አዲስ አበባ:– ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ትብብርና መግባባትን መርሆዋ አድርጋ ትቀጥላለች ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ:: የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከእራሱ አልፎ የሌሎችን ሰላም በመጠበቅ ምስጋና የተቸረው የሀገር መሠረት የሆነ ተቋም መሆኑን አመልክተዋል::
117ኛው የመከላከያ ሠራዊት በዓል “በፈተናዎች ውስጥ እየተገነባ የሚገኝ ሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ትናንት ተከብሯል:: በወቅቱ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ የትብብር ከፍ ሲልም ለሌላው የመትረፍ ልምድ ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህንንም አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል::
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሲሆን መተባበርን ምርጫዋ አድርጋ ትሠራለች፤ ከመተባበር ውጪ ደግሞ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን በውይይትና በመግባባት እንዲፈታ የምትፈልግ የመርህ ሀገር ናት ሲሉ ገልጸዋል::
ለምክክር ዝግጁ መሆን አስፈላጊ ቢሆንም የሀገራችን የፖለቲካ ነፃነትና ሉዓላዊነት የሚበየነው በጀግናው ሠራዊት ተጋድሎ ነው ሲሉ አብራርተዋል:: ሠራዊታችንም ከእራሱ አልፎ የሌሎችን ሰላም በመጠበቅ ምስጋና የተቸረው የሀገር መሠረት የሆነ ተቋም መሆኑን አንስተዋል::
በቅርቡ በመዲናዋ በተካሄደው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሪፎርም የተደነቀና አርዓያ መሆን የሚችል መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት የሀገሪቷ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ታላላቅ ድሎችን የፈፀመ መሆኑን ጠቁመዋል::
መከላከያም እንደ ተቋምና እንደ ሠራዊት በዘመናት ያዳበረውን ፈተናና አይበገሬነት የጥንካሬ ምንጭ አድርጎ በመውሰድ አቅሙን አጎልብቷል ሲሉ ገልጸዋል::
ሠራዊቱ የኅብረታችን መድመቂያ የልዩነታችን ማስወገጃና አንድ ማድረጊያ ውህድ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በኢትዮጵያ ለሚገኙም ሆነ ለሌሎ ችም አርዓያ የሚሆን ተቋም ነው ብለዋል::
የገጠሙንን ፈተናዎች በመመከት በግዳጅ ተሰማርታችሁ ለእናት ሀገራችሁ ለምትሠሩ የመከላከያ ሠራዊት አመራርና አባላት እንዲሁም ቤተሰቦች ልባዊ አክብሮቴን እገልጻለሁ ብለዋል:: ሁሉም ዜጋ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ረገድ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል::
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፤ ሠራዊቱ በቴክኖሎጂ፣ በአቅምና በተለያዩ ጉዳዮች እራሱን ማደራጀት መቀጠሉን ጠቁመዋል::
ወቅቱ በሚፈልገውና የሀገሪቷ ሁኔታ በሚፈቅደው ልክ አቅሙን እያሳደገ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ማስጠበቁን ይቀጥላል ብለዋል::
ኢትዮጵያን በደም መስዋዕትነት ያቆየውን ሠራዊት ለመገንባት ሰፊ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰው፤ ጠንካራ በብሔርና በጎጥ የማይከፋፈል ሀገራዊ እሳቤ ያለው ተቋምና ሰራዊት መገንባቱን አስረድተዋል::
በመርሀ ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሀመድ (ኢ/ር)፣ አባት አርበኞች ፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል::
በዕለቱ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ሚዲያዎች ስለኢትዮዽያ የሚሟገተውን መሐመድ አልአሩሲን ጨምሮ አራት ኢትዮጵያውያንን የክብር አባል አድርጓል::
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም