የጀስቲን ትሩዶ መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ “የህዝብ ቁጥር መጨመርን ለጊዜው በመግታት” ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ የሚፈቅደውን የስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ አስታወቀ።
ካናዳ በ2025 በሥራ ፈቃድ የሚገቡ 500 ሺህ ነዋሪዎችን እንደምትወስድ ብታስታውቅም ይህ አሃዝ በ21 በመቶ ቀንሶ ወደ 395 ሺህ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። ይህ ከለውጦቹ አንደኛው ተደርጎ የተወሰዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ በበኩላቸው፤ መንግሥታቸው የሠራተኛ እጥረትን ለመፍታት በሚል ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ የወሰዱት እርምጃ “ሚዛኑን አልጠበቀም” ብለዋል ።
በካናዳ ለስደተኞች የሚሰጠው ህዝባዊ ድጋፍ እየቀነሰ መጥቷል። ከህዝብ የተሰበሰበ አስተያየት እንደሚያሳየው የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ በቤቶች እና በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።
እርምጃው ቀደም ሲል የተተገበረውን ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች እና በጊዜያዊ ፈቃድ የሚሰጣቸው የውጭ ሠራተኞች ቅነሳን ተከትሎ የመጣ ነው።
ሐሙስ ዕለት ደግሞ ትሩዶ እና የካናዳ የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ማርክ ሚለር በሥራ ፈቃድ የሚገቡ ላይ ተጨማሪ ቅነሳ መኖሩን አሳውቀዋል።
ዓላማው ከሁለት ዓመት በኋላ 365 ሺህ አዲስ በሥራ ፈቃድ የሚገቡ ሰዎች ብቻ እንዲኖሩ ግብ ለማዘጋጀት ነው ሲሉ ሚለር ተናግረዋል።
ይህ ቅነሳ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በካናዳ የሚኖረውን የህዝብ ቁጥር መጨመርን ይገታዋል ሲሉ ትሩዶ ተናግረዋል። በዚህ ወቅትም የጤና እና የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማጠናከር ዕድል ይሰጣል ሲሉ አክለዋል።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማጠናከር እና የተለያዩ ማህበረሰቦችን የያዘች ሀገር ለመገንባት ረድቷል ያሉትን የስደተኞች ቅበላን በመተግበራቸው ካናዳውያን ኩራት ይሰማቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
“የስደት ሥርዓታችን ሁልጊዜም ተጠያቂነት ያለበት እና እንደሁኔታው የሚለዋወጥ ነው። ዛሬ የምንሠራው ከወረርሽኙ በኋላ የሠራተኛ ፍላጎቶቻችንን በመፍታት እና የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን በማስጠበቅ መካከል ሚዛኑን በትክክል ባለማግኘታችን ነው” ብለዋል።
በመንግሥት መረጃ መሠረት ያለፈው የፈረንጆች ዓመት የካናዳ የሕዝብ ቁጥር 97 በመቶ ያህሉ ያደገው ከስደት ጋር በተያያዘ ነበር።
በተመሳሳይ የካናዳ የስራ አጥነት መጠን ወደ 6.5 በመቶ ሲያድግ ከዚህ ውስጥ የወጣቶች ቁጥር 14 በመቶ በላይ ደርሷል።
እርምጃው የሕዝብን ኢላማ ለማሟላት እና የሥራ ክፍተቶችን ለመሙላት በአዲስ መጤዎች ላይ የተመሠረተው እና ለአስርት ዓመታት ቀጥሎ ከነበረው የስደተኞች ፖሊሲ አካሄድ መለወጡን ያሳያል።
ትሩዶ ወደ መንበሩ ከመጡበት እአአ ከ2015 እስከዚህ ዓመት ድረስ በሥራ ፈቃድ በዓመት የሚቀበሉት የስደተኞች ቁጥር ከ272 ሺህ ወደ 485 ሺህ አሳድገዋል። ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ ያደገው ደግሞ በ2021 ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ነው።
ትሩዶ እና መንግስታቸው አገልግሎቶችን ወይም የመኖሪያ ቤት ግንባታን ሳያጠናክሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞችን በመጨመራቸው ተወቅሰዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በበኩላቸው በካናዳ በፍጥነት እያደገ ያለው የሕዝብ ቁጥር እንደቤቶች እና የህዝብ አገልግሎቶች ላይ ጫና ፈጥሯል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
እአአ ከ1977 ጀምሮ ካናዳውያን ለስደት ያላቸውን አመለካከት የተከታተለው ኢንቫይሮኒክስ ተቋም ባደረገው ጥናት 58 በመቶ ካናዳውያን የስደተኞች መጠን በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ይሰማቸዋል ብሏል።
ኢንስቲትዩቱ ውጤቶች እንደሚጠቁሙት በስደተኝነት ዙሪያ ያለው የህዝብ አስተያየት “ተቀባይነት ካለው ወደ ችግር ተቀይሯል።”
የስደተኞች ቁጥር ቅነሳው እንደ የማይግራንት ራይትስ ኔትወርክ ባሉ ተሟጋች ቡድኖች ተችቷል። ለትሩዶ እና ሚለር በጻፉት ግልፅ ደብዳቤ ላይም ስደተኞች ለካናዳ የጤና እና አገልግሎት ችግር አለአግባብ ተወቃሽ እየተደረጉ ነው ብሏል።
“ለካናዳ የመኖሪያ ቤት ችግር፣ ለሥራ እጦት፣ ወይም በቂ ላልሆነ የጤና አጠባበቅ ወይም ለሌሎች የሕዝብ አገልግሎት ችግሮች “ስደተኞች ተጠያቂ አይደሉም” ብሏል።
እነዚህ ችግሮች “ለአስርት ዓመታት በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት ፖሊሲዎች የገንዘብ ድጋፍ ስላላገኙ እና የህዝብ አገልግሎቶችን ወደ ግል ንብረትነት በመዘዋወራቸው የተገኙ” ውጤቶች ናቸው ሲል ቡድኑ ማመልከቱን የዘገበው ቢቢሲ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም