- ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የገሊላ የጫማ ፋብሪካ ተመርቆ ሥራ ጀመረ
አዲስ አበባ:- ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ሰፊ አበርክቶ ያላቸው የሀገር ውስጥ ማምረቻዎች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
ገሊላ የጫማ ፋብሪካ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን ማምረቻ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ትናንትና አስመርቆ ሥራ አስጀመረ።
በወቅቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ሀብት ማኔጅመንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዓለማየሁ ሰይፉ እንደተናገሩት፤ የሀገር ውስጥ ማምረቻዎች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ የሚረዱ የሕግ፣ የአሠራርና የመሥሪያ ቦታ ድጋፍ እየቀረበ ይገኛል።
እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለጻ፤ ሀገር በቀል ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ ልከው የሚያመጡት የውጪ ምንዛሪ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን እንቅስቃሴ ያቀላጥፈዋል፡፡
ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ጥራቱን ጠብቆ ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱ ማምረቻዎች ለኢኮኖሚው ያላቸው አበርክቶ ለማሳደግ ያግዛል። ወደ ሥራ የገባው የገሊላ የጫማ ፋብሪካ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በመደገፍ ረገድ የራሱ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ሌሎች ሀገር በቀል ድርጅቶችም ወደ ምርት በመግባትና ምርቶቻቸውን በማሳደግ የተጀመረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከዳር እንዲደርስ አስተዋፅዖ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በጫማ ማምረት ላይ የተሠማራው የገሊላ ጫማ ፋብሪካ የቆዳ ምርት የተሻለ ዋጋ እንዲኖረው ያደርጋል ያሉት አቶ ዓለማየሁ፤ በቆዳ ኢንዱስትሪ ውስጥ በመሳተፉ የቆዳ እሴት ሰንሰለት ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ሲሉ ጠቁመዋል።
ድርጅቱ በአጭር ጊዜ ወደ ምርት እንዲገባ ከኮርፖሬሽኑ ድጋፍ ነበር፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪዎች እንዲገቡ አርዓያ ይሆናል ብለዋል፡፡
በርካታ ኢንቨስትመንቶች ወደ ሀገር እንደሚገቡ የገለጹት አቶ ዓለማየሁ፤ ነገር ግን በተለያየ ጊዜና ምክንያት ኢንቨስትመንቶች ተመልሰው ከሀገር ይሸሻሉ፡፡ የገሊላ የጫማ ፋብሪካ ሀገር በቀል ድርጅት በመሆኑ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል ሲሉ አስረድተዋል።፡
በኢንዱስትሪያል ፓርኮች ውስጥ ለሚያለሙ የሀገር በቀል ድርጅቶች ጠንካራ ድጋፍ እንደሚደረግ በመግለጽ ባለሀብቶች እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የገሊላ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ በርሄ እንደገለጹት፤ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው ማምረቻ በሰባት ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ነው፡፡
በቀን ሁለት ሺህ ጥንድ ጫማዎች የማምረት አቅም ያለው ድርጅቱ፤ ለአንድ ሺህ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡ ከሁለት ወር በኋላ የሠራተኞች ቁጥር ወደ አምስት ሺህ በማሳደግ በቀን አራት ሺህ ጥንድ ጫማዎችን ለሀገር ውስጥና ለተለያዩ የዓለም ሀገራት እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።
ኩባንያው የተለያዩ የሕጻናትና የአዋቂ ጫማዎችን ያመርታል ያሉት አቶ አሰፋ፤ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ ኤዥያና በሌሎች ሀገራትም የገበያ መዳረሻዎች መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በመቀሌ የአውቶቡስ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ከፍቶ ለመሥራት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡን አመላክተው፤ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ማምረቻው የበኩሉን ጥረት እያሳደገ እንደሚሄድ አሳውቀዋል።
ሞገስ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም