አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ በበጋው ወቅት መርሀ ግብር ከስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሰጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከአንድ ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትን የ2017 በጀት ዓመት የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መክፈቻ መርሀ ግብር ትናንት ተካሂዷል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት የበጋ ወቅት ከስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
በኮሚሽኑ የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ መንግሥት የዜጎችን ማህበራዊ ፍትህ በማረጋገጥ ረገድ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም መንግሥት ሊሸፍነው ያልቻለውን በርካታ ሥራዎች በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም የመደጋገፍ እሴትን ማጠናከር ችሏል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም አንድ ሚሊዮን በጎ ፍቃደኞች እንደሚሰማሩ የገለጹት አቶ ዳዊት፤ ከ781ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደታሰበ ጠቅሰዋል። በዚህም ከስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሠጣል ነው ያሉት። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶቹም ሰብዓዊ ድጋፎች፣ የቤት እድሳት፣ አረንጓዴ ልማት፣ የጤና እንክብካቤና ሌሎች ሰው ተኮር የሆኑ ሥራዎች እንደተካተቱበት ጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ደረጀ ካሳ እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እና የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ከመሆኗ ባሻገር የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችም የሚስተዋሉባት ናት። ችግሮችን ለማቅለል በጎነትን በማስፋፋት የተለያዩ ሰው ተኮር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 12 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንደተቻለ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። በተሰሩ የሰው ተኮር በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መቅረፍ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ይበልጥ በማጠናከር በተያዘው በጀት ዓመት በ12 ፕሮግራሞች በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ በጎ ፈቃደኞች፣ ባለሀብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፣ በ2016 የክረምት በጎ ፈቃድ ፕሮግራም የተሰሩ ስራዎችን በማስቀጠል የ2017 በጀት ዓመት የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሻለ ውጤት እንደሚሰራ ተጠቅሷል፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም