አቶ አሸናፊ አሰፋ የላይፍ አግሮ የቡና ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤትና ስራ አስኪያጅ
ሰሜን ሸዋ ዞን፣ መንዲዳ የሚባለው አካባቢ የትውልድ ስፍራቸው ነው። የተማሩትም በዚያው አካባቢ ነው። የ12ኛን ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃ ነጥብ በማግኘታቸው የጂማ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ። በዚያም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቡና እና ሻይ እና ቅመማቅመም ፕሮዳክሽን ማኔጅመንት (Coffee, Tea and Spices Production and Management) ላይ ሰርተዋል።
ቡና እና ሻይ ድርጅት ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት በሙያቸው አገልግለዋል። ከተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ጋርም በቡና ዙሪያ ሰርተዋል። በ2011 ዓ.ም በቡና ዙሪያ ስልጠናን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ የራሳቸው ኩባንያ መስርተዋል፡፡
ኩባንያቸው በዋናነት ለቡናው አምራች አርሶ አደር፣ ላኪ እና በሰንሰለቱ ውስጥ ላሉ አካላት፤ በቡና ማምረት፣ አዘገጃጀት፣ አቆላል፣ ደረጃ አወጣጥ፣ ኤክስፖርት አሰራር ላይ ስልጠና የሚሰጥ ነው።
እንግዳችን አቶ አቶ አሸናፊ አሰፋ ይባላሉ፤ የላይፍ አግሮ የቡና ማሰልጠኛ ተቋም መስራች እና ስራ አስኪያጅ ናቸው ። ቡናን በተመለከተ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ሲሰሩ የቆዩ እንደመሆናቸው ካላቸው የካበተ እውቀት እና ልምድ እንዲያካፍሉን ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርገን ተከታዩን አጠናቅረናል።
አዲስ ዘመን፡- በቡና ዘርፉ ወደስልጠና ለመምጣት የተነሳሱበት ምክንያት ምንድን ነው ?
አቶ አሸናፊ፡– በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ከቡና ጋር ተያያዥ የሆኑ ስራዎችን ተቀጥሬ ስሰራ ረጅም ዓመት አስቆጥሬያለሁ። በተለይም ከቡና አምራች አርሶ አደር ጋርም ሆነ ከቡና ላኪው ጋር ሰፋ ያለ ቁርኝነት ነበረኝ። በዚህ ሰንሰለት ውስጥ ብዙ እንደ መቆየቴ በርከት ያለ ክፍተቶችን ለማየት ችያለሁ። የኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕሙ ጥሩ ቢሆንም፤ በቅድመ ምርት እና በድህረ ምርት አያያዝ ላይ ችግር መኖሩን ማስተዋል ችያለሁ። ከዚህ አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ ቡና ችግር ውስጥ እንዳለና ክፍተት ያለበት መሆኑን መረዳት አያዳግትም።
ይህንን ክፍተት ሙሉ በሙሉ መሙላት ባንችልም የራሳችንን ድርሻ እናበርክት በሚል ኩባንያውን ለመመስረት የወሰንነው። በዋናነቱ ዘርፉ ላይም እንደቆየ እንደ አንድ ባለሙያ ትልቁ ችግር የነበረው ከአመራረትና ከጥራት ጋር የተያያዘ ችግር ነው። ይህን ችግር አስተውለን በተሻለ መልኩ ቡና ላይ ብንሰራ በሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ በሙሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ በሚል ተነሳሽነት ነው ወደስራ የገባነው። በዚህም አሁን ላይ የበኩላችንን በመወጣት አገራችን የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን።
ቡናችን በጥራቱና በጣዕሙ የተሻለ ሆኖ እንዲወጣ ፍላጎታችን ነው፤ ከዚህ አኳያ ባለሙያዎችን እያፈራን ማውጣት ካልቻልን ችግር በመሆኑ በኩባንያችን በኩል በርከት ያሉ ባለሙያዎችን ባለፉት ስድስት ዓመታት ማፍራት ችለናል። ቢያንስ ከ700 እስከ 750 ያህል ባለሙያዎችን ብቁ አድርገናል ብለን እናስባለን። ከዚህ ቀደም ቡና እንዴት እንደሚሰራ ይህ አይነቱ የስልጠና እድል አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ምን ያህል የቡና አይነቶች አሉ?
አቶ አሸነናፊ፡- ቡና የተወለደው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ለዓለም ያበረከተችውም ኢትዮጵያ በመሆኗ “አረንጓዴው ወርቃችን” ብለን እስከመጥራት ደርሰናል። ወደቡና አይነቶቹ ስመጣ ዘርዘር አድርጎ መናገርን ይጠይቃል፡፡
በዝርያ ደረጃ የምናወራ ከሆነ በዓለም አቀፍ ላይ ቡና ወደ 500 ዝርያዎች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ ግን በደንብ እየተመረቱ ያሉት ሁለት አይነት ዝርያዎች ናቸው። እነዚህም አረቢካ እና ሮቡስታ የቡና ዝርያዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ የምታመርተው አረቢካ የተባለውን የቡና አይነት ነው። አረቢካ የተባለው ቡና ደግሞ በጣዕሙ በጣም የተወደደ፣ ቃናውም ሆነ ካፊኑም ለሰዎች ተስማሚ ነው። ሩቡስታው ደግሞ ምሬቱና ካፊኑ ከፍ ስለሚል ሲጠጣ ምሬቱ ትንሽ ያዝ ያደርጋል። ስለሆነም በግማሽ ያህል ተመራጭነቱ ከአረቢካ ቡና ይቀንሳል።
ኢትዮጵያ የምታመርተው አረቢካ ቡና ይሁን እንጂ በውስጡ ደግሞ የተለያዩ የአረቢካ ቡና ንዑስ ዝርያዎች አሉ። እነዚህ ንዑስ ዝርያዎች ከአስር ሺ በላይ ናቸው ተብሎ ይታሰባል። በተለያዩ አካባቢዎች አሁን እየበቀሉ ያሉና ወደ ዓለም ገበያም እየቀረቡ የሚገኙ በርካታ ዝርያዎች አሉ፡፡
በሌላ ቡኩል ቡናን በቅርጽ ስናስተውለው ደግሞ በሁለት የተከፈለ ነው። ይኸውም አንደኛው (Bourbon) የተባለ አይነት ሲሆን፣ ከበብ ብሎ ወፈር የሚል ቅርጽ ያለው ነው። የዚህ አይነቱ የአረቢካ ቡና ንዑስ ዝርያ ብዙ ጊዜ መገኛው በሲዳማ፣ በይርጋ ጨፌ እና ጉጂ እንዲሁም አርሲ አካባቢ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሽንጠ ረጃጅም ሆኖ ጫፍና ጫፉ ሾል ያለ የቡና አይነት ነው። ይህ መገኛው ጅማ፣ ነቀምት፣ ካፋ፣ ቴፒ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በሐረር ዙሪያ ሲሆን፣ ቲፒካ (typica) በመባል የሚታወቅ የአረቢካ ቡና ንዑስ ዝርያ ነው።
እነዚህ ሁለቱ ዝርያዎች በጣም ታዋቂ ይሁኑ እንጂ በርካታ ንዑሱ ዝርያዎች አሉ። የቡና መገኛ እንደመሆናችን ለዓለም ያስገኘነው የቡና ዝርያዎችም በጣም በርካታ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አካላት ደግሞ ዝርያዎቹን እያዳቀሉ ወደተለያየ የዝርያ አይነት አስፍተዋቸዋል። ይሁንና እኛ የቡና ምንጩ ነን።
አዲስ ዘመን፡- ከምርቱ ምን ያህል ተጠቃሚ ሆነናል? ካልሆንስ የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ እንዳንሆን በዋነኛነት የሚጠቀሱ ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ አሸናፊ፡- ኢትዮጵያ ያላት የመሬት አቀማመጥና የአየር ንብረት አጠቃላይ ለቡና ምርት ምቹ ነው። በተለይ የኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች በሙሉ ከፍተኛ ቡና የማምረት አቅም አላቸው። ይህ ሁሉ ቡናን ማምረት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይኑር እንጂ ከቡና ምርት የሚፈለገውን ያህል አልተጠቀምንም፡፡
አለመጠቀማችንን የሚያሳይ ምን ነገር አለ ከተባለ እስካሁን በቡና ተሸፍኖ ያለ መሬት በሔክታር ሲሰላ ከ500 ሺ አይበልጥም፤ ይህ የቅርብ ጊዜ መረጃ ነው። ቡና ማምረት የጀመርነው ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ይሆናል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም እንኳ ቡና ማምረት የሚያስችል ወደ ሶስት ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ መሬት ቢኖረንም አሁንም ከ500 ሺ ሔክታር መሬት እልፍ አለማለታችን የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ ማለት ካለን መሬት እየተጠቀምን ያለው አንድ በመቶ የሚሆነውን ብቻ ነው ማለት ነው።
ወደ 25 ሚሊዮን የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቡና ዘርፉ ላይ ተቀጥሮ ራሱን የሚያስተዳድር ነው። ከ35 እስከ 40 በመቶ ደግሞ ውጭ ምንዛሬውን ወደ ኢትዮጵያ የሚያመጣው ይኸው ቡና ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ባላት ምቹ ሁኔታ ቡናን ማምረት ብትችል ዘርፉ ብቻ የኢትዮጵያን ሕዝብ መቅጠር የሚችል ነው። የውጭ ምንዛሬያችንም አሁን ከምናገኘው በአምስትና በስድስት እጥፍ እንደሚጨምር መገመት አያዳግትም። እውነት ለመናገር ሀብታችን በሆነው ቡናችን ላይ ተኝተንበታል።
አዲስ ዘመን፡- በሀገር ውስጥ ቡናን የሚመለከቱ ምርምሮች በመካሔድ ላይ ናቸው ማለት እንችላለን?
አቶ አሸናፊ፡– እኔ እስከማውቀው ድረስ ምርምሮች አሉ፤ የጅማ ምርምር ማዕከል ብዙ ጊዜ በቡና ላይ ምርምር ይሰራል። በተለይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችንና በሽታን እንዲሁም ድርቅን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን እያወጣ ለአርሶ አደሩ እያሰራጨ ይገኛል። ይሁንና እኔ እስከማውቀው እየተሰራ ያለው የምርምር ስራ በቂ አይደለም።
እኛ ቡናን ከአንዱ ቦታ ሔደን ለቅመን በማምጣት የዚህ አካባቢ ቡና ነው ከማለት በዘለለ የአንዱን ጣዕም ከሌላው ጋር በማወራረስ የተለያዩ ስራዎችን ብንሰራ እና ተጨማሪ የጣዕም አይነቶችን ለገበያ ብናቀርብ ውጤታማ የሚያደርገን ነው፤ ይሁንና በዚህ ዙሪያ ገና ምንም አልተሰራም ማለት ይቻላል። ምርምር ሲሰራ ከቡና ቀማሽና ከአግሮኖሚስት በተጨማሪም ከገበያው አንግልም እንዲሁ ባለሙያዎች መኖር አለባቸው። ብዙውን ስራ በአሁኑ ሰዓት እየሰራ ያለው የጅማ ምርምር ማዕከል ቢሆንም፤ በቡና ምርምር ዙሪያ በበቂ ሁኔታ ተሰርቶ የኢትዮጵያ ቡና የተሻለ ደረጃ ላይ ነው ብዬ ግን አላምንም።
አዲስ ዘመን፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ አንዳንድ ድርጅቶች፤ ሀገር ውስጥ መሬት ወስደው ቡና እያለሙ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህ ሀገሪቱን ምን ያህል ተጠቃሚ ያደርጋል፤ ከእነዚህ ተቋማት የሚወሰድ ተሞክሮ አለ?
አቶ አሸናፊ፡– መጠኑ አነስተኛ ነው እንጂ የውጭ ባለሀብቶች ገብተው በማልማት ላይ ናቸው። ብዙዎቹ ደግሞ የሚሰሩት ከኢትዮጵያ ጋር በጆይንት ቬንቸር ነው። በተወሰነ ደረጃ እርሻው ላይ መስራት የተጀመረ ሲሆን፣ አዲሱ ፖሊሲም ኢትዮጵያ በሯን ክፍት ማድረጓን የሚያሳይ ነውና የውጭ ኢንቨስተሮች በቡናም ሆነ በሌሎችም ስራዎች ላይ ገብተው መስራት የሚያስችል ሁኔታ በመፈጠር ላይ ነው። ይሁንና እስካሁን ባለው ሒደት በእርሻውም ሆነ እሴት ጨምሮ በመላኩ ረገድ ገብተው እየሰሩ ያሉ ውስን ናቸው ማለት ይቻላል።
የውጭ ባለሀብቱ ሲመጡ ካፒታል ይዘው ነው፤ ከሁሉ በላይ ግን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው ስለሚመጡ ኢትዮጵያን የሚጠቅማት የእውቀት ሽግግሩ ነው። ያላየነውንና ያላስተዋልነውን አንግል እንድናይ ያግዘናል። ስለሆነም ከምንም በላይ በዚህ ዙሪያ ቢሰራበት የበለጠ ውጤት ያስገኛል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የጥዑም ቡና ባለቤት ናት እየተባለ ይነገራል፤ የኢትዮጵያ ቡና የጣዕም ልኬት የሚገለጸው እንዴት ነው?
አቶ አሸናፊ፡- ቡናን በተመለከተ እንደ አገር ውስጥም ሆነ እንደ ውጭ ስታንዳርድ አለን። ጥሩ ጣዕም አለው ለማለትም መለኪያ መንገዶች አሉን። እነዚህም ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸው የጥራት መለኪያዎች ናቸው። እነዚህም በዋናነት የሚከፈሉት በሁለት ነው፡
አንደኛው በጥሬው የሚመረመር ነው፤ በጥሬ ላይ የሚያሟላቸው ለምሳሌ በውስጡ ያለው የእርጥበት መጠን ጣዕሙ ላይ ተጽዕኖ ያመጣል፤ የፍሬው መጠንና ሽታው ራሱ ስለቡናው አዘገጃጀት ስለጣዕሙ ብዙ ይናገራል። የቡና ቀለም በራሱ መለኪያ ነው።
በዋናነት ግን ስናመርት በድኀረ ምርትና በቅድመ ምርት አያያዝ ምክንያት ቡናው ላይ የሚመጡ ጉድለቶች አሉ። ለምሳሌ በአግባቡ ባለመልቀም፣ ባለማስጣትና ቡናው ሳይደርስ በመልቀም ወይም ደግሞ አልፎበት በመልቀም የሚፈጠሩ ጉድለቶች አሉ። ጉድለቱ እየበዛ ከመጣ ደረጃውም የዚያኑ ያህል ዝቅ ስለሚል እስከ አምስተኛ ደረጃ ድረስ ዝቅ እያለ ስያሜ የሚያገኝ ይሆናል።
በዋናነት ግን ጥራትን ለመመዘን የቡናውን 60 በመቶው የሚይዘው ቅምሻ ሲሆን፣ 40 በመቶው ደግሞ የሚይዘው ጥሬው ነው። አንድ ሰው ቡና ቀምሶ ጥዑም ነው የሚለው በአራት መስፈርቶች ለክቶት ነው። የመጀመሪያው አሲዲቲ የሚባለው ነው፣ ቡናውን ስንጠጣ የምላሳችን ጫፍና ጫፉ ላይ ወጋ አድርጎ ወዲያውኑ እንድንውጠው የሚያደርገን ነገር ካለው ማለትም ልክ እንደ ዋይን ፍሬ ወጋ አድርጎ ወዲያውኑ የሚጣፍጥ አይነት ነገር ካለው እንድንተፋው ሳይሆን እንድንውጠው የሚያደርገው ነገር አለውና በቀጥታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋ ማውጣት የሚችል ቡና ነው ማለት ነው። እናም ዓለም አቀፍ ቡና ገዥዎች ለዚህ አይነት ጣዕም ያለው ቡና ለመክፈል ፈቃደኞች ናቸው።
ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ በባህላችንም የሚታወቅ አይነት ሲሆን፣ “ክባዴ” በመባል ይታወቃል። ከየትኛውም አካባቢ የተገኘ ቡና በእኩል ውሃና ዱቄት ተፈልቶ፤ አንዱ ወፍራም፣ ሌላው ቀጭን ሊሆን ይችላል። የውፍረቱም የቅጥነቱም ደረጃ የተለያየ ይሆናል፤ ሶስተኛው መለኪያ ቃና የምንለው ነው፤ ብዙ ጊዜ የአሲዱና የክባዴው መስተጋብር ነው ቃና የሚሰጠው ይባላል፡፡
ቃና ሲባል ለምሳሌ ዋይን ዋይን የሚል ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ ጅማ ላይ ያለውን የታጠበ የሊሙ ቡና ልክ ቀይ ዋይን ሲጠጣ የሚሰጠውን አይነት ቃና ያለው ነው። ወደ ሲዳማ ብንሔድ ደግሞ የድብልቅ ቅመም አይነት ቃና ያለው ነው። ወደ ይርጋ ጨፌ ደግሞ ሲኬድ ከአበባ ውስጥ የሚነሳው የዱቄቱ አይነት ቃና ያለው ነው። ወደ ጉጂ ስናቀና ደግሞ የማንጎ፣ ፓፓያ፣ አፕልና መሰል የፍራፍሬ አይነት ቃና ያለው ነው። ወደ ሐረር ብንሔድ ደግሞ ልክ የለጋ ቅቤ ወይም የገበታ አይነት ቃና ያለው ነው። ኢትዮጵያን ለየት የሚያደርጋት እነዚህ የተለያየ ቃና/ጣዕም ቡና ባለቤት በመሆኗም ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ቡና የጣዕም ልኬት ያለበት ደረጃስ ከሌሎች ቡና ላኪ አገሮች የሚለየው በምንድን ነው?
አቶ አሸናፊ፡- በዋናነት የሚለየው ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ ጣዕም ያላት ናት። ለምሳሌ የዓለማችን አንደኛ ቡና አምራች አገር ብራዚል ብንሔድ ቡናው በደረጃ ይለያያል እንጂ ጣዕሙ አንድ አይነት ነው። ደረጃ አንዱ በጣም ንጹህ ነው፤ ደረጃ ሁለት ደግሞ አነስ ያለ ጥራት የያዘ ነው፤ በዚያ ልክ ጥራቱ እንደየደረጃው እያነሰ ይቀጥላል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ያለውን ቡና የምንሸጠው በጣዕሙ ነው። ኢትዮጵያ ቡናን ለገዥ የምትሸጠው “የትኛውን አይነት ጣዕም ትፈልጋለህ” በማለት ነው። በአሁኑ ወቅት የተለዩና የታወቁ በትንሹ ወደ 30 ገደማ ጣዕም አለን። እንዲያውም ከዚህ በላይ እንደሆነ ይነገራል። 30ዎቹ ግን ወደገበያው የገቡ የጣዕም አይነቶች ናቸው። አንዳንዴ ከፍራፍሬም በተናጠል የብርቱኳን ጣዕም ብቻ ያለው አለ። እንዲህ የብዙ ጣዕም ባለቤት መሆኑ ትልቅ እድል ነው፤ ሌላው አገር ላይ ያለው በጣም ውስን ጣዕም ነው።
ኢትዮጵያ የዚህ ሁሉ ጣዕም ባለቤት መሆን የቻለችው የአየር ንብረት ምቹ በመሆኑ ነው። በአገራችን እያንዳንዱ ቦታ ያለው የመሬት አቀማመጥም ሆነ በአፈር ውስጥ ያለው ይዘት የተለያየ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ቡናዋን ስትሸጥ ቡና ብላ ብቻ አይደለም፤ ደንበኞቿን “የትኛውን ጣዕም ነው የምትፈልጉት?” በማለት በማማረጥም ጭምር ነው። ልክ ምግብ ቤት ገብተን ሜኑ (የምግብ ዝርዝር) ቀርቦልን ማማረጥ እንደምንችለው ሁሉ ኢትዮጵያም የምታስመርጠው የተለያየ አይነት የቡና ጣዕም አላት።
ነገር ግን በዚህ ረገድ የበለጠ የቡና ጣዕም እንዲኖረን በውስን ደረጃ እንጂ በሰፊው እየሰራንበት አይደለም። ከዚህም በላይ የአንዱን አካባቢ ቡና ከሌላው አካባቢ እያደባለቅን መስራት ብንችል የተለያየ አይነት ጣዕም ማምጣት የሚያስችለን ምቹ ሁኔታ አለን። ይህ እድል ዓለምን ገና ጉድ የምናሰኝበት ነው፤ በአሁኑ ወቅት ቡናችንን እየሸጥን ያለነው የይርጋ ጨፌን በይርጋ ጨፌ፣ የሲዳማን በሲዳማ፣ የነቀምትን በነቀምት፣ የጂማን በጂማ እያደረግን ነው።
ነገር ግን እያዳቀልን የተለያየ የቡና ጣዕም እያወጣን ዓለምን ጉድ ልናሰኝበት የምንችልበት አቅም ደግሞ አለን። በዋናነት ግን አሁን ወደ 30 አይነት ጣዕሞች አሉና እሱ ኢትዮጵያን ከሌላው ቡና ላኪ አገር ለይቷል ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ከጥዑም ቡና ጀርባ ያሉ ቡና አምራቾች ተገቢው መስመር ላይ ናቸው ብለው ያስባሉ? የዓለም ገበያ በሚፈልገው ጥራትና ብዛትስ በማምረት ላይ ይገኛሉ?
አቶ አሸናፊ፡– በመጠን ደረጃ ሲታይ ኢትዮጵያ አስቀድሜ እንደገለጽኩት ገና አንድ ስድስተኛውን እንኳ የማምረት እድላችንን አልተጠቀምንበትም። በአማካይ ኢትዮጵያ እስካሁን የላከችው 320 ሺ ቶን ቡና አካባቢ ነው። ይህንን የላከችው ከለማው ከ500 ሺ ሔክታር መሬት ላይ ነው። ስለዚህ ካለን አቅም አኳያ ቡናውን በአግባቡ አምርተናል ብዬ አለላስብም። ነገር ግን ከተደራሽነትና ከጣዕም አኳያ በርካታ ቡና ወደተለያየ የዓለም ክፍል በመላክ ላይ ይገኛል። በብዛትና በጥራት ነው ወይ ከተባለ ግን አይደለም።
ወደ አምራቾቹ አርሶ አደሮች ስንመጣ ደግሞ እስካሁን ባለው ሁኔታ በአግባቡ ተጠቅመዋል የሚል መረጃ የለኝም። በአጠቃላይ የቡና አሻሻጡ ሰንሰለት የተራዘመ ነበር። እንዲያው ከጥቂት ዓመት በፊት በአምራቹ አርሶ አደርና በቡና ላኪው መካከል ብዙዎች ነበሩ። ከዚህ የተነሳ ተጠቃሚ የሚሆኑት ከአርሶ አደሮቹ ይልቅ በመካከል ያሉ አካላት ናቸው፡፡
አሁን ግን ይህን ትንሽ ለማጥበብ ተሞክሯል። ይሁንና አሁንም በመካከል ሌላ አካል መኖር የለበትም ማለት አይቻልም። አንድ ላኪ ወደ እያንዳንዱ አርሶ አደር ዘንድ በቀላሉ መድረስ አይችልም፤ የግድ ሌላ አካል ያስፈልጋል። ቡና አምራቹ በተለያየ ክልልና በተለያየ ቦታ ተበታትኖ ያለ እንደመሆኑ ስራው ሊስተጓጎልበት ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ቡናን በመላክ አምስተኛ ደረጃ ላይ እንዳለች ይነገራል፤ በመላኩ ረገድ ፊተኛው መስመር ላይ እንደመገኘቷ በዚያው ልክ ተጠቃሚ ናት ይላሉ?
አቶ አሸናፊ፡– በእርግጥ ቡና በላክነው ልክ ተጠቃሚዎች ነን፤ ነገር ግን ካለን ምቹ ሁኔታ የተነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ አምስተኛ ደረጃ ላይ መገኘት ነበረብን ወይ? የሚያስብል ነገር አለ፤ ይህ ቁጭት የሚፈጥር ነው። ምክንያቱም ምቹ እና ተስማሚ የአየር ንብረትም ሆነ ሰፊ መሬት ያለን አገር እንደመሆናችን ከዚህም በላይ ደረጃ መያዝ ነበረብን ባይ ነኝ፤ እነ ብራዚልና ቬትናም በአሁኑ ወቅት ሊታረስ የሚችል መሬታቸውን ጨርሰዋል። ሶስተኛዋ ኮሎምቢያ አራተኛዋ ደግሞ ኢንዶኔዥያ ናት፤ እነርሱም ቢሆኑ ሀብታቸውን አሟጥጠው በመጠቀማቸው አቅማቸውን ጨርሰዋል ማለት እንችላለን።
እኛ ግን ሙሉ በሙሉ አቅማችንን መጠቀም ብንችል ተጠቃሚነታችን በዚያው ልክ የሚያድግ ሲሆን፣ የላኪነት ደረጃችንም ወደ ሁለትና ሶስት መምጣት ይችላል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቡና በብዛቱ ሳይሆን ጥራቱ በጣም የታወቀ ስለሆነ ተደራሽነታችን ይሰፋል። የውጭ ምንዛሬ የማግኘት እድላችንም ያድጋል። በዚያው ልክ በሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ሁሉ የተሻለ ተጠቃሚዎች መሆን ይችላሉ። እኔ በዚህ ደረጃ ተጠቃሚ ባለመሆናችን ቁጭት አለብኝ። ወደፊት በተሻለ መስራት ይኖርብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ጣዕም ያለው ቡና ታምርት እንጂ የዓለም ቡና ገበያን የመወሰን አቅም የላትም፤ ገበያውን ለመወሰን የሚያስችለው ጅማሮ ምን መሆን አለበት?
አቶ አሸናፊ፡- ገበያውን በዋናነት የሚወስኑ በአገር ውስጥ አምራቾች ብቻ አይደሉም። እኛ ቡና ስላመረትን ብቻ የዓለም አቀፍ ገበያን እንቆጣጠረዋለን ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም ቡናውን ገዝተው እሴት ጨምረው የሚያዘጋጁት የውጭ ኩባንያዎች ስለሆኑ የመደራደር አቅማቸው ከፍ ያለ ነው። እንዲያውም ምርታችን በጣም በጨመረ ቁጥር ዋጋ እንድንቀንስ የማድረግ አቅም ይኖራቸዋል።
ለምሳሌ ብራዚል ቡናን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ በኩል አንደኛ አገር ናት። ይሁንና እኔ አንደኛ ቡና አምራች አገር ነኝና ቡናዬን የምሸጥላችሁ በውድ ዋጋ ነው ማለት አትችልም። አንደኛ በጥራት የሚበልጣት ይኖራል፤ ሌላው ደግሞ የገዥዎች ፍላጎትና የመግዛት አቅም ከጠጪው አቅም ጋር የሚወዳደር ነገር ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ከሌሎች ቡና ላኪ አገሮች ይልቅ በጉዳዩ ላይ እድሉ አላት፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ቡና በጥራትም የተሻለ በመሆኑ ማለት ነው። ስለዚህ የተሻለ ጥራት ያለውን ቡና በተሻለ ዋጋ ካቀረብን በገበያው የተሻለ ድርሻ ሊኖረን ይችላል።
በአሁኑ ወቅት የእኛ የገበያ ድርሻ ከአምስት በመቶ የሚበልጥ አይደለም። ብራዚል ከ30 እስከ 35 በመቶ ያህል ድርሻ ያላት ሲሆን፣ አጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚመረተው ወደ 160 ሚሊየን ኬሻ ቡና ነው። ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ የምታመርተው ከሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኬሻ ቡና አይበልጥም። ይህን መጠን ከ160 ሚሊዮን ኬሻ አኳያ ሲሰላ ከአራትና አምስት በመቶ ከፍ የሚል አይደለም። ስለዚህ እኛ በዚህች መጠን ከገበያው ብንወጣ የዚያን ያህል በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የቡና እጥረትን አንፈጥርም፡፡
ነገር ግን ጥሩ ጣዕም ያለው ቡና፤ እንደቅመም የሚጠቀሙበትን ቡና ልናሳጣቸውና በዛ ልክ ልናጎድልባቸው እንችላለን። ይሁንና ኢትዮጵያ ቡና አላመርትም ብላ ብታቆም የምታመጣው ነገር የለም። የኢትዮጵያ ቡና የቅመም ያህል ሌላውን ቡና ማሻሻጫ ጭምር በመሆኑ ከጣዕም አኳያ ጉዳት ልናመጣ ግን እንችላለን። በመሆኑም በጣዕም ረገድ ኢትዮጵያ ጠንክራ ብትሰራ የተሻለ ገቢ ይኖራታል።
አዲስ ዘመን፡- ኢ ትዮጵያ ዶላሩን፤ ዓለም አቀፍ ገዥዎች ደግሞ ቡናውን እንዲያጣጥሙት ኢትዮጵያ ምን ምን ላይ መስራት ይጠበቅባታል?
አቶ አሸናፊ፡– በዋናነት ትልቁ ነገር ቡና አምራች አገሮች ከ70 በላይ መሆናቸው ታሳቢ መደረግ አለበት። ከእነዚህ አገራት ውስጥ ኢትዮጵያን ለየት የሚያደርጋት የተለያየ ጣዕም ያለው ቡና ማምረት መቻሏ ነው። በጣም ሰፊ የጣዕም አይነት ያለባት አገር ናት። ይህን ጣዕም በብዛትና በጥራት አሁን ካለበት ከፍ ማድረግ ዋናው ነገር ነው።
አሁን ያለንን ቡና ጥራቱን ለመጠበቅ መስራት ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ብዙ ጥረትን ይጠይቃል። ከአምራቹ አርሶ አደር ጀምሮ ያለው የቡና ሰንሰለት ምርምር ማዕከላትን ጨምሮ በጥራትም በጣዕምም ላይ በአግባቡ እንዲሰሩ ማድረግ የተሻለ ነገር እንዲኖረን ማድረግ ያስችለናል።
ቡናችን ትልቅ አቅም ያለው ነው። አቅማችንን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በጥምር የሚሰራ በርካታ የቤት ስራ አለ። በአሁኑ ወቅት ያገኘነው የውጭ ምንዛሬ ድሮ ከምናገኘው ይልቅ የተሻለ እድገት አለው።
ይሁንና የሚፈለገው መጠን ላይ ደርሰናል ማለት አይቻልም። ስለዚህ ከፖሊሲ አውጪዎች፣ ከአስፈጻሚ አካላት፣ ከአምራቹና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጀምሮ በጥምር በመስራት የኢትዮጵያን ቡና ልናሳድግ የግድ ይለናል። አሰራርን ማዘመን፣ ንግዱ ላይም ያሉ ጉድለቶችን መከታተል ይፈልጋል፤ በተለይ ከአርሶ አደሩ ተሰብስቦ የሚመጣ እንደመሆኑ ጥራት አጠባበቅ ላይ መስራት ያሻል፤ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግም ተገቢ ነው።
እኛ አገር በሔክታር እስከ ሰባትና ስምንት ኩንታል ምርት የሚገኝ ሲሆን፣ ብራዚል ደግሞ እስከ 15 ኩንታል ድረስ ይገኛል፤ ስለዚህ በዚህ ላይም መስራት ተገቢ ነው። በዚህ መልኩ የሚሰራ ከሆነ ብዙ ወጣቶቻችን የስራ እድል ያገኛሉ፤ የውጭ ምንዛሬም በከፍተኛ ሁኔታ ማግኘት ይቻላል። የአገር ኢኮኖሚም ከፍ ይላል።
አዲስ ዘመን፡- ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አሸናፊ፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም