ዜና ሐተታ
ፌኔት ዘላለም የ10ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ከታናሽ ወንድሟ ተማሪ ሚሊካይና ዘላለም እና ከጓደኛዋ ተማሪ ፍራኦል ጋር በመሆን ለአይነ ስውራንና ለአካል ጉዳተኞች የሚያገለግል ስማርት ዊልቸር ሰርተዋል፡፡ ዊልቸሩን በሪሞትና በሞባይል መተግበሪያ መቆጣጠር የሚያስችል ሲሆን በመንገዶች ላይ የተሰመረውን መስመር ይዞ ይጓዛል፡፡
ተማሪ ፌኔት እንደምትናገረው ተጠቃሚዎች በተሰራለት የስልክ መተግበሪያ አማካኝነት ወደሚፈልጉበት ቦታ እንዲታጠፍ ወይም እንዲዞር ማድረግ ይችላሉ፡፡ በድምጽ ትዕዛዞችን ተቀብሎ የተሰጠውን መስመር ተከትሎ በመሄድም አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ዊልቸሩ እግራቸው መንቀሳቀስ ለማይችሉ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለአይነስውራን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው የምትለዋ ተማሪ ፌኔት፤ እንቅፋቶች ሲያገኙትና በአምስት ሴንቲ ሜትር ዝቅታ ላይ ሲደርስ በተገጠመለት ሴንሰር አማካኝነት ሞተሩን በራሱ ጊዜ እንዲያቆም ፕሮግራም የተደረገ መሆኑ ተመራጭና ልዩ እንደሚያደርገው ትጠቁማለች፡፡
በኢትዮጵያ በአሁን ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በርካታዎቹ ዊልቸርን ገዝቶ ለመጠቀም የሚያስችል አቅም የላቸውም የምትለው ታዳጊዋ፤ ስማርት ዊልቸሩ ቀለል ባሉ ግብዓቶች የተሰራ በመሆኑ በስፋት ተመርቶ ወደ ገበያ መግባት ሲጀምር በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚቀርብ ትናገራለች፡፡
ዊልቸሩ የራሱ የሞባይል መተግበሪያ ያለው በመሆኑ ተመርቶ ወደ ገበያ በሚቀርብበት ወቅት ተጠቃሚዎች ከፕሌይ ስቶር ወይም አፕስቶር መተግበሪያውን በማውርድ መገልገል ይችላሉ የምትለው ተማሪ ፌኔት፤ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስትቀላቀል የኢኮኖሚክስና የሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ በመማር በዘርፉ ያላትን ዕውቀትና ክህሎት ይበልጥ የማሳደግ ህልም አላት፡፡
ተማሪ ቶፊክ ሞሀመድ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ከተማሪ ዳዊት ሚካኤል፣ ከተማሪ ፊሊጶስ ተዘራና ከሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የሶላር ትራኪንግ ሮቦት ሰርተዋል፡፡ የሰሩት ሶላር ትራኪንግ ከዚህ ቀደም የሚታወቀውን ውስን የሆነውን የሶላር አቅጣጫ በመቀየር በራሱ ሴንስ እያደረገ በሚፈለገው ሁኔታ በመንቀሳቀስ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ከሌሎቹ ለየት እንደሚያደርገው ይናገራል፡፡
እንደ ተማሪ ቶፊክ ገለጻ፤ የሶላር ትራኪንግ ሮቦቱ የተሞላው ኃይል ሲያልቅ በራሱ ከቤት በመውጣት ቻርጅ ካደረገ በኋላ ወደቦታው ይመለሳል፡፡ በመተግበሪያው አማካኝነት ከተጠቃሚዎች በሚሰጠው ትዕዛዝ ሶላሩ በራሱ ሴንስ አድርጎ አስፈላጊውን ሁሉ ተግባር መፈጸም የሚችልም ነው፡፡
ሶላሩ የማንንም እገዛ ሳይፈልግ አንዴ በተሰጠው ትዕዛዛ አማካኝነት ጸሀይ ሲሆን ወደ ውጭ ይወጣል፤ ዝናብ ሲሆን ወደቤት ይገባል የሚለው ተማሪ ቶፊክ፤ ተጠቃሚዎች የፈለጉበት ቦታ ሆነው ሲያጨበጭቡለት እስካሉበት ስፍራ ይሄድላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ህጻናትም ሆኑ ማንኛውም ግለሰብ ባልተገባ ሁኔታ ከነኩት አላርም በማድረግ የድረሱልኝ ጥሪ ያስተላልፍላቸዋል ይላል፡፡
ለፈጠራ ስራው መነሻ የሆነን በገጠርም ሆነ በከተሞች አካባቢ የሚገኙ እናቶች በቂ የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ምግብ ለማብሰልም ሆነ የተለያዩ የቤት ውስጥ ስራዎችን ለማከናወን እንጨትን በመጠቀም ለተለያዩ የጤና ጉዳቶች እየተዳረጉ መሆናቸው ነው ይላል ተማሪ ቶፊክ፡፡
በተጨማሪም የፈጠራ ስራው በከተሞች አካባቢ ለሚስተዋለው የመብራት መቆራረጥ መፍትሄ ሰጪ እንደሆነ የሚናገረው ተማሪው፤ በአብዛኛው የወዳደቁ እቃዎችን በግብዓትነት በመጠቀም እንደሰሩት ይናገራል።
ተማሪ ሰሎሜ ዳንኤል የ9ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ከተማሪ አማኑኤል ወዳጆ እና ከሌሎች ሶስት የቡድን አባላት ጋር በመሆን የ3D ፕሪንትድ ሮቦት የሆነውን ኦቶ ሮቦት ሰርተዋል፡፡ ይህ ሮቦት በሚቀበለው ትዕዛዝ አማካኝነት ይደንሳል፣ ይራመዳል እንዲሁም ካለበት ሁኔታ ጋር ተስማሚ እንቅስቃሴዎችን ያከናውናል፡፡
እንደ ተማሪ ሰሎሜ ገለጻ፤ ኦቶ ሮቦት የተሰራበት ዓላማም ያለምንም መታከት ሰዎችን ለማዝናናት ሲሆን ፌስቲቫሎች ወይም የሙዚቃ ኮንሰርቶች በሚዘጋጁበት ወቅት በተሞላለት ቻርጅ አማካኝነት ያለምንንም ማቋረጥ ዳንሶችንና እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ፕሮግራሙን ማስቀጠል ይችላል፡፡
አሁን ባለንበት ወቅት በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመጠበቅና ያሉበትን ሁኔታ ለመከታተል አዳጋች እየሆነባቸው መምጣቱን የምታነሳዋ ተማሪ ሰሎሜ፤ ወላጆች ስለልጆቻቸው ስጋት እንዳይገባቸው ኦቶ ሮቦት በተዘጋጀለት የራሱ መተግበሪያና በተገጠመለት ካሜራ አማካኝነት ልጆቹን ከማጫወት በዘለለ ያሉበትን ሁኔታ በተገጠመለት ካሜራው በመከታተል ለወላጆች እንደሚያሳውቅ ትገልጻለች፡፡
ተማሪ ሰሎሜ፤ በቀጣይም ህጻናትን በማዝናናት የእናቶችን ችግር በከፊልም ቢሆን መቀነስ እንዲቻል አሁን ላይ ያለውን ኦቶ ሮቦት ስርዓት ለማሻሻል ማቀዳቸውንም ትናገራለች፡፡
አዲሱ ትውልድ በዲጂታሉ ዓለም በእውቀትና በፈጠራ ብቁና ተፎካካሪ እንዲሆን ዘመኑን የሚመጥን የትምህርት መሰረተ ልማትና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ ከሰሞኑ አቡጊዳ ሮሆቦቲክስና የቴክኖሎጂ ማዕከል ከአብረሆት ቤተመጽሐፍት ጋር በመተባበር ያዘጋጁትን የክረምት ወቅት ስልጠና የወሰዱ ታዳጊዎች የሰሯቸው የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስራዎችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጎብኝተዋል። ታዳጊዎቹ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች መስክ ልቀው ለመውጣትና ሀገራቸውን ለማገልገል ትልቅ ፍላጎት እንዳደረባቸው የሰሯቸው የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስራዎች ትልቅ ማሳያ ናቸው፡፡
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም