የኮሪደር ልማቱ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማበልፀግ የመዲናዋን ዕድገት እያፋጠነ ይገኛል

አዲስ አበባ፡- የኮሪደር ልማቱ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማበልፀግ ባለፈ የመዲናይቱን ሁሉን አቀፍ እድገት እያፋጠነ መሆኑን የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሣው (ዶ/ር ) ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ሳምንትን በማስመልከት በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የአዲስ አበባ ሙዚየምን፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያን፣ የሠላምና የወጣቶችን ፓርክንና ሌሎችንም በመዲናዋ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሣው (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የኮሪደር ልማቱ የመዲናይቱን ሁሉን አቀፍ እድገት በማፋጠን የአዲስ አበባ ከተማን ለመኖሪያ ምቹ ቦታ እንድትሆን እያገዘ ነው።

አዲስ አበባ በፈጣን እድገት ውስጥ ትገኛለች ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ፤ ከተማዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እጅግ አስደናቂና አበረታች የሆነ ለውጥ እያስመዘገበች ሲሆን ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ጎብኚዎችን የምትስብ ከተማ እየሆነች ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ጨምሮ በርካታ የልማት ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የኮሪደር ልማቱ ለሁሉም ምቹና ተስማሚ የሆነች ከተማ ከመፍጠር ባለፈ ለዘላቂ የቱሪዝም እድገት ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።

የቱሪዝም ሳምንት መከበሩ ባሕልን በመጠበቅ፣ ሠላምን በማስፈን እና በዜጎች መካከል አንድነትን በማጎልበት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ራዕይ ለማሳካት ቱሪዝም የዜጎችን አንድነት፣ የጋራ መግባባትንና መከባበርን በማጠናከር ረገድ የራሱን ሚና እንዲጫወት ጥረት እያደረገች ነው ብለዋል፡፡

የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓለም ለ45ኛ በኢትዮጵያ ለ37ኛ ጊዜ “ቱሪዝም ለሠላም፣ ሠላም ለቱሪዝም” በሚል መሪ ሃሳብ መከበሩን በመግለፅ፤ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ሳምንት ከጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ጎብኝዎቹ በበኩላቸው አዲስ አበባ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጓትን የተለያዩ የልማት ሥራዎች እያከናወነች መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉን አቀፍና በፈጣን የልማት ሥራዎቿ በሁለንተናዊ መልኩ ዘመናዊነትን እየተላበሰች እንደሆነ ተናግረዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You