የእንስሳትን ጤና ለመጠበቅ ተጨማሪ ጥረት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፦ የእንስሳትን ጤናና ደኅንነት ለመጠበቅ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዓለም የእንስሳት ቀን በኢትዮጵያ ለ14ኛ በዓለም ለ99ኛ ጊዜ “ለሰው ልጅ ደኅንነት እና ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና በእንስሳት ደኅንነት ላይ ኢንቨስት እናድርግ’’ በሚል ሃሳብ በዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ተቋም ትናንት ተከብሯል።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና እና ቬተርነሪ ፐብሊክ ሄልዝ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ውብሸት ዘውዴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የእንስሳትን ጤናና ደህንነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻዎች በትብብር መሥራት አለባቸው።

የዓለም እንስሳት ቀን ሲከበር ትኩረት የሚያደርገው የእንስሳትን ደኅንነት ማስጠበቅ ላይ ነው ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ጤናና ደኅንነታቸው ላይ አሁንም ብዙ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።

ደኅንነቱና ጤናው ያልተጠበቀ እንስሳን ለምግብነት መጠቀምም ሆነ ምርታማነቱ እንዲያድግ መጠበቀ አዳጋች መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት የእንስሳትን ጤና፣ ደኅንነትና በሽታ ቁጥጥር እንዲሁም የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌማት ትሩፋት ፕሮግራም በተሠራው ሥራ በእንስሳት ምርትና ምርታማነት ላይ ትልቅ ውጤት መመዝገቡን አንስተው፤ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን የእንስሳት ጤናና ደኅንነት መጠበቅ ይገባል ሲሉ አብራርተዋል።

የምርምር ተቋማት፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎችም ባለድርሻዎች በትብብር በመሥራት የእንስሳትን ጤና ለመጠበቅ መትጋት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ሥራዎችን በሕግ ማዕቀፍ ለመደገፍም የእንስሳት ጤናና ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ ረቂቁ ሲፀድቅ ሙሉ በሙሉ ወደሥራ እንደሚገባ አመላክተል።

የኢትዮጵያ የእንስሳት ጤና ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ቦጃ እንደቦ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ከእንስሳት ጋር የተገናኘ ነው። በመሆኑም እንስሳት ጤናና ደህንነት ላይ መሥራት ከሰዎች ሕይወት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው።

የእንስሳት በሽታዎች ወደ ሰው እንደሚተላለፉ ጠቅሰው፤ የእንስሳትን ደኅንነት መጠበቅ የሰዎችን ጤና የማረጋገጥ አንድ አካል መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

የእንስሳት ጤናና ደኅንነት የሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር ዘርፉ ላይ ትልቅ ክፍተት ፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰው፤ የእንስሳት ጤናና ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ ፀድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ችግሩን ይቀርፈዋል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ አመላክተዋል።

ከአጋር አካላት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን በአግባቡ ለመምራትና የባለሙያዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅም አጋዥ ይሆናል ሲሉ ጠቁመዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You