በአዲስ አበባ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ የጋራ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ:- በመዲናዋ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ የጋራ ኢንቨስትመንቶች ተሳትፎ ማሳደግ ያስፈልጋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ጥሪ አቀረቡ። ኖህ ሪል እስቴት 750 የመኖሪያ ቤቶችንና ሱቆችን አስመርቆ ለነዋሪዎች አስረከበ።

በወቅቱ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ፤ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል፣ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣትና የልማት ማነቆዎችን ለመቅረፍ በማለም አዲስ አበባ ለጋራ ኢንቨስትመንቶች ክፍት መሆኗን ገልጸዋል።

ከለውጡ በኋላ በቅርቡ የተካሄደውን የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ ጨምሮ የተተገበሩ የሕግ ማዕቀፎች የመንግሥትና የግል ኢንቨስትመንቶችን በማጎልበት ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ናቸው ብለዋል።

ሦስተኛዋ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲና ማዕከልና የአፍሪካ ኅብረት መገኛ በመሆኗ የነዋሪዎቿን ፍላጎት የሚያረካ ፈጣን ልማት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ጃንጥራር፤ የመልካም አስተዳደር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለማሟላት የመንግሥትና የግል ዘርፍ የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

መንግሥት የመኖሪያ ቤቶችን ተደራሽነት ለማሳደግ ጥረት ቢያደርግም ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ የሚፈለገውን ያህል ውጤት አለመምጣቱን አስታውሰው፤ ከመንግሥት ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን በግል ኩባንያዎች እና በመንግሥትና የግል ባለሀብቶች የሚገነቡ የቤት ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

የኖህ ሪል እስቴት ዋና ሥራ አስከያጅ አቶ ፍቃዱ አዋሽ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኩባንያው መኖሪያ ቤቶችን በጊዜ እና በጥራት ገንብቶ በማጠናቀቅ ልምድ ማካበቱን ጠቁመዋል።

በቅርቡ በአዲስ አበባ እንቁላል ፋብሪካ በተሰኘ አካባቢ 750 መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም በአቧሬ ሴቶች አደባባይ 152 ቤቶች ለነዋሪዎች እንደሚያስረክብ አመላክተዋል።

ሕንፃዎች በፍጥነት መገንባት ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ የግንባታ ቡድን በማዘጋጀት፣ ዘመናዊ የኮንክሪት መሙያን በመጠቀምና የድርጅቱን የጥራት ላብራቶሪ በማቋቋም ለግንባታው ጥራት ከፍተኛ ቦታ መስጠቱን ተናግረዋል።

ሪል ስቴቱ ባለፉት 10 ዓመታት በ33 ሳይቶች 10 ሺህ የሚጠጉ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የመኖሪያ ቤቶችን ለቤት ፈላጊዎች ገንብቶ አስረክቧል ብለዋል።

በቀጣይ ወር በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ሆምስ በተባለ አካባቢ ከአምስት ሺ በላይ የሚሆኑ ቤቶችን ግንባታ እንደሚያስጀምር ገልጸዋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You