መጪውንም ትውልድ ታሳቢ ያደረገው የኮሪደር ልማት

ከተማን መልሶ የማልማት ተግባር ከተማ ነክ ችግሮችን ለማቃለል፣ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻልና የተፋጠነ የከተማ ለውጥና ብቃት ያለው የመሬት አጠቃቀምን ማስገኘት ታስቦ የሚፈፀም መሆኑን የከተማ ፕላን አዋጅ ቁጥር 574/2000 ያመላክታል፡፡ አዋጁ የከተማ እድሳትን፣ ማሻሻልን፣ የመሬት እንደገና ድልደላንም ያካትታል። ከተሞች የአስተዳደሮቻቸውን፣የነዋሪዎቻቸውንና የአልሚዎቻቸውን ተነሳሽነት ተከትለው መዋቅራዊና የአካባቢ ልማት ፕላኖችን መሠረት በማድረግ እንደገና እንዲለሙ ስለማድረግ አስፈላጊነትም አስፍሯል።

በአዋጁ መሠረት ከተማን የማደስ ተግባር በአንድ ከተማ የሚታዩትን የፈራረሱ፣ ያረጁና የተተዉ መዋቅሮችን በከፊል ወይም በሙሉ በማስወገድ ምቹ የመኖሪያና የሥራ አካባቢ በመፍጠር ዓላማ ላይ አተኩሮ የሚፈጸም ተግባር ነው፤ ለዚህም የከተማ እድሳት ይከናወንበታል ተብሎ በታሰበው አካባቢ የሠፈሩ ነዋሪዎች እድሳቱ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በቅድሚያ ስለሁኔታው እንዲያውቁና እንዲመክሩበት ይደረጋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያካሄደ ባለው የኮሪደር ልማትም ይሄው እየተከናወነ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኮሪደር ልማቱ ቀዳሚውን ትኩረት ለሰዎች በመስጠት፣ መጪውን ትውልድ ጭምር ታሳቢ በማድረግ እየተከናወነ ስለመሆኑም ይገለጻል፡፡

ከሰሞኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎቹ ሕይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ዘመቻ በጀመረበት የአንደኛው ዙር የኮሪደር ልማት አፈፃፀም ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከማኅበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር ተወያይቷል። በመድረኩ የኮሪደር ልማቱ ሥራ አፈፃፀም፣ ጠንካራ ጎኖችና ጉድለቶች እንዲሁም በቀጣይ በምን መልኩ መሥራት ይገባዋል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ጽሑፍም ቀርቧል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ አዲስ አበባን ለማዘመን እንዲሁም ፅዱ፣ ውብ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ለማድረግ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ዋነኛ ዓላማ መዲናዋን እንደስሟ ውብ አበባ ማድረግን ያለመ ነው፡፡ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ ማድረግ የሚቻለውም መሠረተ ልማቷ በተሟላ ሁኔታ ሲገነባ፣ ያሉት መሠረተ ልማቶቿም ሲታደሱ፣ ከተማዋ ስትታደስ እና ነዋሪዎቿ ምቹ መኖሪያ ቤት እና አካባቢን ሲያገኙ ነው።

‹‹የኮሪደር ልማቱ የሚካሄደው ለዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድም ጭምር ነው›› ያሉት ከንቲባዋ፣ ከተማዋ የዛሬ ብቻ ሳትሆን የወደፊት ከተማም መሆኗን አስገንዝበዋል። ዛሬ ለነዋሪዎቿ ምቹ አድርገን ስናለማት ወደፊት የሚመጡት ሕጻናት በደስታ ቦርቀው፣ በጥሩ አየር እና ንጹሕ አካባቢ ላይ የተገነባ መጫወቻ አግኝተው የሚያድጉባት ልትሆን እንደሚገባም አመልክተው፣ ይህም ከትውልድ ግንባታ ሥራዎች አንዱና መሠረታዊ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከንቲባዋ እንደተናገሩት፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው ንጹሕ መኖሪያና መዝናኛ፣ የጋራ መጠቀሚያና መገልገያዎችን ማግኘት አለባቸው። ከተማዋ የሀብታሞች መኖሪያ ብቻ ሳትሆን የድሆችም ናት፤ ሁሉም እኩል ሊዝናኑባት ይገባል፡፡ የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚሳለጥባት፣ ባለመኪናው የተሻለ የተሽከርካሪ መንገድ እንደልብ ሊያገኝ የሚችልባት እንድትሆን ማድረግ ያስፈልጋል፤ እግረኛውም ከመኪና ጋር ሳይጋፋ፤ የአደጋ ስጋት ሳይኖርበት በእግሩ መጓዝ የሚችልበትን ዕድል መፍጠር፣ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች መሥራት ይገባል።

በኮሪደር ልማት ላይ በተደጋጋሚ በብዙኃን መገናኛዎች ማብራሪያዎች መስጠታቸውን ከንቲባዋ አስታውሰው፣ ይሁንና መረጃዎች በተሟላ መልኩ ለሕዝቡ ደርሰዋል፤ ሁሉም ሰው እኩል ተረድቷል ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል፤ ከኮሪደር ልማቱ ዓላማ ውጪ የሆኑ የተዛቡ መረጃዎች እየወጡ ያሉበት ሁኔታም ይህንኑ እንደሚያመለክት ጠቅሰው፣ ከተማ አስተዳደሩ በጉዳዩ ላይ መወያየት ያለበት መሆኑ ተገቢ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ በበኩላቸው የከተማዋን ገፅታ እየቀየረ ባለው የኮሪደር ልማት ፋይዳ ላይ ያተኮረ የውይይት መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል። በጽሑፋቸውም የኮሪደር ልማቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቅቆ ሁለተኛው የኮሪደር ልማት ምዕራፍ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

መዲናዋ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ የሚሻገሩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶችን ማስመዝገቧን ጠቅሰው፣ በኮሪደር ልማቱ የከተማ ማደስ፣ የከተማ ማልማት፣ እንደገና የመገንባት ዓላማና የቀደሙ ልምምዶችን ታሪካዊ ዳራ አስመልክተው አብራርተዋል።

አቶ ጥላሁን እንዳስታወቁት፤ መዲናዋ በፕላን ያልተመሠረተች፣ አብዛኛው ነዋሪዋ በሰነድ አልባ የሚኖርባት፣ በሰፈራ መልክ ያለች፣ ስሟ እና ግብሯ የማይመጥን ከተማ ሆና ቆይታለች። ይሄንንም ለመቀየር የየዘመናቱ መሪዎች የየራሳቸውን ጥረት አድርገዋል።

በ1928 ዓ.ም በጣሊያን አገዛዝ፣ በ1948 ዓ.ም ከብር ኢዮቤልዩ፣ በ1955 ዓ.ም ከአፍሪካ አንድነት ምሥረታ ጀምሮ እስከ አብዮቱ ድረስ፤ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በልደታ እና በካዛንቺስ መልሶ ማልማት ከተማዋ ሕዝቧን የምትመጥን አሕጉራዊ ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዋን የምትወጣ እንድትሆን ለማድረግ ጥረት ተደርጓል።

የአሁኑ የኮሪደር ልማት ከተማዋ የምትታደስበት፣ የምትዘምንበት፣ የከተማዋ ስምና ግብር የሚገናኝበት፣ ከተማዋ ለሕዝቦቿ ምቹ የምትደረግበት ነው። ከተሞች ግዑዛን ውቅሮች ሳይሆኑ፣ በሰዎች የሚመሠረቱ፣ ሰዎች አቅደው በዲዛይን የሚገነቧቸው ሥነሕይወታዊ ውቅሮች ናቸው ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ከተሞች ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይሞታሉ ሲሉም ገልጸዋል።

ባለፉት ጊዜያት የነበሩት ጥረቶችም ሆኑ የአሁኑ የኮሪደር ልማት ከተማ ከመሞቱ በፊት ሕይወት እንዲዘራ የሚደረግባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የኮሪደር ልማቱ የደቀቁ፣ ገፅታቸው በጣም የተበላሹ፣ የዜጎችን ክብር የማይመጥኑ የከተማዋን ክፍሎች አዲስ ገፅታ በማልበስ ማልማትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለልማቱ አንዱ መነሻ ዜጎች በንጹሕ፣ ለኑሮ አመቺ በሆነ ከተማ የመኖር ሕገመንግሥታዊ መብት መሆኑን ተናግረው፣ አዲስ አበባን እንደስሟ የነዋሪዎቿን ክብር የሚመጥን ምቹ እና ፅዱ ለማድረግ ለሕዝብ የተገባው ቃልም ሌላው መነሻ መሆኑን አመላክተዋል።

የኮሪደር ልማቱ በላቀ ደረጃ ዓለም የደረሰበትን የስማርት ከተማ እቅድ የምታሟላ ከተማ ለመገንባት ታሳቢ ተደርጎ እየተካሄደ ነው ሲሉም አስታውቀዋል። ከተማን በማደስ ዓለም አቀፍነትን፣ ሳይንሳዊነትንና ከተማን በማደስ ሊመጡ የሚችሉ ትሩፋቶችን ታሳቢ አድርጎ የሚከናወን ስለመሆኑም አንስተው፤ በማፍረስ፣ ማደስ፣ ማስተካከል፣ ወዘተ ላይ በቂ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮ ተወስዶ እየተሠራበት ያለ መሆኑንም አብራርተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በመዲናዋ የመጀመሪያው ዙር ኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬት ተመዝግቧል፤ ይህም ሊሆን የቻለው የሁሉም ጥረት ታክሎበት እና የሀገራችን መሪዎች የከተማዋ ከንቲባና ከፍተኛ አመራሮች፣ ለስኬታማነቱ ሌት ተቀን በመትጋታቸው ነው።

የልማት ተነሺዎች የሚስተናገዱበት አሠራር ተዘርግቶ፤ የልማት ተነሺዎችን በማወያየት በኃላፊነት ተሠርቷል። ባለፉት አንድ ዓመታት በቅንጅትና በኃላፊነት በተሠራው የኮሪደር ልማት ሥራ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች ሕይወት የተቀየረ መሆኑንም አስታውቀዋል።

አቶ ጥላሁን፤ የኮሪደር ልማት ሥራው የመጨረሻው ግብ ሰው እና ሰው ነው፤ የዜጎች ሁለንተናዊ፣ አዕምሯዊ፣ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ ብልፅግናቸው እንዲጠበቅ መሥራት መሆኑን ይገልጻሉ። አዲሱ ትውልድም የሕይወቱ ልምድ አድርጎት እንዲቀጥል ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የልማት ተነሺዎችን ሊጎዱ ይችላሉ የተባሉ በርካታ ሕጎችን በማሻሻል ጭምር የመዲናዋ ካቢኔ በርካታ ውሳኔዎችን ማሳለፉንም አመላክተዋል።

ለረጅም ጊዜ በገበያ ማጣትና በሥራ መፋዘዝ ሲቸገሩ የነበሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራትን ተጠቃሚ ማድረጉም ከኮሪደር ልማቱ ትሩፋቶች መካከል የሚጠቀሰው መሆኑን ተናግረው፣ መንገድ ዳር ያሉትን የሕንጻ እድሳት ሥራዎችና አጥሮችን የሠሩት፣ የአረንጓዴ ሥራዎችን የገነቡት በትልልቅ ኮንትራክተሮች ሳይሆን በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሁሉ ሂደት በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በርካታ የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸው፣ በኮንስትራክሽን ግብዓት ኢንዱስትሪው ላይ እጥረት እስኪፈጠር ድረስ ከፍተኛ መነቃቃት መታየቱን፣ በርካታ ማሽነሪዎችን ማስገባት፣ ብዙ ምርቶችን ሌት ተቀን ማምረት እንደ ልምድ መወሰዱን ጠቅሰዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማቱ ሂደት የመሪ ሀሳብ አመንጪነት እና መስጠት ለሀገር ለውጥ አስፈላጊ መሆኑ በጥንካሬ መለየቱንም ኃላፊው አስታውቀዋል። ስኬቱ ሕዝብን አስተባብሮ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ዋናው የስኬት ምንጭ የሕዝብ ድጋፍ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና አመራሩም ታች ወርደው በፕሮጀክት ማኔጅመንት ደረጃ ፕሮጀክትን ዕለት በዕለት እስከ ሌሊቱ ስምንት እና ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ ባለሀብቱ በጎ ትብብር በማድረጉና የፌዴራሉና የከተማዋ ተቋማት ለሥራው መተባበራቸውም ለስኬቱ ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መሠረተ ልማት ሲዘረጋ አንድም ሰው መጎዳት የለበትም በሚል መርሕ ልማቱ መሠራቱን ጠቅሰው፣ ለሰው ተኮር የልማት ተነሺዎች አያያዝ ልዩ ክብር በመስጠት ልዩ እንክብካቤ በማድረግ መሥራት መቻሉን በስኬትነት ጠቅሰውታል። በችግር ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ሲነሱ በርካታ ባለሀብቶች እጃቸውን ዘርግተዋል፤ እገዛ አድርገዋል ሲሉም ጠቅሰው፣ የሃይማኖት ተቋማት በተመሳሳይ አካባቢያቸውን ቤቶቻቸውን ቦታቸውን ለልማቱ መልቀቃቸውንም ጭምር አስታውቀዋል፡፡ ከወረዳ እስከ ፌዴራል ያለው አመራርም የኮሪደር ልማቱን ተልዕኮ በየእለቱ በመከታተል እንዲሳካ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

አቶ ጥላሁን ክፍተቶች እንደነበሩም አመልክተዋል፡፡ ውይይት ሳይደረግ አልፎ አልፎ ትነሳላችሁ እያሉ ሕዝብ ለማወናበድ የሞከሩ እና እርምጃ የተወሰደባቸው እንዳሉም ጠቅሰው፣ አልፎ አልፎ በአምራቾች በኩል የታይልስ ንጣፍና የከርቭ ስቶን ጥራት ክፍተቶች እንደነበሩና ተለይተው መታረማቸውንም፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ከፍተኛ ዝናብ ማጋጠሙም ተግዳሮቶች እንደነበሩ አብራርተዋል፡፡

በርካታ በጥገኝነት ወይም በደባልነት የሚኖሩ ሰዎች ጉዳይ ሌላው ተግዳሮት እንደነበር ጠቅሰዋል። አካል ጉዳተኞች፣ አዛውንቶች፣ መንቀሳቀስ የማይችሉ ቤት አግኝተው ወደ ሌላ ቦታ መሄዳቸውን ተናግረው፣ መውደቂያ የለንም ብለው የቀሩ እንዳሉም አስታውቀዋል። ጥያቄያቸው ሕጋዊነት ባይኖረውም እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች መጣል የማይችል መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አምኖበት ልዩ ውሳኔ ላይ በመድረስ ኃላፊነቱን መውሰዱን ተናግረዋል።

በዚህ በኩልም የባለሀብቶች ተሳትፎ የጎላ እንደነበረም ኃላፊው ጠቅሰዋል። ባለሀብቶችን በማስተባበር እና ቤት በመገንባት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደዚህ ቤት እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል። የማሽነሪ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ ሥራው እስኪያልቅ ድረስ ማሽነሪው እናንተ ዘንድ ይቆይ ያሉ ባለሀብቶች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በውስጡ ሆነው ለሚሠሩትም ጭምር የሚያስደንቅ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ተከትሎ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ይፋ መሆኑን አቶ ጥላሁን ገልጸዋል። የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ከቀደመው ልዩ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ልማቱ በከተማ ማዕከላት ያሉትን የልማት አውታሮች ገፅታ በሚቀይር ደረጃ መገንባትና መሠረተ ልማት ያልነበረባቸውን ቦታዎች በመሠረተ ልማት ማዳረስ ብቻ የሚፈጸም አይደለም ብለዋል። ለዘመናት የተረሱ ወንዞችንና የወንዞች ዳርቻዎችን ዳግም ወደተፈጥሯዊ ማንነታቸው በመመለስ ከዋናው የከተማ ማዕከል ጋር በማገናኘት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለቱሪዝም መዳረሻ እና ከፍ ያለች የሕዝቧ ክብር ወደምትሆንበት የተግባር ሥራ የተገባበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው አመላክተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተው ምላሸና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ባለሀብቱ አቶ በላይነሀ ክንዴ በኮሪደር ልማቱ 24 ሰዓት፣ ሰባት ቀናት የሚሠራውን አመራር አድንቀዋል፡፡

ባለሀብቱ ቤቱ ቢነካም አንኳ ገበያ መምጣቱ አይቀርም ሲሉም ጠቅሰው፣ የእሳቸው ቤት ከልማቱ ጋር በተያያዘ እንደሚፈርስ እንዲያም ሆኖ ልማቱን እንደሚደግፉ ተናግረዋል። ከተማ አስተዳደሩ ምግብ የሚያስፈልጋቸውን ከ800 ሺህ በላይ ተማሪዎች እየመገበ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ሀገርን የሚያኮራ ሰዋዊ ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ “ትልቅ ነበርን ትልቅ እንሆናለን” የሚለው ቃል በሚዲያ ብቻ ከመጠቀስ ወጥቶ፣ በእውን እየታየ መሆኑን ተናግረዋል። ስህተት ሲኖርም መጠቆም እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አንዱ የሆኑት የወሎ ሕዝቦች ዴሞከራሲያዊ ፓርቲ አባል አቶ ነፃነት ጣሰው፤ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዘው ቢታዩ ያሏቸውን ጠቁመዋል፡፡ የነፃ ጤና ክዊስኮች ቢኖሩ፣ የጎዳና ላይ ልመና ሕግ ቢዘጋጅለት፣ ያረጁ ተሽከርካሪዎችም የኮሪደር ልማቱ ፀር ሊሆኑ ስለሚችሉ ታሳቢ ቢደረጉ ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረቱ አቶ ገብሩ ገብሬ በኮሪደር ልማቱ ዙሪያ በሚነሱ ቅሬታዎች መሠረት ኮሚቴ አዋቅረን የሕዝቡን ቅሬታ ለመለየት ጥረት አድርገናል ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም የተዛቡ መረጃዎች እንደነበሩ ተረድተናል ብለዋል። መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው የልማት ተነሺዎች የገቡባቸው አንዳንድ አካባቢዎች አግኝተናል፤ በዚህ ላይ ቁጥጥር ቢደረግ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረኩ ምላሾችና ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You