አንዳንዴ ያለችበት፣ ኑሮና የምታሳልፈው ውጣውረድ ከልብ ያስከፋታል። ይህኔ አንገቷን ደፍታ ትቆዝማለች። አልፋ የመጣችው የህይወት መንገድ፣ ወድቃ የተነሳችበት ሜዳና አቀበት ውል እያለ ይፈትናታል። እሷ ሁሉንም ላስብ ካለች መውጫ መንገዷ ሰፊ አይደለም። ከአጣብቂኝ ገብታ ትጨነቃለች። በጥልቅ ሀሳብ ትሰምጣለች።
እጅግ ተከፍታ ባዘነች ቀን ተስፋ መቁረጥ አሸንፏት ያውቃል። ሁሌም እንዴት ለምን እያለች ፈጣሪን መወትወቷ መልስ አልሆናትም። ዞር ብላ የሆነውን ስታስብ፣ የምትይዘው፣ የምትጨብጠው ይጠፋታል። እንዲህ በተሰማት ግዜ ገመድ ይዛ ጣራና ዛፍ የፈለገችባቸው ቀናት ብዙ ናቸው። ደግነቱ ስለሁሉም ፈጥና አትወስንም። አለፍ ብላ ስለልጆቿ ዕጣ ፈንታ ታስባለች። ምን እንደሚገጥማት አይጠፋትም። በተለይ ህጻኗ ታሳዝናታለች። ውስጧ ተረጋግቶ መለስ ሲልላት የገፋፋት ክፉ ስሜት ትቷት ይሄዳል።
ትዝታን እንደማምለጫ…
ትዕግስት ለማ ይህ አይነቱ ስሜት ተመላልሶ ሲፈትናት ተሸንፋ እጅ ላለመስጠት ከራሷ ጋር ትስማማለች። በሀሳብ አርቆ የሚወስዳት መልካም ትዝታ ከልጅነት መንደሯ፣ አዝልቆ ከወላጆቿ ጉያ ይወሽቃታል። ይህኔ መንፈሷ ወደ ማንነቷ ይመለሳል። የእናት አባቷ ድምጽ መድሀኒቷ ሲሆን ይሰማታል። ፍቅር በዚህ ግዜ የልጅነት ቡረቃዋ መድህኗ ነው። ርቃ የሄደችበት ትዝታ ሰምጣ ከገባችበት ጥልቅ ጉድጓድ አውጥቶ በጽናት ያቆማታል። ሁሌም ልጅነቷን ማስታወስ ከክፉ ሀሳብ የማምለጫ መንገዷ ነው። ትዝታዋ ያድናታል። ዕንባዋን እያበሳች በፈገግታ ትሞላለች። ልጅነት አዋቂነቷን አሸንፎ ድል ያደርጋታል። ክፉ ሀሳቧ በበጎ ተለውጦ ራሷ ስለነገ ሲያስብ፣ ሲያቅድ ታገኘዋለች።
ልጅነት…
ትዕግስትና የልጅነት ግዜ የሚተያዩት በክፉ ትውስታ አይደለም። ሁሌም ይህ ግዜ ለእሷ የመልካምነት ትዝታዋ ነው። እናት አባቷ፣ እህት ወንድሞቿ፣ ሀገርና ቀዬው ሁሉ ዛሬ ድረስ ውል ሲሏት በፈገግታ፣ ደስ በሚል ስሜት ታወሳቸዋለች። ልጅነት ለእሷ የክፉ ስሜት ማምለጫዋ ነው። ያለፈውን መልካምነት ስታስብ፣ ስታስታውስ ሁሉን ትረሳለች።
‹‹ሽላላካ ››ከውቅሮ ከተማ አለፍ ብላ የምትገኝ የገጠር መንደር ነች። በዚህች መንደር ትዕግስት ፍቅርና ደስታን ሸምታ፣ በደስታ አሳልፋለች። ገና በልጅነቷ ወላጅ እናቷን በሞት ባጣች ግዜ ሽማግሌው አባቷ ልጆች የማሳደግ ሀላፊነት ወደቀባቸው። ለእሳቸው ይህ ክፉ አጋጣሚ ፈታኝ ነበር።
አባት በግዜው መፍትሄ ያሉት እሷን ወደተሻለ አካባቢ ልኮ ማሳደግና ማስተማርን ነበር። ዕድሜያቸው ገፍቷል። በእሳቸው አቅምና ሀሳብ ልጆችን እንደፍላጎታቸው ማድረግ ይከብዳቸዋል። እንዲያም ሆኖ ሁሉንም ቁምነገር አድርሰው ቦታ ማስያዝ ያስባሉ። በወቅቱ ስለትዕግስት ያቀዱት ወደደተሻለ ቦታ ልከው ማሳደግና ማስተማርን ነበር።
አዲስ አበባ የሚኖሩት የትዕግስት አጎት እሷን ተቀብለው ለማስተማር ፈቅደዋል። ከዚህ በኋላ ስለትንሿ ልጅ ማንም አያስብም። ትዕግስት አዲስ አበባ በአጎቷ ቤት እየኖረች ገብታ ትምህርት መማር ጀመረች። ልጅነቷን ከሽላላካ መንደር ብትተወውም ትዝታው ከእሷ አልራቀም። ክፉ ስታስብ በበጎ እየመለሳት ወጣትነቷ ላይ አድርሷታል።
እንደታሰበው ሆኖ ጥቂት ዓመታትን በትምህርት ዓለም ገፋች። አባት እንዳሰቡት እሷም እንደሞከረችው ሆኖ ከጥግ አልደረሰችም። እህል ውሀ ይሉት እውነት ከትዳር አጋር አገናኝቶ ጎጆ ቀለሰች። ትዳር መስርታ ቤቴን ማለት ስትይዝ የትምህርቱ ጉዳይ ቀርቶ ራሷን የምታግዝ፣ ቤተሰቧን የምትመራ ሆና ተገኘች።
ሶስት ጉልቻ…
አሁን ትዕግስት ባለትዳር የቤት እመቤት ነች። ባለቤቷ ተሯሩጦ አዳሪ ነው። ለፍቶ በሚያመጣው ገቢ እሷንና አንዷን ልጃቸውን በወጉ ያሳድራል። እሷም ብትሆን የባሏን እጅ አይቶ ማደሩ በቂ አለመሆኑን ታውቃለች። በአቅሟ ከከፈተቻት ሻይ ቤት እየሰራች ቤት ጎጆዋን ትደጉማለች፤ ልጇን እንደፍላጎቷ አሳድራ ከትምህርት ታውላለች።
አሁን ባለቤቷና እሷ ኑሯቸው ቢሾፍቱ ላይ ሆኗል። ሁለቱም በህይወታቸው ደስተኞች ሆነዋል። በላብ በወዛቸው የቆመው ጎጆ ፍቅር የሚመነጭበት መተሳሰብ የሚታይበት ነው። እሷ ከህይወት ልምዷ ብዙ ተምራለች። ተራምዳው የመጣችበት መንገድ አያልፍ በሚመስል ፈተና የተሞላ ነበር።
ወይዘሮዋ ብርቱና ጠንካራ ነች። ሁሌም ራሷን ለማሸነፍ፣ ትዳሯን ለመምራት ሌት ተቀን ትለፋለች። የመጀመሪያ ልጇን በወጉ እያሳደገች ማስተማሯ የህይወቷ ስኬት፣ የልፋቷ ውጤት ነው። ከፊቷ የማይጠፋው ፈገግታ ነገን በመከፋት እንዳትሻገር አግዟታል። ሁሌም የውስጥ ሰላሟ ተናግቶ አያውቅም። ደንበኖቿን በወጉ ታስተናግዳለች። ቤቷን በአግባቡ ትመራለች።
አሁን ትዕግስት ነፍሰጡር መሆኗን አውቃለች። ጠዋት ማታ በስራ ብትተጋም። ህመም ተሰምቷት አታውቅም። በፊቷ የሚፍለቀለቀው ፈገግታ ሰላም ደስታዋን ይመሰክራል። እርግዝናዋ አይረብሻትም። ሁሌም ያሻትን፣ ያማራትን ትበላለች። በየግዜው ከሚኖራት የእርግዝና ክትትል አቋርጣ አታውቅም። በአግባቡ በቀጠሮዋ ተገኝታ ግዴታዋን ትወጣለች።
የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ባገኟት አጋጣሚ ስለጤንነቷ፣ ስለለጽንሱ ደህንነት ይነግሯታል። በፍጹም ደስታ የሚሏትን ሰምታ ትመለሳለች። ሁሌም የሀኪሞችን ምክር አታጓድልም። ‹‹አድርጊ›› ያሏትን ትፈጽማለች። የተከለከለችውን ትተዋለች። የሁለተኛ እርግዝናዋ ቀለል ያለ ነው። ይህን ስታስብ የነገውን ታስባለች። ነገ ለእሷ መልካም ይሆናል። ዛሬን ስታልፍ በጎነት ይታያታል። ይህኔ ራሷን አሸንፋ ኑሮዋን ታግላ ለመቆም ብዙ ታቅዳለች።
ከገና ማግስት …
ታህሳስ እንደጀመረ ከሆስፒታል መመላለስ ያዘች። ወሯ ስለገባ ክትትሏ ይበልጥ ቀጥሏል። በዚህ ወር መጨረሻ እንደምትወልድ አውቃለች። እንደ አራስ ለጎኗ የሚሆነውን፣ ለጠያቂ እንግዶቿ የሚያስፈልገውን አሟልታለች። የገናን በዓል እሷና ቤተሰቦቿ በሰላም አሳልፈዋል። ቀኑ ባለፈ በማግስቱ ወይዘሮዋ ከሆስፒታል ተገኘች። የአሁኑ ምክንያት እንደቀድሞው ለክትትል አልነበረም።
በጥቂት የምጥ ቆይታ በሰላም ሴት ልጅ የታቀፈችው ወይዘሮ በምስጋና ፈጣሪዋን አስባለች። አሁን የምታስበው ቤቷ ደርሳ የምታደርገውን ማሰብ ብቻ ሆኗል። አዋላጆቿ ህጻኗን አምጥተው ከማሳቀፋቸው በፊት ጠጋ ብለው እናቲቱን አወጉ። ህጻኗ ቀላል የሚባል የጤና እክል ታይቶባታል። ችግሩ በህክምና ታክሞ የሚድን በመሆኑ ከሆስፒታሉ ቆይታ ክትትል ማድረግ ይኖርባታል።
የተባለችውን በአግባቡ ያደመጠችው እናት ከሀኪሞቹ ትዕዛዝ አልወጣችም። ህጻኗን መርፌ አስወግታ የሚሆነውን በእርጋታ ጠበቀች። ማግስቱን ቤቷ የገባችው ትዕግስት ከአንድ ቀን በላይ አልቆየችም። ከሀኪሞች የተጻፈላትን የአስቸኳይ የህክምና ማዘዣ / ሪፈር/ ይዛ ወደ አዲስ አበባ አቀናች። አዲስ አበባ የደረሰችበት ሆስፒታል ህጻኗን ለመቀበል አልዘገየም። በጀርባዋ ለታየው ክፍተት መፍትሄ ለመስጠት በተወለደች በአምስተኛ ቀኗ አስቸኳይ ቀዶ ህክምና አደረገላት።
የጥያቄው መልስ …
ትዕግስት ባልተለመደ ሁኔታ ያጋጠማትን ችግር ለማወቅ ጥያቄ ማቅረቧ አልቀረም። የልጇ የጤና ችግር የነርቭ ዘንግ ክፍተት መሆኑ ተነግሯታል። ይህ ክስተት በእርግዝና ግዜ የፎሊክክ አሲድ እጥረት ሲኖር የሚያጋጥም ነው። ትዕግስት ቀላል ነው የተባለለት የልጇ ጤና እንደገመተችው አልሆነም። ቀናትን በሆስፒታሉ አሳልፋ ወደቤቷ ተመለሰች።
ከጥቂት ጊዚያት በኋላ በነበራት ቀጠሮ ወደ ሆስፒታሉ መምጣት ነበረባት። አሁን ደግሞ በህጻኗ ጭንቅላት ውስጥ ለሚታየው የተጠራቀመ ውሀ ተጨማሪ ቀዶ ህክምና መደረግ አለበት። በጭንቅላቷ ‹‹ሻንቲ››የተባለ ማገዣ ከገባለት በኋላ በሌላ ቀጠሮ ወደቤቷ ሄደች። ከሁለት ወር በኋላ ተመልሳ ስትመጣ ተመሳሳይ የህክምና እገዛ ማድረግ ግድ ብሎ ነበር።
ፊዶሪያ… ድል መንሻዋ ብላቴና
አሁን ሁሉም ነገር ተጠናቆ ህይወት ወደቀድሞው ተመልሷል። ትዕግስት ግን አብሯት የኖረው ጥንካሬ ከእሷ የለም። ትካዜዋ በዝቷል። ሀዘኗ ከፍቷል። ለምን ? እንዴት? በሚለው ጥያቄ ከራሷ ጋር ስትወዛገብ ታድራለች። ታቅፋት የምትውለው ህጻን ውብና አሳዛኝ ናት። ባየቻት ቁጥር ውስጧ ይላወሳል። በዚህች ህጻን ብዙ አይታለች። በሆነባት ሁሉ ከፍቷት፣ አዝና ተስፋ ቆርጣ በራሷ ልትወስን የሞከረችባቸው ቀናት ጥቂት አይደሉም። አሁን ግን በዚህች ልጅ ፍቅር ተሸንፋ እጅ ሰጥታለች።
‹‹ፊዶሪያ›› ስትል የሰየመቻት ሁለተኛ ልጇ ማንነቷ እንደ ስያሜዋ ሆኗል። ፊዶሪያ ማለት ‹‹ድል ነሳሁ፣ አሸነፍኩ›› እንደማለት ነው። ትዕግስት በልጇ ብዙ መከራና ስቃይ አይታለች። በዚህ ፈተና ግን ተንገዳገደች እንጂ አልወደቀችም። ጽናቷ በርትቶ ዛሬን ለመቆም ምክንያቷ ይህች ብላቴና ነች። ፊዶሪያ ለእሷ የብርታት ጥንካሬዋ፣ ማሳያ፣ የአሸናፊነቷ መለኪያ ሆናለች። የዛሬን ጀንበር ደፍራ ለማየት ምክንያት ሰበቧ እሷው ናትና ለፈጣሪ ምስጋና ከማድረስ አትቆጠብም።
ልጇ ከእነአባቷ በሙሉ ስም ስትጠራ ስያሜዋ ለየት ይላል። ‹‹ፊዶሪያ ጀርመን ። ›› ፊዶሪያ የልጅቷ፣ ጀርመን ደግሞ የአባቷ ስም መሆኑን የሚሰሙ ሁሉ ግኝቷ ከውጭ ሀገር ስለመሆኑ ይጠራጠራሉ። በርካቶች እንዲህ ይበሉ እንጂ የፊዶሪያ ጀርመን ውልደትና ዘር ካገር ቤት የተቀዳ ነው። ፊዶሪያ ይሉትን ትርጓሜ ይበልጥ ውስጧ የሚያውቀው እናት ደግሞ በዚህ ድንቅ ስም ማንነቷን ታይበታለች።
የዛሬን አያድርገውና..
ቆንጆዋ ፊዶሪያ ለእሷ ሁሌም መስታወቷ ነች። ህይወቷን የምታይባት፣ ማንነቷን የምትገልጽባት፣ ጥንካሬዋን የምታስመሰክርባት መገለጫዋ። እናት ትዕግስት የዛኔ የልጇን ጤና ካወቀች በኋላ እውነታውን አምኖ ለመቀበል ጊዜያትን ፈጅታለች። ለምንና እንዴት በሚሉ ጥያቄዎች ተወዛግባ ራሷን የጎዳችባቸው፣ በአጉል ውሳኔ የተፈተነችባቸው ቀናት ጥቂቶች አይደሉም። ዛሬ ያለፈውን ታሪክ ስታስብ በእጅጉ ይገርማታል። በክፉ መንገድ አልፋ፣በሀሳቧ ወስና ቢሆን የልጇ ህይወት አደጋ ላይ በወደቀ ነበር።
ፊዶሪያ ዛሬ ሰድስት ዓመት ሆኗታል። ከእናቷ ጋር ያላት ቅርበት የቁምነገር ብቻ ነው። አስተሳሰቧ እንደ ዕድሜዋ አይደለም። የምታስበው፣ የምትጨነቀው እንደአዋቂዎች ሆኗል። የእናቷን ደስታና ሀዘን የምታውቀው ገጽታዋን አይታ ሁኔታዋን ተረድታ ነው። ከእሷ ጋር የህጻን ጨዋታና ቀልድ አይታሰብም። ልጅ ብትሆንም እንደወላጅ ታስባለች፤ እንደእናት ትጨነቃለች።
ለትዕግስት ሁሌም ከፊዶሪያ አንደበት የሚወጣው ቃል ያስደነግጣታል። ቤተክርስቲያን አዝላት ስትሄድ ልጅ የጸሎቷን ቃል ታዳምጣለች። ለፈጣሪ የምታቀርበው ምልጃና ልመና ምን እንደሆነ አይጠፋትም። አንዳንዴ ፊዶሪያ ከእናቷ ጀርባ ሆና ስጋት ይይዛታል። እናት ስለእሷ እየተማለደች እያዘነች መሆኑ ሲገባት በሚጢጢ እጆቿ የእናቷን ፊት ዳብሳ ማልቀስ አለማልቀሷን ታረጋግጣለች። ሁሌም ቢሆን ‹‹አይዞሽ፣አለሁልሽ›› ብላ ከማጽናናት ዝም አትልም።
የእናት ትከሻ …
ትዕግስት ፊዶሪያ ‹‹ከፈጣሪ መታረቂያ ሰበቤ ናት››ብላ ታስባለች። የቀድሞ ስህተቷን ያረመችው በእሷ ነው። ሁሌም ስለደህንነቷ የሚያገባት እሷ ብቻ መሆኗን ታውቃለች። በህይወት መቆሟ ደግሞ ለልጇ ህልውና እንደብረት አጥር ነው። ሁሌም እንደምትለው እሷ ለልጇ ጠበቃዋ ነች። በምትሄድበት መንገድ ሁሉ ጥላ ከለላ ሆና ታኖራታለች። ያለፈው ታሪክ ዛሬ በ‹‹ነበር›› ቢወሳም። ህመሙ የመላው ቤተሰብ ሆኖ አልፏል።
ዛሬ ግን ይህ እውነት ተቀይሮ ጥንካሬ ነግሷል። እናት ለልጇ መኖርን በተግባር እያሳየች ነው። ፊዶሪያ እንደ እኩዮቿ ትምህርት ቤት ከገባች ወዲህ ትዕግስት በቻለችው አቅም ዊልቸር አዘጋጅታለች። ህጻኗ ራሷን ችላ ለመጠቀም አለመድረሷና ግን ኃላፊነቱ ከእሷ አልወጣም። እናት ሁሌም ስለልጇ ደክሟት፣ ሰልችቷት አያውቅም። ዘወትር ጠዋት ማታ በትከሻዋ አዝላ ታመላልሳታለች።
ፊዶርያ በህይወት እስካለች የዳይፐር ተጠቃሚ መሆኗ ግድ ነው። ዛሬን ትምህርት ቤት ብትውልም አብሯት ያለው ችግር ከእሷ የሚለይ አይሆንም። በኪራይ ቤት ህይወት ፣በኑሮ ውድነት ጫና ይህን መሰሉን እውነት ተቋቁሞ መዝለቁ እጅጉን ይከብዳል። የሰፈሩ አለመመቸት፣የቤቱ መጥበብና ከመጸዳጃው ጥግ መሆን ህይወትን ይፈትናል። እናት ትዕግስት ‹‹ለላም ቀንዷ አይከብዳት›› ሆኖ ሁሉን እንደአመጣጡ ተቀብላዋለች።
ሁሉን በሆዷ…
አንዳንዴ ስለልጇ አርቃ ስታስብ ብዙ ጉዳዮች ያስጨንቋታል። ይህ ስሜቷ እንዳይታወቅ በውስጧ መያዝ ፣ማመቅን ለምዳለች። ማልቀስ ካለባት በልጇ ፊት አታደርገውም። ዞር ብላ ዕንባዋን ጨርሳ በፈገግታ ትመለሳለች። ባለቤቷ ዛሬ በቂ ይሉት ስራ የለውም። ፊዶሪያ ከተወለደች በኋላ ውስጡ ተጎድቷል። የእሷ ህመም ችግር እኔ ነኝ ብሎ እያሰበ ነው። ሁሉም መከራ በእርሱ ሰበብ እንደመጣ በማሰቡም ገለልተኝነት ከታየበት ቆይቷል። ባልና ሚስት በአንድ ታዛ ስር ይኖራሉ። እንደባልና ሚስት ባይሆኑም ኑሮና ህይወትን በእኩል እየተጋሩት ነው።
ትዕግስት በባለቤቷ ላይ ያደረውን ዕምነት ማጣት ከፍራቻና ጸጸት ቆጥራ ሀሳቡን አክብራለች። ከዚህ ባሻገር ግን የፊዶሪያ ጉዳይ ሁሌም አብዝቶ ያስጨንቃታል። ዛሬም ሮጣና ተባራ የምታመጣው ጥቂት ገንዘብ ከልጆቿ ዕለት ጉርስ የሚያልፍ አይደለም። ከቀን ስራና በቆሎ ከመሸጥ የሚመጣ ገቢ ቆጥባ ያስቀመጠችው አንዳች ጥሪት የለም።
የመጨረሻው ውሳኔ …
እናት ከባዱን የኑሮ ጫና ባሰበች ቁጥር የፊዶሪያ ዕጣ ፈንታ ውል ይልባታል። እሷ ከማንም የበለጠ ፍቅርና ትኩረት ትሻለች። በአንድ አጋጣሚ ቢለያዩ የሚደርስባት ጉዳት ያሳስባታል። ድንገት በሞት ስለመለየት ስታስብ ደግሞ ብዙ የእሷ አይነት ልጆች ያሏቸው እናቶች እንደሚሉት ሆና አትናገርም።
እነሱ ከራሳቸው በፊት በአንዲት ደቂቃ ልዩነት ልጆቻቸው ቢቀድሙላቸው ይወዳሉ። እሷ ደግሞ አይቀሬው ሞት ቢመጣ ሁለቱም በአንድ ሸለብታ በአንድ ቀን ፣በአንድ ደቂቃና ሰከንድ በእኩል ቢሞቱ ምርጫዋ ይሆናል። ይህ የመጨረሻ ውሳኔዋ ነው። ወይዘሮ ትዕግስት የፊዶሪያ እናት።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም