አዲስ አበባ፡– አዲስ አበባ ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስድስት ዓለምአቀፍ ጉባኤዎችን (ኮንፍረንሶች) በስኬት ያካሄደች መሆኗ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን በተግባር እያረጋገጠች መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ባሕል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረ እግዚአብሔር በዓለም ለ37ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን ምክንያት በማድረግ ትናንት መግለጫ ሲሰጡ እንዳሉት፤ በመዲናዋ ከ2011 ዓ.ም ወዲህ በርከት ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፋራዎች በመገንባታቸው የከተማዋን ልዕልና ከፍ ያደረገ ነው። በዚህም ከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስድስት ዓለምአቀፍ ጉባኤዎችን (ኮንፍረንሶች) በስኬት አካሂዳለች፡፡በዚህም የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን በተግባር እያረጋገጠች ነው፡፡
አዲስ አበባ ከተማ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን በተግባር እያረጋገጠች ያለች መሆኗን ጠቅሰው፤በአጭር ጊዜ ውስጥ ስድስት ዓለምአቀፍ ጉባኤዎች (ኮንፍረንሶች) በከተማዋ ተካሂደዋል ብለዋል፡፡
ከተማዋን ይበልጥ ለማስተዋወቅ በከተማዋ የሚገኙ ከ70 በላይ አምባሳደሮች የተሰሩትን የልማት ስራዎች ማለትም መስቀል አደባባይ፣ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች ስፍራዎች ለማሳየት ልዩ ጉብኝት የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሰላም ለዘርፉ ዕድገት እጅግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ወጣቶች ለሀገራቸው ሰላምና ልማት እንዲተጉም አርአያ የሚሆኑ የልማት ስራዎችን ማስጐብኘት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡
ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ ወጣቶች ከከተማዋ ወጣቶች ጋር በማስተሳሰር የከተማዋ የልማት ስራዎች እንዲጎበኙ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን አመልክተው፤ የሰላም መረጋገጥ ለከተማ ዕድገትና የልማት ስራዎች መሳካት ጉልህ ሚና እንዳለው አዲስ አበባ አንዷ ማሳያ መሆኗን ወጣቶች እንዲገነዘቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በዓሉን ምክንያት በማድረግም የአዲስ አበባን ለውጥ እና አወንታዊ ጉልበት ለሌሎች እንዲዳረስ ቱሪዝም ለሰላም በሚል መሪ ቃል ሲምፖዚየም እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ 400 ያህል ተሳታፊዎች የሚሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች በተለይ ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው የሚቆረቆሩ እና በጎ ገፅታ የሚያስደስታቸውን በማሰባሰብ ከተማዋን ከማስጎበኘት ባሻገር የእግር ጉዞ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዓለም ለ45ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም ቱሪዝም ቀን ምክንያት በማድረግ “ቱሪዝም ለሰላም” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ከጥቅምት 21 እስከ 23 / 2017 ዓ.ም ቀናት በተለያየ ሁነቶች በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር ታውቋል፡፡
ሄርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም