አዲስ አበባ፡– በቅርቡ በግብጽ አስተባባሪነት በአፍሪካ ቀንድ የተደረጉ ወታደራዊ ጥምረቶች የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ማደናቀፍ የማይችሉ መሆናቸውን በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ፀጥታ ትምህርት ክፍል መምህር የኔነሽ ተመስገን (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ፀጥታ ትምህርት ክፍል መምህር የኔነሽ ተመስገን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤በቅርብ ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ ወታደራዊ ጥምረት ያደረጉ ሀገራት የራሳቸው የሆኑ የውስጥ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ወታደራዊ ጥምረቱም ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ተደማምሮ ቀጣናውን አለመረጋጋት ውስጥ የሚያስገባው ነው፡፡
እንደ መምህሯ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ሕብረት መቀመጫነቷ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ናት፡፡ በአህጉር ሆነ በቀጣናው ደረጃ የኢትዮጵያ ሀያል መሆን ለሌሎች ስጋት ይፈጥርባቸዋል፡፡ ከዚህ መነሻነትም ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሁለተናዊ ውህደት የምታደርገውን ጥረት የማጣጣል ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡
የግብጽ፣ ሶማሊያና ኤርትራ የሦስትዮሽ የወታደራዊ ጥምረት ስምምነትም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ በቀጣናው የሚስተዋሉ ጣልቃ ገብነቶች፣ ወታደራዊ ስምምነቶችና ጥምረቶች የኢትዮጵያን ማደግና የመልማት ፍጥነት ለመገደብ ያሰቡ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ ያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ የኔነሽ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም መስፈን ያላት ሚና ትልቅ መሆኑ እየታወቀ ኢትዮጵያን ለመግፋት የሚደረጉ ጥረቶች ውጤት አያመጡም፡፡ ግብጽና ሶማሊያ ወታደራዊ ስምምነት አድርገዋል፤ ከጥቂት ወራት በኋላም የግብጽ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ይገባሉ፡፡
ነገር ግን ግብጽ ፍላጎቷ የሶማሊያን ችግር መፍታት ሳይሆን ከኢትዮጵያ ጋራ አለኝ የምትለውን ችግር በቅርበት ለመከታተል ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ ኢትዮጵያ ለሁለንታዊ እድገቷ መሳካት የምታደርጋቸውን ጥረቶች በአጭሩ ለማስቀረት ያቀዱ ናቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚያደርጋትን የባህር በር ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ግብጽ ድንበር አልፋ ለቀጣናው ችግር እየፈጠረች እንደምትገኘ ገልጸው፤የሶማሊያ፣ የግብጽና የኤርትራ ጥምረት እንደ ሉዓላዊ ሀገር መብት ቢሆንም ለኢትጵያ ስጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ የኔነሽ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የጦርነቶች መፈጠር የመጀመሪያው ምክንያት ጥምረት መፍጠር ነው፡፡ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት መነሻው ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን በመሞከሯ ነው፡፡ የሦስቱ ሀገራት ጥምረትም የኢትዮጵያን የማደግና የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ለማዳከምና ለማጥቃት ነው፡፡
ከታሪክ ለመረዳት እንደሚቻለው ሀገራት ጥምረት የሚፈጥሩት ስጋት የሆነባቸው አካል ሲኖር ነው፤ ሦስቱ ሀገራት ያሰባሰባቸው ጉዳይና ፍላጎታቸው ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት መፈራረሟ ነው ያሉት የኔነሽ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ወደብ ማግኘት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖዋን ስለሚያሳድገው ስምምነቱ በኢትዮጵያ ባላንጣዎች አልተወደደም፤ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሆና በኢኮኖሚ እንድትጎዳ ፍላጎታቸው ነው ብለዋል፡፡
እንደ የኔነሽ (ዶ/ር)፤ በምሥራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ ሀያል መሆን በግብጽ በበጎ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ግብጽ የውሃና የምግብ ደህንነት ይኖርብኛል በሚል የተዛባ ስጋት አላት፤ ስጋቷ እውን እንዳይሆን ኢትዮጵያ ደካማ ሀገር መሆን አለባት የሚል የተሳሳተ መርህን ትከተላለች። ከዚህ አንጻር የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ከኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገር ጋር ጥምረት በመፍጠር ለማደናቀፍ እየጣረች ነው፡፡
የግብጽ ስጋት ተገቢ አለመሆኑን ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስረዳት ሞክራለች የሚሉት የኔነሽ (ዶ/ር)፤ ግብጽ እውነታውን ብታ ውቅም መረዳት አትፈልግም፡፡ የሶስቱ ሀገራት የወታደራዊ ስምምነት የቀጣናውን የጸጥታ ስጋት ይጨምረዋል፤ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ጥምረት በመፍጠር ስጋቱን መቀነስ አለባት፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የውጭ ኃይሎች የውስጥ ችግሯን እንዳይጠቀሙበት በፍጥነት በመፍታት አንድ ነቷንና አይበገሬነቷን ማጽናት እንዳለባት ጠቁመዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም