ኢንስቲትዩቱ በፋሽን ቴክኖሎጂና ዲዛይን ትምህርት መስክ ስልጠና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ዓመት በፋሽን ቴክኖሎጂና ዲዛይን ትምህርት መስክ ስልጠና ሊሰጥ መሆኑን የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤የፋሽን ቴክኖሎጂና ዲዛይን የስልጠና መስክ በገበያው ተፈላጊ መሆኑ ተለይቷል። በዚህ መነሻነትም በተያዘው ዓመት በኢንስቲትዩቱ የፋሽን ቴክኖሎጂን በደረጃ ስድስት ለመስጠት በሴኔት ጸድቋል፡፡

በባዮ ሜዲካል ቴክኖሎጂ፣ በአቪዬሽን፣ በማዕድን፣ በሬልወይ ኢንጂነሪንግ እና ሌሎች አዳዲስ የስልጠና መስኮችን በማካተት በቴክኒክና ሙያ የሚሰጡ ስልጠናዎችን ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ተፈላጊ የሆኑት የባዮሜዲካል ቴክኖሎጂ፣ የአቪዬሽን፣ የማዕድን፣ የሬልወይ ኢንጂነሪንግ እና ሌሎች የስልጠና መስኮች ስርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም ቀረጻ) ሲጠናቀቅም ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የፕሮግራም ቀረጻና ክለሳ ተጠናቆ ውይይት እየተደረገበት እንደሆነ ጠቁመው፤የፕሮግራም ቀረጻና ክለሳው በኢንስቲትዩቱ የሚሰጡት ስልጠናዎች የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ምን ያህል ታሳቢ ያደረጉ ናቸው የሚለውን የሚፈትሽ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ በደረጃ ስድስት 21 የስልጠና መስኮች በደረጃ ሰባት ደግሞ 19 የስልጠና መስኮች መኖራቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ ካሉት የስልጠና መስኮች በተጨማሪ አዳዲስ የስልጠና መስኮችን ለመጨመር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በአጭር ጊዜ ስልጠና የሚሰጡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የሮቦቲክስ እና ሌሎች የስልጠና መስኮችን ወደ መደበኛ የስልጠና መስክ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የዜጎችን ህይወት የሚቀይር ተቋም መሆኑን አምኖ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤በቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ውጤታማ ከሆኑ ሀገራት ማለትም ከጀርመን፣ ከቻይና፣ ከፊላንድ፣ ከኮሪያ፣ ከሲንጋፖር ልምድ በመውሰድ ሀገር በቀል ከሆኑ የሙያ መስኮች ጋር የማስተሳሰር ስራ መሰራቱን አንስተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በፌዴራል ደረጃ ከደረጃ ስድስት ጀምሮ ስልጠና የሚሰጥበት ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ የሳተላይት ተቋማትን ጨምሮ 10 ሺህ የሚደርሱ ሰልጣኞችን የመቀበል አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰልጣኞችን የመቀበል አቅም መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው የትምህርት ዘመን የሰልጣኞች ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን፤ የግብዓት አቅርቦትን የማሟላት፣ የአሰልጣኞችን አቅም የማሳደግ እና ሌሎች በርካታ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቴክኒክና ሙያ ለዜጎች የተግባር ክህሎት የሚያስጨብጥ ተቋም ስለሆነ የብዙ ዜጎች ህይወት የሚቀይር ነው ብለዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም

Recommended For You