አዲስ አበባ፡– ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የኢትዮጵያና የማሌዢያ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። የማሌዢያ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲሳተፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከማሌዢያ አቻቸው አንዋር ኢብራሂም ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ካደረጉ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ጋር የኢትዮጵያንና የማሌዢያን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማሳደግ የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ እና በማሌዢያ መካከል ያለው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የፈጀው የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተመሳሳይ የመሪዎች ጉብኝት ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል።
የግል ዘርፉ፣ የቱሪዝምና የመንግሥት ለመንግሥት ትብብሮች የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የማሌዢያ የንግድ ማኅበረሰብ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲጠቀሙ አበረታታለሁ በማለትም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ከማሌዢያ ወደኢትዮጵያ ለሚመጡ ባለሃብቶች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማቅረብና ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከማሌዢያ ስለፌዴራል መንግሥት ሥርዓት፣ ከተሞችን በማዘመን እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ዙሪያ ብዙ የምትማራቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በማሌዢያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ብሎም የማሌዢያ ሕዝብ እና መንግሥት በቆይታችን ለሰጣችሁን ደማቅ አቀባበል እና ፍቅር እናመሰግናለን ብለዋል።
ትብብራችንን ትኩረታቸውን በግብርና፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ታዳሽ ኃይል ላይ ባደረጉ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ብሎም ሰፊ አድማስ ባላቸው ሌሎች ቁልፍ ሥራዎች ላይ ለማጠናከር ተስማምተናል በማለትም ገልጸዋል።
የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አሕጉር ከሚገኙ ሀገራት መካከል ዋነኛ የሀገራቸው አጋር መሆኗን አስታውቀዋል።
ማሌዢያ ከኢትዮጵያ የምትማራቸው በርካታ ጉዳዮች በመኖራቸው ግንኙነቱን በማጠናከር እንሠራለን ሲሉ ገልጸዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ወደ ማሌዥያ ያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ ከሀገሪቱ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ተወይይቷል።
ልዑኩ በኢትዮጵያ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በጨርቃጨርቅ፣ በማዕድን እና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተመለከተ ለንግድ ማኅበረሰቡ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በአማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም