የእግር ኳስ ሕጎች ከመብዛታቸው የተነሳ አንድም ሳይቀር ሁሉንም ጠንቅቆ የሚያውቅ የስፖርቱ ባለሙያ የለም ማለት ባይቻልም፣ በእግር ኳስ ውስጥ ያሉ አሠልጣኞችና ፕሮፌሽናል ሰዎች ሁሉ ያውቋቸዋል ማለትም ድፍረት ይሆናል። ፊፋ በየጊዜው በርካታ ሕጎችን ያሻሽላል፡፡ የስፖርቱ ባለሙያዎችም እነዚህን የተሻሻሉ ሕጎች በየጊዜው እየተከታተሉ ራሳቸውን ከጊዜውና ከሁኔታዎች ጋር ማራመድ ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡
የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋ ካወጣቸውና በስፖርቱ ተግባራዊ ከሆኑ አስገራሚ ሕጎች መካከል አንዳንድ አሠልጣኞች እንዲሁም ፕሮፌሽናሎች ላያውቋቸው ይችላሉ ተብለው ከሚታሰቡ ሕጎች መካከል የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
# አንድ አሠልጣኝ ከፈለገ ለቡድኑ ሜዳ ገብቶ የመጫወት መብት አለው። ይህ ሕግ ብዙ ጊዜ ሲተገበር ስለማይታይ ብዙዎች ላያውቁት ይችላሉ። ይሁን እንጂ አሠልጣኝ የቡድኑ አንድ አካል እንደመሆኑ መጠን በተጫዋች ምትክ ወይም ተቀይሮ ሜዳ ገብቶ የመጫወት ሕጋዊ መብት አለው። ለዚህ ትክክለኛው ማሳያ ጂያንሉካ ቪያሊ ነው። ከዓመት በፊት በ58 ዓመቱ ሕይወቱ ያለፈው ጣሊያናዊው የቀድሞ የጁቬንቱስ ተጫዋች በ1990ዎቹ አጋማሽ በቼልሲ ቤት አሠልጣኝም ተጫዋችም ሆኖ ማገልገሉ ይታወሳል። ስለዚህ አንድ አሠልጣኝ አቅሙ እስካለው ድረስ ሜዳ ገብቶ ለቡድኑ ሲጫወት ቢታይ አያስደንቅም።
# በእግር ኳስ የረጅም ዓመታት ታሪክ አንድ ጨዋታ መምራት የጀመረ ዳኛ ጨዋታውን አጠናቆ ሲወጣ እንጂ እንደ ተጫዋች ተቀይሮ ሲወጣ ማየት የተለመደ አይደለም። ይሁን እንጂ በፊፋ ሕግ መሠረት አንድ ዳኛ የጀመረውን ጨዋታ ማጠናቀቅ የማይችልበት ችግር ከገጠመው በሌላ ዳኛ በተለይም በረዳት ዳኛ ተቀይሮ ሊወጣ እንደሚችል ተደንግጓል።
# ብዙ ጊዜ መስመር ዳኞች ከጨዋታ ውጭና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ዋናውን ዳኛ በማገዝ እንጂ ካርዶችን በመምዘዝ አይታወቁም። ይሁን እንጂ መስመር ዳኞች ካርድ ማሳየት የሚችሉበት አግባብ ግን አለ። ረዳት አሠልጣኞች ከዳኛ እይታ ውጪ የሆኑ ጥፋቶች (በተለይም ከሜዳ ውጪ ተጠባባቂ ወንበር አካባቢ ሊሆን ይችላል) ለሚፈጠሩ ችግሮች ረዳት ዳኞች ካርድ እንዲመዙ መጠየቅ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ረዳት ዳኞች በቀጥታ ካርድ አይመዙም፣ የዋናውን ዳኛ ይሁንታ ይጠብቃሉ። የዋናውን ዳኛ ይሁንታ ሲያገኙም በተመለከቱት ጥፋት ልክ የሚመጥነውን ካርድ መምዘዝ ይችላሉ። ረዳት ዳኞቹ ይህን ካርድ ቢመዙም ካርዱን ያሳየው ግን ዋናው ዳኛ ተደርጎ እንደሚቆጠር የፊፋ ሕግ 6 ላይ ተደንግጎ ይገኛል።
# አንድ ተጫዋች በቅጣት ምት፣ በማዕዘን ምት፣ በእጅ ውርወራ ወቅት ከጨዋታ ውጪ ቢሆን እንደ ጥፋት አይቆጠርበትም። በነዚህ አጋጣሚዎች ከጨዋታ ውጪ የሆነ ተጫዋች ኳስና መረብ ቢያገናኝ ይፀድቅለታል እንደማለት ነው። ይህን ሕግ ጠንቅቆ ባለማወቅ በአንዳንድ ሊጎች ላይ ተጫዋቾች የተቃራኒ ቡድን ተጫዋችን ከጨዋታ ውጪ ያደረጉ መስሏቸው ግብ ሲቆጠርባቸው የሚታይበት አጋጣሚ አለ።
# አንድ ተጫዋች ተቀይሮ እንደገባ ከቆመ ኳስ መሻማት እንጂ ጨዋታ ማስጀመር አይችልም። ይህ ማለት አንድ ተጫዋች ተቀይሮ ከመግባቱ በፊት ኳስ የእጅ ወይም የማዕዘን ምት ወጥቶ ከሆነ ልክ ተቀይሮ ሲገባ የወጣውን የእጅ ወይም የማዕዘን ምት (ኮርና) ኳስ ማሻማት ወይም ማስጀመር አይችልም።
# ግብ ጠባቂዎች እጅጌ ሙሉ ማለያ መልበስ ይፈቀድላቸዋል። ነገር ግን በጨዋታ መሐል እጅጌ ሙሉው ማልያ አልተመቸኝም ብለው ወደላይ ከፍ ማድረግ ወይም መሰብሰብ አይችሉም። ይህን ያደረገ ግብ ጠባቂ ካርድ ይመዘዝበታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም