የባሕር በርና ዓለም አቀፍ ሕግጋት

ቀደም ባሉ ዘመናት አንዳንድ የሕግ ሊቃውንቶች በተለይም ውቅያኖሶችና መሰል የውሃ አካላትን በማንም ሀገር ቁጥጥር ስር ሊሆኑ እንደማይችሉና ለማንም ሊሆኑ እንደሚገባ መከራከሪያ አቅርበው ነበር። በዚህ የዓለም አቀፍ ሕግ መርሕ መሠረት የባሕር አካላትን በነፃነት መጠቀም የሚለውን መርሕ ፈጥረዋል።

እ.አ.አ. በ1982 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ ደግሞ ሀገራት የባሕር ክልልና ወሰንን በምን መንገድ መጠቀም እንደሚገባቸው መሠረታዊ መርሆዎችን አስቀምጧል። ሕጉ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሀገራት መካከል የሚገኙ የውሃ አካላትን ጥቅምና ሉዓላዊነትን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል።

ዓለም አቀፍ የባሕር ሕጉ በአንቀጽ 69 የባሕር በር ባለቤት የሆኑ ሀገራት የባሕር በር ከሌላቸው ጋር እኩል የባሕር አካሉን ሃብት የመጠቀም መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስረዳል።

የባሕር በር ሰፊ የሃብት ክምችትን የሚንቀሳቀስበት፣ አንድ ሀገር ከሌላው ጋር በቀጥታ የመርከብ ንግድ ግንኙነት የሚፈጥርበት ምስጢራዊ ዕቃዎችም ሆነ መሣሪያዎችን ለማስገባት የሚረዳ ተፈላጊ የአንድ ሀገር መተንፈሻ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚህ የተነሳ የባሕር በርን ለአንዳንድ ሀገሮች ብቻ የተፈቀደ ለሌሎች ደግሞ የተከለከለ በማስመሰል የሚቀርቡ ክርክሮች በአሁኑ ዘመን ላይ ተቀባይነት እያጡ ይገኛል።

ኢትዮጵያም ካላት የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ዕድገት አንጻር በጂቡቲ ወደብ ብቻ መጠቀም እንደሌለባት ገልጻ፤ ተጨማሪ ወደቦች እንደሚያስፈልጓት ማሳወቋ የሚታወስ ነው። ለመሆኑ ዓለም አቀፍ የባሕር በር አጠቃቀም ሕጎችና መርሆዎች ምን ይላሉ ጉዳዩስ ከሀገሪቷ ሁኔታዎች ጋር ምን ዝምድና ይኖራቸዋል በሚሉ ሃሳቦች ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

የሕግና የአስተዳደር መምህሩ አሮን ደጎል፤ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የባሕር በር ብቻ ሳይሆን ሌሎች የኢኮኖሚ ጥቅም ሊያስገኙ የሚችሉ ነገሮች ካሉም ወደብ ያላቸው ሀገራት የእኔ ብቻ ነው ብሎ መጠቀም ብቻ ሳይሆን በእኩል ደረጃ የማስጠቀም ግዴታም ተጥሎባቸዋል ይላሉ።

በተመድ የዓለም አቀፍ ሕግ አንቀጽ 31 ላይ እንደተመላከተውም የአንድን ሀገር ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ መርከቦች በባለወደብ ሀገራት በኩል ሲያልፉ ሀገራቱ በእኩል ደረጃ መርከቦቹን የማስተናገድ ግዴታ እንዳለባቸውም ግዳጅ ያስቀምጣል ሲሉም ያነሳሉ።

እ.አ.አ. በ1958 የወጣው የጄኔቫ ስምምነት አንቀጽ 03 ወደብ የሌላቸው ሃገራት፣ የባሕሩን አካል የመጠቀም ዕድሉ ካላቸው ሀገራት ጋር በመነጋገር እንዲጠቀሙ መደረግ እንዳለበትም እንደሚደነግግም ነው የሚገልጹት።

እ.አ.አ. በ1965 በተፈረመ ዓለም አቀፍ ስምምነት ደግሞ ወደብ ወይንም የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ምንም አይነት የባሕር በር ሊያገኙ አይገባም የሚል ፍጹም የሆነ ክልከላ መኖር እንደሌለበትም ያስቀምጣል።

በመሆኑም ሶማሊያ፣ ፑንት ላንድ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን በታሪክ አጋጣሚ ወይም በተፈጥሮም ቢሆን የባሕር በር ባለቤቶች ሆነዋል፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ተጠቃሚ እንድትሆን ከእነዚህ ሀገራት ጋር ስምምነት ውስጥ መግባት እንዳለባት ይጠቁማሉ።

ስምምነት ላይ ተደርሶም ምናልባት በስምምነቱ አፈጻጸም፣ ይዘት፣ አተረጓጎም ላይ አለመግባባት ከተነሳ ወይም ደግሞ እኛ አንስማማም፣ ወደብ አንሰጥም ወይም በባሕር በር ኢትዮጵያ እንድትጠቀም አናደርግም ካሉ ደግሞ ሀገራቱ ዓለም አቀፍ ሕግ መጣሳቸው አይቀርም ይላሉ።

በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረትም የባሕር አካላትን በሚመለከት ወደብ ያላቸው ሀገራት ግዴታቸውን ካልተወጡ ወደፍርድ ቤት ይመጣሉ። ጉዳዩንም ወደስምምነት ኮሚሽን ወይንም ዓለም አቀፍ ልዩ ፍርድ ቤት (INTERNATIONAL TRIBUNAL) አምጥቶ ማሸነፍ የሚቻልበት ዕድልም እንዳለ ነው ያመላከቱት።

ስምምነት ካለ መልካም ነው፤ ስምምነት ከሌለና ባለወደብ ሀገራት ግዴታችንን አንወጣም አይነት እምቢተኝነትን ካሳዩ ደግሞ በሕጉ መሠረት ወደዓለም አቀፍ የፍትሕ ተቋማት ሄዶ መብትን ማስከበር እንደሚቻል ይጠቁማሉ።

ሕጋዊ መንገድን ከመጠቀም ውጭ ግን የማስገደድ፣ የጦርነትና መሰል መንገዶችን ዓለም አቀፉ ስምምነት አይደግፈውም፤ አመክንዮም የለውም፤ ይህንንም ኢትዮጵያውያን ይረዳሉ ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የባሕር በር ጥያቄ ማንሳት የመርሕ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን መብትም ጭምር ነው የሚሉት መምህር አሮን፤ ዓለም አቀፉ የሕግ ማዕቀፍ፣ የ1982 የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት፣ የጄኔቫ ስምምነት የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ደጋፊ ሕጎችም የባሕር በር ተጠቃሚነትን የሚያግዙ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያም በባሕር በር ጉዳይ እንደሀገር ያነሳችው የመብት ጥያቄ ነው። መብትን መጠየቅ በሕግ የሚያስጠይቅ ባለመሆኑ የግዴታው ባለቤት የሆነው ሌላኛው አካል የባሕር በር ተጠቃሚነት መብቱን ማክበር አለበት ይላሉ።

ምናልባት በባሕርና በወደብ አጠቃቀም አለመግባባቶች ቢያጋጥሙ ግጭቶች ወይም አለመግባባቶች ቢያጋጥሙ የሚፈታበት ሕግ ስላለ በጎረቤት ሀገራት የሚነሱ ስጋቶች አላስፈላጊ መሆናቸውን ያነሳሉ።

የ1982ቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባሕር ሕግን የሚደነግገው ስምምነት አንቀጽ 279 እና ተከታዮቹ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ማስቀመጡን ይገልጻሉ። ለአብነት አንዱ ዘዴ በሚኖረው የእርቅና የስምምነት ኮሚሽን መሠረት ይፈታል። በዚህ ካልተፈታ በየደረጃው እየታየ እስከ ዓለም አቀፉ የፍትሕ አካል የሚሄድበት ሁኔታ ይኖራል። ወይንም ለዚህ ዓላማ ብቻ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጡ አካላት ሊቋቋሙም ይችላሉ። በተቻለ መጠን ከሀገራት ጋር በሕግ፣ በስምምነት እንዲፈቱ የሚያበረታታ ነው ይላሉ።

የስምምነት ኮሚሽኑ መጨረሻ ላይ የሚያቀርበው ሪፖርት ገዢ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን መመሪያ አሊያም አቅጣጫ ያስቀምጣል። ነገር ግን ወደጦርነትና ግጭት የሚሄድበት አግባብ እንደማይኖር ሕጉ ይደነግጋል ሲሉ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመችው አይነት የወደብ ተጠቃሚነትን የሚያሰፋ ስምምነት ከሌሎች ሀገራት ጋርም መቀጠል እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ የምጣኔ ሀብት ምሑሩ ቆስጠንጢኒዮስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) ናቸው።

የመግባቢያ ሥምምነቱ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ኩነት ነው፤ ዓለም አቀፍ ሕግጋት የሚደግፉትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ መሠረት ያደረገ በመሆኑ ኢትዮጵያን በተመድ ጉባኤዎች ላይም በስፋት አንስታ ልትጠይቅበት የምትችልበት አግባብ መኖሩን ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያ እራሷ የምታለማው ወደብ ሲኖራት፣ የሸቀጥ ዕቃዎችን ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ሰፊ አማራጭ ያስገኝላታል። ይህም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሶማሌላንድም የገቢ ምንጭ ይኖረዋል ይላሉ።

ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ በሠላምና ደኅንነት ዘርፍ ያላትን አዎንታዊ ሚና ይበልጥ እንድታጠናክርም ዕድል ይሰጣታል፤ በመሆኑም ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በማጣቀስና ሀገራትን በዲፕሎማሲ በማግባባት ቀጣይነት እንዲኖረው መሥራት ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ።

ዘላለም ግዛው

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 / 2017 ዓ.ም

Recommended For You