የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የኢትዮጵያና ማሌዢያን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው

አዲስ አበባ፡– ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያና ማሌዢያን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ የሁለት ቀን ጉብኝት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማሌዢያ ኳላላምፑር ትናንት ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የማሌዢያና የኢትዮጵያን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ነው፡፡

እንደ ማሌዢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጻ፤ የሁለትዮሽ ውይይቱን ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው በማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቱክ ሴሪ አንዋር ኢብራሂም አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ውይይት የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር መሆኑን በመግለጽ፤ በተለይም በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ዘላቂ ልማት፣ ጤናን ጨምሮ፣ ቱሪዝምና ትምህርት ትብብር ላይ ያተኮረ መሆኑን የማሌዥያ ዴይሊ-በርንማ ዘግቧል።

ሁለቱም መሪዎች በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው የማሌዢያ የውጭ ጉዳይ፤ ይፋዊ ጉብኝቱ በማሌዢያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ እኤአ በ2023 በአፍሪካ አህጉር የማሌዢያ 26ኛዋ ትልቅ የንግድ አጋር መሆኑዋን በመግለጽ፣በሀገራቱ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ንግድ 446 ነጥብ 8 ሚሊዮን የማሌዢያ መገበያያ ገንዘብ ሲሆን፤ የሀገራቱ የወጪ ንግድ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ24 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ ማሳየቱም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከማሌዢያ የተለያዩ የኤሌክትሪክ፣ ኤሌክትሮኒክ ፣የፓልም ዘይትና ዘይት ነክ የግብርና ምርቶች፣ ጨርቃጨርቅ አልባሳትና ጫማዎችን እንደምታስገባም ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜናም ወደ ማሌዥያ ለሥራ ጉብኝት ያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ በሀገሪቱ ከሚገኙ የቢዝነስ ማህበረሰብ አባላት ጋር መክሯል፡፡ በዚሁ ወቅትም በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የልዑካን ቡድኑ አባላት አብራርተዋል፡፡

በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በቴክስታይልና ጋርመንት፣ በማዕድንና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ የማሌዥያ ባለሀብቶች እንዲሠማሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በሀገራቱ መካከል ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር፣ ኢትዮጵያ ስላላት የኢንቨስትመንት እድልና ቅድሚያ ስለሚሰጣቸው ዘርፎች እና ለባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ለመፍጠር የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት ገለጻ ተደርጓል፡፡

የማሌዥያ ቢዝነስ ማህበረሰብ አባላት በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት የሚያደርግ ልዑክ እንልካለን ማለታቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ልውውጥ ለማሳደግ እንደሚሠሩ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You