የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በርካታ ወጣቶችን ሥራ ፈጣሪ የሚያደርግ ዘርፍ ነው

  • ኮሌጁ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከሁለት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ይቀበላል

አዲስ አበባ፦ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በርካታ ወጣቶችን ስራ ፈጣሪ የሚያደርግ መሆኑን የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ፡፡ ኮሌጁ ለ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሁለት ሺህ ሰላሳ ዘጠኝ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ተጠቁሟል፡፡

የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ተሾመ ፈይሳ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ፤የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በርካታ ወጣቶችን ብቁና ተወዳዳሪ ብሎም ስራ ፈጣሪ የሚያደርግ ዘርፍ ነው፡፡

ከኮሌጁ የተመረቁ በርካታ ባለሙያዎች የራሳቸውን ስራ ፈጥረው በመሰማራትና በትልልቅ ኩባንያዎች ሳይቀር በመቀጠር ለሀገር አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ አውስተው፤ ዘርፉ ለበርካታ ወጣት ባለሙያዎች ስራ እየፈጠረና ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኮሌጁ ለ2017 የትምህርት ዘመን ሁለት ሺህ ሰላሳ ዘጠኝ ተማሪዎችን በአስራ አንድ የተለያዩ የስልጠና ዘርፎች እና ከ40 በላይ የትምህርት ክፍሎች በመደበኛ፣የማታ፣የቅዳሜና እሁድ እንዲሁም አጫጭር ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

ዘንድሮ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ መግቢያ ነጥብ የሚያሟሉ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የ12ኛ ክፍል የጨረሱ የመግቢያ ነጥብ ያላቸውን እንዲሁም የመጀመሪያ ዲግሪና ሁለተኛ ያላቸው የሚቀበል መሆኑን አስታውቀዋል።

ኮሌጁ በብረታ ብረት እና እንጨት ስራ፣ በአይሲቲ፣በሆቴልና ቱሪዝም፣በሜካፕ፣ በፀጉር ስታይሎች፣ በአውቶሞቲቭ፣ በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽን ፣በቢዝነስ እና ፋይናንስ እንዲሁም በሌሎች የሙያ ዘርፎች ስልጠና የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም በኮሌጅ ደረጃ እንደሀገር ብቸኛ የሆነውን የስቴቲክስ ሙያ የሚሰጥ ተቋም መሆኑ ከሌሎቹ የሚለየው መሆኑን ጠቅሰው፤ስልጠናውንም በከተማው ብሎም ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚመጡ ተማሪዎች እየሰጠ የሚገኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ስልጠናውን በተደራጁና ደረጃቸውን በጠበቁ ቤተሙከራዎች የተግባር ስልጠና መስጠት፣ ስልጠና ላይ እያሉ ከኢንዱስትሪዎች ጋር በተግባር ልምምድ ቀድመው ከገበያው ጋር እንዲላመዱ ማድረጉና ስልጠናው ከመጠናቀቁ በፊት የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ወስደው ብቁ እንዲሆኑ ማድረጉ ኮሌጁን ተመራጭ የሚያደርጉት ናቸው ብለዋል፡፡

አቶ ተሾመ እንደገለጹት፤ ስልጠና ከመጀመሩ በፊት በአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ አማካኝነት የስራ ገበያ ፍላጎት ያጠናል፡፡ በዚህም ሰልጣኞች በቀጥታ የስራ ገበያ ካላቸው ተቋማት ጋር ሊተሳሰሩባቸው የሚችሉባቸው እድል ይመቻቻል፡፡ መቀጠር ብቻም ሳይሆን የራሳቸውን ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችል ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

የከተማውን ወጣቶችና ስራ ፈላጊዎች በአነስተኛ ዋጋ ጥራቱ በተረጋገጠ የክህሎት ስልጠናዎች በመሰልጠንና በመማር ስራ ፈጥረው ራሳቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም

Recommended For You