ከነበረ አሁን በ50 ሺህ ዶላር ያቋቁማል።
ገበያው ይምራው ሲባል በተወሰነ መልኩ ገንዘቡ ዋጋውን ማጣቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን እንዲመጣ ከሚያደርገው አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸውም የገለጹት በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
መንግሥት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ አስገባለሁ ላለው አምስት ቢሊዮን ዶላር እቅድ የመሠረተ ልማት ያለመሟላት፣ የትራንስፖርት፣ የኃይል አቅርቦት ወይም መቆራረጥ ተግዳሮት እንዳይሆን መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ የሚጠቁሙት አቶ ሽፈራው፤ ኤልሲ ለመክፈትና ሌሎች የባንክ ሥርዓቱ ቢሮክራሲዎች ባለሀብቶችን ተስፋ እንዳያስቆርጡ ትኩረት መደረግ አለበት፣ ሠላም መስፈንም አለበት ባይ ናቸው።
መሠረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃና መጠን መቅረብ እንዳለበት እና ቢሮክራሲው በተቻለ መጠን ሥራውን ማቀላጠፍ የሚችልበት ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ አመላክተው፤ የቪዛ አሰጣጥ፣ አቀባበል እና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱ የተፋጠነ መሆን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደሀገር እንዲመጣ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ይጠቁማሉ።
አቶ ሸዋፈራሁ፤ ከተፅዕኖ መላቀቅ የሚቻለው በሥራ ነው። ለስኬቱ ጠንክሮ በሀገር ውስጥ ምርታማነትን ማስፋት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ሰው በተሠማራበት ዘርፍ ላይ ጠንክሮ በመሥራት ተወዳዳሪ መሆን ይገባዋል ነው የሚሉት።
በሀገር ውስጥ ገንዘብ በማዞር የሚመጣ ለውጥ አይኖርም፤ ተወዳዳሪነትም አይሰፋም። ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የውጭ ምንዛሪ ማስገባት ሲቻል እንደመሆኑ፤ የውጭ ምንዛሪ በማከማቸትና በየጊዜው እንዲጨምር በማድረግ እድገት እንዲመጣ ማድረግና የሥራ ባሕል ለውጥ ያስፈልጋል ሲሉም ይመክራሉ።
እንደሚባለውም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከሌለ ‹‹በኢትዮጵያ ኢንቨስት ባደርግ ትርፌን ይዤ እመለሳለሁ›› በሚል ተስፋ ባለሀብቶች ሊመጡ እንደሚችሉና የተባለውን እቅድ ማሳካት እንደሚቻልም ይስማማሉ።
እቅዱን ለማሳካት መሠረተ ልማት ማሟላት፣ የቢዝነስ አሠራርን ቀላል ማድረግ፣ ሠላም ማስፈንና የባንክ አገልግሎትን ማዘመን ትኩረት እንዲሰጣቸውም ያሳስባሉ።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም