የ46 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶቹ የመስኖ ልማትን ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና አላቸው

ቢሾፍቱ:- በ46 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በሦስት ክልሎች ውስጥ እየተገነቡ ፕሮጀክቶች የመስኖ ልማትን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና እንዳላቸው የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርታማነት ማሳደጊያና የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮጀክት ላይ ትናንትና ውይይት ተካሂዷል። የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ጊዳቦ፣ በለጪትና ጣባ የመስኖ ፕሮጀክቶች በኦሮሚያ፣ በአማራና ሲዳማ ክልሎች እየተገነቡ ይገኛል።

ፕሮጀክቶቹ ግብርናን ለማዘመን፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ከኢንዱስትሪው ጋር የምርት ትስስር ለመፍጠር አይነተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል። የተለያዩ ማኅበረሰቦችን የሚያስተሳስሩት ፕሮጀክቶቹ በተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማስፋፋት የግብርና ምርትን ምርታማነት ለማሳደግ ያለሙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቶቹ በተለይም የተረጋጋ የንግድ ሥርዓትን ለመፍጠር ከኢንዱስትሪው ጋር ትስስር እንዲኖር የሚያስችሉ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተጨማሪ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘመናዊ ግብርናን ለማሳደግ ይረዳሉ ብለዋል። በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ የአርሶ አደሮችንና ወጣቶችን የግብርና ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለልማቱ መፋጠን አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ጌታሰው መኮንን በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መስኖን በማዘመን ወንዞችንና ግድቦችን ተከትሎ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሠማራት ያለሙ መሆናቸውን አንስተዋል። በፕሮጀክቱ አማካኝነት ሦስት ሺህ ወጣቶች ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁለት ዓመታት ውስጥ ግንባታውን በማጠናቀቅ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል።

በሦስቱ ክልሎች ተግባራዊ የሚደረጉት ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ወጪ 46 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የግብርናውን ዘርፍ ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር የግብዓት አቅርቦትን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በፕሮጀክቶቹ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ልማት ባንክ በኩል ለወጣቶች የቴክኖሎጂና ለእርሻ ግብዓት የሚሆኑ መሣሪያዎች ግዥ የሚውል ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል። ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የሚውሉ የሞተር ሳይክልና ተሽከርካሪዎች ለክልሎችና ለፌዴራል የፕሮጀክቱ አስፈጻሚዎች ተበርክቷል።

በመድረኩ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You