ቪታ ፉድ ኢንዱስትሪ ምርቶቹን አስመስለው ለገበያ የሚያቀርቡ አካላት መኖራቸውን አስታወቀ

አዲስ አበባ፡- ቪታ ፉድ ኢንዱስትሪ ምርቶቹን ለጤና እክል ሊሆኑ በሚችል መልኩ አስመስለው አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡ አካላት መኖራቸውን አስታወቀ።

የቪታ ፉድ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው፣ የደህንነትና የጤና መስፈርቶችን ያሟሉ ጣፋጭ ምርቶችን ለንግድ ስራ ማቅረብ የምንጊዜም መርሁ መሆኑን ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ አመላክቷል፡፡

የቪታ ፉድ ኢንዱስትሪ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በርከር እንሰካራ እንደገለጹት፤ድርጅቱ የተቋቋመው ከቱርክ በመጡ ባለሀብቶች ቢሆንም በቱርክ ሀገር ያከባቱትን ሙያዊ ልምድና ቴክኖሎጂ 65 ለሚሆኑ ኢትዮጵያያውያን የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡ ኢንዱስትሪው በራሱ ዲዛይን ላለፉት አምስት ዓመታት ጥራትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ታይ ታይ ከረሜላ እና ሎሊፖፖችን ሲያመርት ቆይቷል፡፡

ድርጅቱ የሚያመርታቸው የታይ ታይ ከረሜላዎች በብዙዎች ዘንድ የታወቁ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ገበያ ተመሳሳይ ምርቶች እየታዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምርቶቹን አመሳስለው የሚያመርቱት አካላት የሚያመረቱበት ቦታ አለመታወቁን እና የሚጠቀሙት የግብዓት ምንነትም ያልተረጋገጠ በመሆኑ ለማህበረሰቡ የጤና ችግር እየሆነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የማህበረሰብ የጤና ችግር ከመሆናቸው ባለፈም በሕጋዊ ኢንቨስተሮች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረብን ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ችግሩን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አሳውቀናል ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ በዚህም ምርታችንን በሕገወጥ መንገድ አመሳስለው ለገበያ የሚያቀርቡ አካላትን ለሕግ ማቅረብ እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡

የቪታ ፉድ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው፣ የደህንነትና የጤና መስፈርቶችን ያሟሉ ጣፋጭ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ የምንጊዜም መርሁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቱርክ ኤምባሲ ዋና ጸሐፊ ሙስጠፌ ከማል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ቱርክ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው እያለሙ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የሁለቱን ሀገራት አጋርነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You