ለሁሉም ክፍት የሆነ የታዳጊዎች ሜዳ ቴኒስ ውድድር ነገ ይጠናቀቃል

ለሦስት ቀናት የሚቆይ ለሁሉም ክፍት የሆነ የታዳጊዎች ሜዳ ቴኒስ ውድድር በአዲስ አበባ ሦስት የተለያዩ ሜዳዎች ሲካሄድ ቆይቶ ነገ ይጠናቀቃል፡፡ ውድድሩ በሦስት የእድሜ እርከኖች የሚካሄድ ሲሆን ለታዳጊዎች የውድድር ዕድል ለመፍጠርና ተተኪዎችን ለማፍራት ታስቦ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ታሪኩና ደስታ የቴኒስ ስፖርት ክለብ ከሶሊኖ ኢትዮጵያ ኮፊ ጋር በትብብር የሚያካሄዱት ይህ የታዳጊዎች ሜዳ ቴኒስ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተውጣጡ ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል። የውድድሩ ዓላማም ኢትዮጵያን በታላላቅ የውድድር መድረኮች የሚወክሉ ታዳጊ የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ለስፖርቱ ልዩ ፍቅርና ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች ለማበረታታት እንደሆነም ተጠቁሟል።

ውድድሩ ዓለም አቀፍ ደረጃ በጠበቀ መልኩ በሒልተን ሆቴል፣ መኮንኖች ክበብና በገነት ሆቴል እየተካሄደ ሲሆን፣ በሦስት የእድሜ እርከኖች ከ10፣ 12 እና 14 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እየተሳተፉበት ነው። ይህም በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ውድድሮች ረጅም ጊዜን የሚወስዱና በሌላ ዓለም የሚካሄዱት በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁ በመሆኑ ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ ፉክክር ለማዘጋጀት ታስቦ መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

በውድድሩ ኢትዮጵያን በዓለም መድረኮች የሚወክሉ የቴኒስ ስፖርተኞችን ማፍራት እንዲቻል፣ መሰል ውድድሮችን በየጊዜው ማድረግ የሚገባ ቢሆንም ተተኪዎችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ የስፖርት ተቋማት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከነዚህ የቴኒስ ስፖርት ላይ በተለይም ታዳጊዎችን መሠረት አድርገው ከሚሠሩት መካከል ታሪኩና ደስታ ቴኒስ ክለብ አንዱ ነው፡፡

ክለቡ ለረጅም ዓመታት ሀገርን በስፖርትና በሌሎች ዘርፎች ማስጠራት የቻሉ ታዳጊዎችን አፍርቶ ለትልቅ ደረጃ ያደረሰ ሲሆን፣ ታዳጊዎች ቴኒስን በመጠቀም በሁለንተናዊ ስብዕና ታንጸውና የስፖርት ሥነ-ምግብር ተላብሰው እንዲያድጉ እየሠራ ይገኛል፡፡ በክለቡ የሥልጠና ማዕቀፍ ውስጥ የሚካተቱትም ገቢያቸው አነስተኛ ከሆኑ ቤተሰቦች የተገኙ ታዳጊዎች ሲሆኑ፣ ታዳጊዎቹ ከሥልጠና በተጨማሪ በትምህርትና በሌሎች ጉዳዮች ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡

ክለቡ ሁለት አስርተ ዓመታትን ባስቆጠረ እድሜው በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በስፖርትና በትምህርት ዕድሎችን እያመቻቸ ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በክለቡ ውስጥ 80 ያህል ታዳጊዎች ሥልጠናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሥልጠናም ባሻገር ለታዳጊዎች ውድድር ዕድልን ለመፍጠር የሚሠራ ሲሆን ነገ የሚጠናቀቀው ውድድርም የዚህ አንድ አካል ነው፡፡

ይህም በክለቡ ከታቀፉት ባሻገር በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች ላሉ የቴኒስ ስፖርተኞች የውድድር ዕድል ለመፍጠር እና ልምድ ለመቅሰም የሚያስችል (TDKET junior open 2024) የተሰኘ ውድድር መሆኑን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡

የክለቡ መሥራችና ዋና አሠልጣኝ ታሪኩ ተስፋዬ፣ ለሁሉም ክፍት የሆነ የታዳጊዎች ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ ጠቁሞ፣ ክለቡ ከዚህ ቀደም ታዳጊ ስፖርተኞችን አሠልጥኖ ለብሔራዊ ቡድን ማብቃት ላይ ሲሠራ እንደነበር ገልጿል። በዚህም መሠረት ባለፉት 24 ዓመታት ከ350 በላይ ታዳጊዎችን አሠልጥኖ ለትልቅ ደረጃ ማብቃት ችሏል። ከክለቡ የወጡትም ታዳጊዎች ብሔራዊ ቡድንን በመወከል በምሥራቅ አፍሪካና በአሕጉር ደረጃ በርካታ ሜዳሊያዎችን ማሳካት እንደቻሉም ጠቅሷል። ባላቸው ከፍተኛ አቅምም በሀገር ውስጥና በውጪ ከአምስት መቶ በላይ ዋንጫዎችን ማሳካታቸውንም አክሏል፡፡

እነዚህ ታዳጊዎች በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በመወከል በርካታ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገባቸውም ተጠቁሟል። በትምህርትና በስፖርቱ የመሪነት ቦታን እንዲሁም በውጪ ሀገር አሠልጣኝ የሆኑ ስፖርተኞችን ለማፍራትም ችሏል። በኢትዮጵያ ታዳጊዎችን የሚያሳትፍና የሚያበረታታ ውድድር በስፋት ባለ መኖሩና እራሳቸውን የሚያነቃቁበት ውድድር በማስፈለጉ ውድድሩ እንደተዘጋጀም አመላክተዋል። በተጨማሪም በሥልጠና ላይ ለሚገኙ ታዳጊዎች የውድድር ዕድል ለመፍጠርና ጠንካራ ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ታስቦ ውድድሩ እንደተዘጋጀም አሠልጣኙ ገልጸዋል።

የቀድሞ የቴኒስ ተጫዋችና የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ አቶ ብርሃኑ አበበ፣ የታሪኩና ደስታ ክለብ ፕሮጀክት ሊበረታታ እንደሚገባ ገልፀው፣ የስፖርቱ ትልቁ ችግር ውድድር ማዘጋጀት መሆኑን ጠቁመዋል። ድጋፍና ገንዘብ ከሌለ ውድድር ማዘጋጀት የማይቻል በመሆኑ እንደ ሶሊኖ ኢትዮጵያ ኮፊ ያሉት የስፖርቱ ደጋፊዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። ስፖርቱ ያለ ውድድር የትም መድረስ የማይችል በመሆኑ በስፋት ሊሠራበት ይገባልም ብለዋል። ለዚህም ታሪኩና ደስታ ውድድሮችን የማዘጋጀት ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አበረታተዋል፡፡ በተጨማሪም በፕሮጀክቱ ውስጥ አልፈው ለትልቅ ደረጃ የበቁ ስፖርተኞች ድጋፋቸውን እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል። በሜዳ እጥረት ምክንያትም በርካታ የቴኒስ ክለቦች ባለመኖራቸው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You